Tuesday, October 9, 2018

ዘጠኙስ ወዴት አሉ? (ሉቃ ፲፯÷፲፯)



Add caption

※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፱/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
Ø  የቃሉ ተናጋሪ፡- መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡
Ø  ቃሉ የተነገረው፡- ከለምጹ ለነጻ ለአንድ ሰው ነው፡፡
Ø  ቃሉ የተነገረበት ምክንያት፡- ከላይ ከቁጥር ፲፪ ጀምረን እስከ ቁጥር ፲፱ ድረስ ስናነብ የምናገኘው ይሆናል፡፡
‹‹ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው፡፡ እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው›› ይላል ስለቃሉ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
Ø  በኦሪት ሕግ መሠረት በለምጽ ደዌ የተያዘ ሰው ከከተማ ውጭ ከሰፈር ርቆ እንዲቆም ይደረግ ነበር፡፡ እነዚህ ዐሥር ሰዎችም በዚህ ምክንያት ነው ከሰፈር ርቀው ቆመው የነበረ፡፡ ዘሌ ፲፪÷፵፭-፵፮ ላይ፡-
‹‹የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይኹን፡፡ ራሱም የተገለጠ ይኹን፡፡ ከንፈሩንም ይሸፍን ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል፡፡ ደዌው ባለበት ዘመን ዅሉ ርኩስ ይኾናል፡፡ ርሱ ርኩስ ነው፡፡ ብቻውን ይቀመጣል፡፡ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይኾናል›› ይላል፡፡
Ø  በለምጽ የተመቱ ሰዎች በአንድ ላይ ይቀመጡ እንደነበር ሲናገር ኢሳ ፮÷፭ ላይ፡-
‹‹እኔም ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመኾኔ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዐይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለኹና ወዮልኝ! አልኹ›› ይላል፡፡ ‹‹ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ›› ሲል በለምጽ የተመቱ ከንፈሮቻቸው የረከሱባቸው ሰዎች በአንድነት ይሰበሰቡ ወይም ተለይተው ይቀመጡ እንደነበር ያስረዳል፡፡
Ø  ከርእሳችን የምንረዳው እና የምንማረው ነገር ምንድን ነው?
እስከ ፍጻሜ ድረስ መጽናት የሚያስገኘውን ዋጋ እንረዳለን፡፡ አበርክቶ ሲመግብ ሲከተለው የነበረው ህዝብ በኋላ መከራን በመስቀል ላይ ሲቀበል  ሸሽቷል፡፡ የ፭ ገበያን ሕዝብ በ ፭ እንጀራ እና በ፪ ዓሣ እስኪጠግቡ ድረስ አበርክቶ አብልቶ ፲፪ መሶብ ፍርፋሪ ሲነሣ የነበረው የሕዝብ ብዛት የሚገርም ነበር፡፡
Ø  ማቴ ፲፬÷፲፮-፳፩ ላይ “ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት ፭ ሽህ ወንዶች ያህሉ ነበር” ይላል እናንተ ቃሉን ከላይ ከቁጥር ፲፮ ጀምራችሁ አንብቡት፡፡ በዚህ የበረከት ሰዓት ሴቶችና ሕጻናት አብረው ተሳትፈዋል ነገር ግን ወንዶች ብቻ ናቸው እንደተመገቡ ተደርጎ የተቆጠሩት ምክንያቱም ሴቶች ሲመገቡ ወንዶች ካዩአቸው ያፍራሉ ሕጻናትም ከሚመገቡት ይልቅ የሚደፉት፣ የሚጥሉት እና የሚያበላሹት ይበዛልና ከቁጥር ውስጥ አልተካተቱም፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ በወንዶች ብቻ ብንወስደው ፭ ሺህ ህዝብ እንደተከተለው ልብ ይሏል፡፡
