Tuesday, October 9, 2018

ነገረ መስቀል



※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፲፮/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
እንኳን ለደመራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! በዓሉ የሰላም የፍቅር የአንድነት እንዲኾንልን እመኛለሁ፡፡ የደመራ በዓልን ስናሰብ በመስቀሉ ላይ የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ በቤቱ ለመጽናት አስፈላጊ የኾነው ነገር ነገረ መስቀሉን ኹልጊዜ ማሰብ ነው። ነገረ መስቀሉን ስናስብ የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ ከማስታወሳችንም በተጨማሪ በግራና በቀኝ የተሰቀሉትን ወንበዴዎች እና ከእግረ መስቀሉ ሥር የቆሙትን ቅዱሳን እንዲሁም በሰማይና በምድር የተደረጉ ተአምራትን እናስብበታለን።
በመጀመሪያ የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ መመልከት ተገቢ ነው። ነገረ መስቀሉ በልባችን ጽላት ከተሳለ ኃጢአትን እናደርግ ዘንድ እጅ አንሰጥም። ምክንያቱም ለቤዛ ዓለም በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ የተሰቀለውን ክርስቶስ በፊታችን እየተመለከትን ኃጢአትን የምናስብበት ጊዜ የለምና። ዮሐንስ ፊቱ ሳይፈታ ቁጽረ ገጽ ኾኖ ዘመኑን ኹሉ ያሳለፈው በመስቀሉ ሥር ቆሞ ለቤዛ ዓለም እጁ በመስቀል ላይ የተዘረጋውን ክርስቶስ ተመልክቶ ነው። እኛ ህግ ጥሰን ትእዛዝ አፍርሰን አምላክነትን ሽተን አትብሉ የተባልነውን በልተን ስለበድልነው ከሰማይ የወረደልን የፍቅር ባለቤት አምላካችን ፈጣሪያችን ጌታችን መድኃኒታችን እርሱ ነው ከመስቀሉ ላይ ዕርቃኑን ተሰቅሎ ያየነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስ «ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት - የሰው ፍቅር ኃያል ወልድን ከሰማይ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው» ይላል። ለመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠ ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል እንደኾነ እናውቃለን። የእኛ ፍቅር አገብሮት አንዳች ኃጢአት ሳይኖርበት ሰማያዊ መለኮት ምድራዊውን ደካማ ሥጋ ተዋሕዶ የቤዛነት ሥራውን ሠርቷል። ይህን የቤዛነት ሥራ የፈጸመው በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ አደባባይ በተተከለው ዕፀ መስቀል ላይ እጅና እግሮቹን ተቸንክሮ ተሰቅሎ ሞቶ ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት መዝ ፸፫÷፲፪ ላይ «ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር - በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ» እንዳለው በምድር ማእከል በኾነችው በቀራንዮ እጆቹን እና እግሮቹን ለችንካር ጎኑንም ለጦር ሰጠ።
«ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል - የአባቶች ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ። የነጻነት አርማ መስቀልም በቀራንዮ አደባባይ ተተከለ» እንዲል (መልክአ ሥላሴ)። የነቢያት ትንቢት የአበው ተስፋ የተፈጸመው በንጽሕተ ንጹሐን በቅድስተ ቅዱሳን በእመ ብርሃን በወላዲተ አምላክ በድንግል ማርያም ነው። በቀራንዮ አደባበይ በተተከለው መስቀል ተሰቅሎ የተመለከትነው ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ነውና የድኅነታችን መጀመሪያ ንጽሕት ዘር ድንግል ማርያም ናት።
ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ ድንግል ማርያምን ማስታወስ ግዴታችን ነው። እርሷ ባትኖር ኖሮ ጌታ ሥጋን ተዋሕዶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ባልተመለከትነውም ነበር። ስለዚህም «የመመኪያችን ዘውድ የድኅነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት አንች ነሽ» እያልን ቅዱስ ኤፍሬም እንዳመሰገናት እኛም እናመሰግናታለን። ስለዚህ ነው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ይህን የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ ማሰብ ይገባናል የምንለው። ጌታ ለመስቀል ሞት ቀራንዮ አደባባይ የደረሰው እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም በርካታ ድብደባዎችን፣ ግርፋቶችን፣ እንግልቶችንና መከራዎችን ተቀብሎ ነው እንጂ። በባህላቸው ሰውን በስቅላት ሲገድሉ ይፈጽሟቸው የነበሩትን ተግባራትም ፈጽመውበታል። እነዚህም፡-
፩ኛ᎐  ከመስቀሉ በፊት ይገርፋሉ። ማቴ ፳፯÷፳፮
፪ኛ᎐ መስቀሉን (የመስቀሉን ግንድ) ተሸክሞ ከከተማ ወደ ውጭ ወዳለው የመስቀያ ቦታ ይወስዱታል። ዮሐ ፲፱÷፲፯-፳
፫ኛ᎐ በምሳሌ ፴፩÷፮ የተጻፈውን በማሰብ በኢየሩሳሌም የነበረው የሴቶች ማኅበር የስቃይ ማደንዘዣ መጠጥ ለሚሰቅሉት ሰው ይሰጡ ነበር። ማቴ ፳፯÷፴፬
፬ኛ᎐ በመስቀል ላይ በችንካር ይቸነክሩታል ወይም በገመድ ያስሩታል። ዮሐ ፳÷፳፭
፭ኛ᎐ ከበደለኛው ራስ በላይ የሟቹን ወንጀል (ጥፋት) ጽፈው ይለጥፋሉ። ጲላጦስ በክርስቶስ የመስቀል ሞት የፈረደበት አይሁድ «ተሳድቧል» ስላሉ ሳይኾን «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ» ስላለ የቄሣር ተቀናቃኝ ነው በማለት ነው። ዮሐ ፲፱÷፲፱
፮ኛ᎐ የተሰቀለውን ሰው ልብስ ወታደሮች እንዲካፈሉት ይደረጋል። ዮሐ ፲፱÷፳፫
፯ኛ᎐ የተሰቀለው ሰው የሚሞተው ደሙን በማፍሰስ ሳይኾን በልቡ ድካም ነው። የሚሰቀለው ሰው ብዙ ጊዜ በኹለተኛው ወይም በሦስተኛው ቀን ይሞት ነበር ማር ፲፭÷፵፬ ወዳጆች እንዳያወርዱትም መስቀሉን በወታደሮች ያስጠብቁታል። ቶሎ እንዲሞት ሲፈልጉም እግሮቹን ይሰብራሉ። ኢየሱስን ግን ጎኑን ወጉት እንጂ እግሮቹን አልሰበሩትም። ዮሐ ፲፱÷፴፩-፴፬

ነገረ መስቀሉን ስናስብ እነዚህን ኹሉ እናስታውሳለን። ይህን ኹሉ መከራ መቀበሉ ስለእኛ እንደኾነም እንረዳለን። ሊቃውንቱም ጌታ የተቀበላቸውን መከራዎች «፲፫ቱ ሕማማተ መስቀል» ብለው አስተምረውናል። እነዚህም ተአስሮ ድኅሪት፣ ተስሕቦ በሐብል፣ ወዲቅ ውስተ ምድር፣ ተከይዶ በእግረ አይሁድ፣ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ፣ ተጸፍዖ መልታህት፣ ተወክፎ ምራቀ ርኩሳን፣ ተኮርዖተ ርእስ፣ አክሊለ ሶክ፣ ፀዊረ መስቀል፣ተቀንዎ በቅንዋት፣ ተሰቅሎ በዕፅ እና ሰሪበ ሐሞት ናቸው። እነዚህን መከራዎች ትኩሳቱን አብርዱልኝ መከራውን አስታግሱልኝ ሳይል ስለእኛ በትሕትና እና በትዕግሥት የተቀበላቸው ናቸው። ስለዚህ በነገረ መስቀሉ ውስጥ ይህንን ኹሉ መከራ የተቀበለውን ኢየሱስ ክርሰቶስ እንመለከትበታለንና በሕይወት ለመጽናት ይጠቅመናል።
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ግራና ቀኝ ያሉትን ወንበዴዎች ማሰብ ያስፈልገናል። እነዚህ ወንበዴዎች የኃጥአንና የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው። በዓለም ፍጻሜ ጊዜ ኃጥአንን በግራው ጻድቃንን በቀኙ አቁሞ ዘለዓለማዊውን ፍርድ ይፈርዳልና በዚያ ምሳሌ እርሱ ባወቀ ይህን አድርጓል። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስብ በዓለም ፍጻሜ ጊዜ የሚጠብቀን ፍርድ ምን ይኾን «ሑሩ እምኔየ» እንባል ይኾን ወይስ ደግሞ «ንዑ ኀቤየ» እንባል ይኾን ብለን ነገረ ምጽአትን እናስታውስበታለንና በቤቱ ለመጽናት እንተጋለን። እዚህ ላይ በተለይ በቀኝ የተሰቀለውን ጥጦስ በምግባር በሃይማኖት እንመስለው ዘንድ ወደ ሰማይ ቀና ብለን ሦስቱን ወደ ምድርም ዝቅ ብለን አራት ተአምራትን ተመልክተን «ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ - አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ» ልንል ይገባናል። እነዚያ ሰባቱ ተአምራት ያለአንዳች ነገር እንዳልተደረጉ ራሳችንን ልናሳስበው ይገባናል። ይህን ኹሉ ተአምር ሳይከፈልብን እየተመለከትን እንደ ዳክርስ የጥፋት ዕቅዳችንን ማቀድ የለብንም። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስብ የተፈጸሙትን ተአምራትም ማስታወስ ይገባናል ማለት ነው።
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ከእግረ መስቀሉ አጠገብ ኾነው ዓይናቸውን ወደ ላይ አቅንተው የተሰቀለውን ጌታ የሚመለከቱትን እና መከራ መስቀሉን አስበው ፊታቸውን በእንባ ያራሱ ቅዱሳንን ማሰብ አለብን። ዮሐ ፲፱÷፳፭ ላይ «በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እኅት፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር» ይላል። በእግረ መስቀሉ የቆሙት ወንጌላዊው ዮሐንስ እና እነዚህ ቅዱሳን ናቸው። ለዚህ ክብር የደረሱት መከራውን ኹሉ ታግሰው ፍርሐታቸውን ኹሉ አርቀው ነው። እስከ ቀራንዮ አደባባይ መከራውን ታግሰን ፍርሐታችንን አርቀን ከእግረ መስቀሉ ሥር ካልተገኘን «እነኋት እናትህ» ዮሐ ፲፱÷፳፯ ለመባል አንችልምና እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ መጓዝ አለብን። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ከልባችን ጽላት ልንጽፈው ያስፈልገናል።
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ያስፈልገናል። መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ ፩ኛ ቆሮ ፩÷፲፰ ላይ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው» ይለናል። ስለዚህ እነዚህን የመስቀሉ ላይ ቃሎች ኹልጊዜም ማስታወስ ማሰብ ይገባናል ማለት ነው ምክንያቱም ኃይለ እግዚአብሔር ነውና። ጌታችን በመስቀሉ ሳለ የተናገራቸው ለእኛ ብርታት ጽናት ድኅነት የሚኾኑ ፯ ቃላት አሉ። እነዚህም ሰባቱ አጽርሐ መስቀል በመባል ይታወቃሉ። እነዚህም ከነሀተታቸው እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ቀርበዋል።