Ø  እንደዚሁ ያለ ተመሣሣይ ታሪክ አለ ማቴ ፲፭÷፴፬-፴፰ ድረስ ተመልከቱት፡፡ ቁጥር ፴፰ ላይ ያለውን ልጻፍላችሁ እንዲህ ይላል “የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ” ይላል፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ደግሞ ሰባት እንጀራን እና ጥቂት ዓሣን አበርክቶ ፬ ሺህ ሕዝብ በበረከቱ መግቧል፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ እየተከተለው ያለው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ? ለምን ይህ ሁሉ ሕዝብ ይከተለዋል የሚለው መልስ የሚመለሰው በመከራው ጊዜ ነው፡፡
ይህ ኹሉ ህዝብ እስከ መጨረሻው ድረስ አልተከተለውም፡፡ አንድ አንድ እያለ እየሸሸ ጥሎት ሄዷል፡፡ የእጁን ተአምራት ለማየት የቃሉን ትምህርት ለመስማት እስከ መጨረሻው ድረስ የተከተሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ፭ም ፬ም ሽህ የኾነ ሕዝብ ስለተለያዩ ነገሮች ይከተሉት ነበርና ሽሽታቸውም እንደዚያው ኾኗል፡፡ በምክንያት ተከተሉት በምክንያት ሸሹት፡፡
v መልኩን ለማየት ይከተለው የነበረው በአይሁድ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ተደብድቦ፣ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀራንዮ ላይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሲሰቀል ለንጊኖስ ጎኑን በጦር ሲወጋው ያን ጊዜ ይሸሹታል፡፡ ምክንያቱም ደም የሸፈነውን ፊቱን መመልከት አይፈልጉምና፡፡
v ሲያበረክት ለመመገብ የተከተሉትም ተርቦ ፍሬ አልባ ወደ ሆነችው ዕጸ በለስ ሲቀርብና ፍሬ ሲያጣባት ያን ጊዜ በለስን ሲረግም ይሽሹታል አንድም በመስቀል ላይ ሆኖ ተጠማሁ ሲል የራሱን ጥማት የማያረካ እኛን እንዴት ይመግበናል ብለው ይሸሹታል፡፡ (ማቴ ፳፩÷፲፱፣ ማቴ ፳፯÷፵፰፣ ዮሐ ፲፱÷፳፰)
v ፈውስን ሽተው የተከተሉትም እንዲሁ በአይሁድ እጅ በፈቃዱ ተይዞ ሲሰቀል ፈያታዊ ዘጸጋም (ዳክርስ) ራስህን አድን እያለ ያልተገባን ንግግር ሲናገር ሲሰሙ ይኼስ ራሱንም ማዳን አልተቻለውም እንኳን እኛን ሊያድን ብለው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ (ማቴ ፳፯÷፵፪)
ይሸሻሉ የምላችሁ በልባቸው ነው እንጅ በአካልማ ድሮ ነው ችግራቸው ሲፈታ  የሸሹት፡፡ የሰው ልጅ የሚገርመው ታሪኩ እዚህ ላይ የሚጀምር ነው፡፡ ሲያዝ እና ሲለቀቅ በጣም ትልቅ የሆነ ልዩነትን ያሳያል፡፡ በህመም ወቅት እጅግ ከባድ መከራና ሃዘን በደረሰበት ወቅት የሚሰማው አምላኩን የማክበርና በአምላኩ ትእዛዝ የመሄድ ስሜትና በኋላ ይህ ሁሉ አልፎ የደስታ ጊዜ ሲተካለት የሚኖረው ስሜት ይለያያል ስለዚህም አብሮ ፈጣሪውን በደስታው ይለውጠዋል፡፡ በመከራው ጊዜ፣ በፈተናው ጊዜ በስቃዩ ጊዜ፣ በህመሙ ጊዜ፣ በረሃቡ እና በማጣቱ ጊዜ ስእለት የማይሳልበት ቤተክርስቲያን የለም፡፡ አምላክ መሐሪ ነውና ይቅር ይለዋል፣ ይምረዋል በበረከት በደስታ በፈውስ በጥጋብ ይጎበኘዋል ያን ጊዜ የተሳለውን ስእለት እንኳ አይመልስም ኖኅ እንደላከው ቁራ በዚያው እንደወጣ ይቀራል፡፡ ከላይ እየተመለከትነው የሚገኘው ይህንን መሰል ድርጊት ነው፡፡ በዚህ በበረከቱ ሰዓት ፭ም ፬ም ሺህ ሕዝብ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አሁን ይህ ሕዝብ መከራው ላይስ ይሳተፍ ይሆን?