፩. አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ ወለምንት ኀደገኒ፡- አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ ማለቱ ነው። «አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ» ማለቱ ነጽር ሊተ ተመልከት ሲል ነው። ምዕመናንን ከፍትወታት እኵያት ከኃጣውእ ርኵሳት ጠብቅልኝ በዓይነ ምሕረት እይልኝ ሲል ነው። ወለምንት ኀደገኒ፡- አቤቱ ምዕመናንን በበደሉት በደል እኔ ከካስኹላቸው በኋላ ምነው ለምን ችላ ትልብኛለህ አውጣልኝ እንጂ ምነው ገሐነመ እሳት አወረድክብኝ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ሥጋ መልበሱን ሲያስረዳንና እኛን ተገብቶ ሲጸልይልን ነው።
፪. አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ፡- የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ነው። መላእክት በቀትር ፈጣሪያቸውን ሊያመሰግኑ ሲመጡ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁቱን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ፊቱ ደም ለብሶ ሲያዩት ደንግጠው እንደ ሻሽ ተነጸፉ እንደ ቅጠል ረገፉ። ከዚህ በኋላ መልአኩ ሚካኤል ዝም ሲል መልአኩ ገብርኤል ግን በጣም ተበሳጭቶ አይሁድን በሰይፍ ሊያጠፋቸው ሰይፉን አነሣ የዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱን ተዋቸው አታጥፋቸው የሚሠሩትን እና የሚደርጉትን ስለማያውቁ ነው ብሎታል። ገብርኤል ግን የአንተ ቸርነት አያልቅም ብሎ ተቆጥቶ ሰይፉን ወረወረው ሰይፉም የቤተ መቅደሱን መጋረጃ ለኹለት ከፍሎ ወደ መሬት ገባ እስካኹንም ድረስ ወደታች ሲሄድ ይኖራል።
፫. ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ ፡- እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ ማለቱ ነው። ጌታችን የተሰቀለ ዕለት እመቤታችን በከተማው ውላ ነበርና ጌታችን ዮሐንስን ጠርቶ እናቴን ጥራልኝ መከራየን ትመልከት አለው። ዮሐንስም ሄዶ እመቤታችንን እነሆ ልጅሽን ሰቀሉት ሲላት እርሷም ደንግጣ በሐዘን እያለቀሰች እየወደቀች እየተነሣች ከተሰቀለበት ቦታ ደርሳለች። በዚያም ራቁቱን ተሰቅሎ ስታይ ምርር ብላ አለቀሰች መልአኩ ጌታን ትወልጃለሽ ብሎ ያበሰረኝ ብሥራት ሞት ኾኖ በገደለኝ ነበር እያለች አለቀሰች። ጌታም እናቴ ሆይ ብታለቅሽ ብታለቅሽ አይታክትሽምን እኔ ካልሞትኹላቸው ፶፭፻ ዘመን በዲያብሎስ ቁራኝነት የተያዙ ነፍሳት አይድኑም ዛሬ መከራው ሐዘኑ እንደበዛብሽ ነገ ዘመዶችሽ ብርሃን ለብሰው ከሲዖል ሲወጡ ስታዪ ደስታሽ ይበዛልና ተዪ አታልቅሽ አላት። የታመመ ሰው ልጄን ሚስቴን አደራ እንዲል እንዲሁ ጌታም እናት ትኾነው ዘንድ እርሱም ልጅ ይኾናት ዘንድ ለዮሐንስ አደራ ብሎታል። ይህን ቃል የተናገረው ለዚሁ ነው።
፬. ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ፡- ትርጒሙ እንደ መጀመሪያው አምላኪየ አምላኪየ እንዳለው ያለ ነው። ነገር ግን «ኤልማስ» ሲል አይሁድ ኤልያስ ያለ መስሏቸው ኤልያስ መጥቶ ሳያድነው ቶሎ የሚገድለውን ነገር እንስጠው ብለው የዝኆን ሐሞት አጠጥተውታል።
፭. ወአንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነተ፡- አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ማለቱ ነው። ከጌታ ጋር ፪ ወንበዴ ሽፍቶች አብረው ተሰቅለው ነበር። አንደኛው በቀኝ ያለው ጥጦስ በሰማይ ፫ በምድር ፬ ተአምራት ሲደረጉ አይቶ «ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ዳግም ምጽአትከ» እያለ ሲጸልይ ጌታ ወደ የማናይ አንገቱን ዘንበል አድርጎ ግብጽ ስንወርድ የነገርሁህ ኹሉ ደረሰ አለው። ስለዚህ ከሞቴ በቀር የቀረኝ የለምና አንተ አዳምን ቀድመህ ገነት ትገባለህ ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶት አዳምን ተቀድሞ ገነት ግብቷል።
፮. አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ፡- አቤቱ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ ማለቱ ነው። በዘመነ ኦሪት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ነፍስ ከሥጋቸው እየተለየች ሲዖል ትወርድ ነበር አሁን ጌታ ከተሰቀለ በኋላ ግን ገነት ይገቡ ጀመር። ስለዚህ ነፍሳችን እንደ ኦሪቱ ሲዖል ብቻ ሳይኾን ገነት መንግሥተ ሰማያትም እንደምትገባ ሲናገር ነው። አንድም አዳምን ተቀድሞ ጥጦስ ገነትን በደመ ማኅተሙ ከፍቶ ገብቷልና ገነት መግባት መጀመሩን ያሳያል።
፯. ተፈጸመ ኩሉ፡- ኹሉ ነገር ተፈጸመ ሲል ነው። አምላክ የመጣበት የድኅነት ሥራ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ ሥጋውን በመቁረስ እንደፈጸመው እንደደመደመው ሲናገር ነው። በመጻሕፍት የተጻፈው በነቢያት የተነገረው ኹሉ ደረሰ የሰው ልጅም ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ ሲል ኹሉ ነገር ተፈጸመ አለ።
እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ኾኖ ተናግሮ እራሱን ወደ ቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ለየ። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስብ እነዚህን የርኅራኄ ቃላት ማስታወስ ይጠበቅብናል ማለት ነው።
በመጨረሻም ክርስቶስን ለመከተል በቤቱም ለመጽናት የግድ መከራ መስቀሉን ማስታወስ እንደሚኖርብን ጌታችን የተናገረውን እንመለከታለን። ማቴ ፲፮÷፳፬ ላይ «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ» ይለናል። ስለዚህ ነው ነገረ መስቀሉን ማሰብ በቤቱ እንድንጸና ይረዳናል ማለታችን። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተልና በቤቱ ለመጽናት በመጀመሪያ ራስን መካድ ያስፈልጋል። ራስን መካድ የቀደሙትን አባቶችና እናቶች አብነት አድርጎ እውቀቴ፣ ሀብቴ፣ ትምህርቴ፣ ወገኔ ዘመዴ፣ ገንዘቤ ንብረቴ ሳይሉ መድኃኔዓለም ክርስቶስንና ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በመከተል ህገ እግዚአብሔርን ማክበር፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን መጠበቅና ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን መፈጸም፣ በጊዜውም ያለጊዜውም ፀንቶ መገኘት ነው። ሐዋርያት በዚያ ዓይነት መከራ ውስጥ ሳሉ ወንጌልን ያስተምሩ የነበረው ራሳቸውን ስለካዱ መስቀሉንም ስለተሸከሙ ነበር። ራሳቸውን ለሞት ሰጥተዋልና ሞትን አይፈሩም ነበር። ስለዚህ እኛም በቤቱ ለመጽናት ፈተናና መከራውን መሰቀቅ አያስፈልግም። ምክንያቱም እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይካድ ብሏልና። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስንከተለው ምግቤ ምን ይኾን፣ ቤተሰቦቼስ እንዴት ይኾኑ ይኾን ሀብት ንብረቴስ እንዴት ይኾን እያልን ማሰብ የለብንም ለዚህ ነው በመጀመሪያ ራሳችንን መካድ የሚስፈልገው።
ራሳችንን ከካድን በኋላ መስቀሉን እንሸከማለን። መስቀሉ መከራው ነው፤ መስቀሉ ስቃዩ ነው፤ መስቀሉ መራብ መጠማቱ ነው፤ መስቀሉ መታሰሩ ነው፤ መስቀሉ መደብደብ መገረፉ ነው፤ መስቀሉ ሥጋን ብቻ ለሚገድሉት ራስን ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ነው። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ በቤቱ እንጸናለን ማለታችን በእነዚህ ነገሮች ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ» ገላ ፭÷፩ ላይ ይለናል። ስለዚህ በመስቀል ሞቶ ነጻነት የሰጠንን አምላክ በማስታወስ በባርነት ቀንበር ዳግም እንዳንያዝ በቤቱ መጽናት ይጠበቅብናል ማለት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው ወይም ዳግም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ፤ በሰይጣን ምክር ዳግም እንዳንታለል የምንኾነው፤ የምንበረታው ደግሞ ነገረ መስቀሉን ማሰብ ስንችል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ገላ ፫÷፩ ላይ «የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዐይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ኾኖ ተስሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ ዐዚም ያደረገባችሁ ማነው» ይላል። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ኹልጊዜም ማሰብ እንደሚገባን ቅዱሱ ሐዋርያ ያስተምረናል። ነገረ መስቀሉን እንዳናስብ የሚያደርገን ዐዚም እንደኾነ ነው የሚገልጽልን። ስለዚህ ኹልጊዜ ነገረ መስቀሉን ማሰብ ማስታወስ በቤቱ እንድንጸና እና ከቤቱ እንዳንወጣ ይጠቅመናል።
የደመራ በዓልን የምናከብረው ይህ ድኅነት የተፈጸመበት መስቀል ከተቀበረበት ተቆፍሮ መውጣቱን በማስታወስ ነው፡፡ ንግሥት ዕሌኒ አይሁዳውያን በምቀኝነት ቆሻሻ እየደፉ የቆሻሻ ተራራ የሰሩበትን የመስቀሉን መገኛ እጣን በማጤስ ጢሱ የሰገደበት ተራራ የጌታ መስቀል የተቀበረበት ቦታ መኾኑን ያወቀችበት ነው፡፡ ይህንን ምክንያት አድርገን ደመራ በዓልን እናከብራለን፡፡ መስከረም ፲፯ ቁፋሮውን አስጀምራ መጋቢት ፲ መስቀሉን አግኝተዋለች፡፡ በዓሉ የቤተክርስቲያናችን በዓል እንደመኾኑ መጠን በጥንቃቄ ቢከበር መልካም ነው፡፡ በዓሉን በመንግሥት ባለሥልጣናት ንግግር ማስከፈት፣ ቢራ እየጠጡ መስከር ወዘተ በዓሉን ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንዲለቅ የሚያደርጉ ኹኔታዎች ናቸው፡፡ በዚህ አካሄድ ከቀጠልን በዓሉ መንግሥታዊ እና ዓለማዊ አለፍ ብሎም ባሕላዊ መኾኑ አይቀርም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት በንግግር ካልከፈቱት ብሎ በዓሉን ለሌላ አካል ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ በማኅበር እየተደራጁ ቢራ ውስኪ አረቂውን እየጠጡ እየሰከሩ በየቦታው መውደቅና ለዝሙት ራስን አሳልፎ መስጠት የበዓሉን ድምቀት የሚያደበዝዝ ነው፡፡ በየደመራዎችም እየተሰባሰቡ ስእለት በመሳል የዛሬ ዓመት ይህን ያህል ካሳ ቢራ ይህን ያህል ወይን ይህን ያህል ለስላሳ ይህን ያህል በግ ወዘተ እናቀርባለን ይላሉ፡፡ ከዚህ ያለፈ መንፈሳዊነት ይዘት ያለው ስእለት እንኳ የለም፡፡ እስኪ አንድ ድኃ ልብስ አለብሳለሁ፣ ለአንድ ድኃ ይህን ያህል እንጀራ እሰጣለሁ ወዘተ እንባባል፡፡
እስኪ በበዓሉ ምድር አላድርቃችሁ፡፡ በሉ ሰላም ኹኑልኝ፡፡
※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB

No comments:

Post a Comment