Ø  እስኪ ወደ መከራው ሰዓት እንሂድ፡፡ ማቴ ፳፮÷፳ ላይ ‹‹በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ጋር በማእድ ተቀመጠ›› ይላል፡፡ እንግዲህ አሁን ፭ ሺህ ሕዝብ የለም ፬ ሽህ ሕዝብም የለም አሁን የቀሩት ከዋለበት የሚውሉት ካደረበት የሚያድሩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፲፪ ቱ መካከልስ እስከ መጨረሻው የሚጸና እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ የሚሄድ ማነው? አሁን እዚህ ላይ እራት እየበሉ ሁለት ነገሮች ተከውናዋል፡፡ የመጀመሪያው ነገር ይሁዳ አይሁድ የመዘኑለትን ሰላሣ ብር በከረጢቱ ይዞ አብሯቸው መቀመጡ ነው፡፡ ሌላኛው ነገር ደግሞ የጴጥሮስ ‹‹ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም›› ያለው መልስ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ይሁዳ የሚስቱ ወንድም የሆነውን ቀማኛ እና ሽፍታ በርባንን እንዲፈቱለትና ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ እንዲይዙለት ከአይሁድ ጋር ምክሩን ጨርሶ የሚያሲዝበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግና ያመቻች ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ያውቅ ስለነበር እንዲህ አለ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል›› በዚህ ሰዓት ደቀመዛሙርቱ ሁሉ እጅግ አዝነው ‹‹ጌታ ሆይ እኔ እሆን›› እያሉ ይጠይቁት ነበር፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ‹‹ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው›› ሲል ይሁዳ ራሱን ያውቅ ነበርና ‹‹መምህር ሆይ አኔ እሆንን አለ ኢየሱስም መልሶ አንተ አልህ›› አለው፡፡
ጌታ በልማዱ ስድስቱን አቁሞ ስድስቱን አስቀምጦ ይዞ ይበላሉ ይመገባሉ፡፡ ዛሬ የቆሙ ነገ ይቀመጣሉ ወጥ የሚያወጣው በተራ ነው፡፡ ጌታ እያወጣ ይበላል አውጡልኝ አይልም ስድስተኛው ለአምስቱ ለራሱም እያወጣ ይበላል፡፡ በዚህ ቀን ከተቀመጡት አንዱ ይሁዳ ነበር  ወጥ ማውጣትም ተራው ነበርና ‹‹ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ ይሰጠኛል›› ሲል ይሁዳ እርሱ እንደሆነ አልጠፋውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እንጀራውንና ጽዋውን በየተራ አንሥቶ ባርኮ መግቧቸዋል፡፡ የሐዲስ ኪዳንን የቁርባን ሥርዓት አስተምሯቸዋል፡፡ እንግዲህ የይሁዳ ልብ እንደሸፈተ ነውና ከደቀመዛሙርቱም መካከል አንዱ ቀነሰ ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ውሎውና አዳሩ ከአይሁድ ጋር ሆነ የአባቱን ቤት የጌታውን ጋጣ ዘነጋ፡፡ የይሁዳ ዓይን በሰላሣ ብር ተሸፈነ ፈጣሪውን ለወጠው፡፡ ከ፲፪ቱ ደቀመዛሙርት መካከል ፲፩ዱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
Ø  ሌላው የሚገርመው ነገር የጴጥሮስ መልስ ነው፡፡ ጴጥሮስ እንዲህ አለ ‹‹ሁሉም ባንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም›› እንግዲህ ጴጥሮስ በራሱ ተመክቶ ነገ የሚሆነውን የሚደረገውን ነገር ስላላወቀ ከሁሉም ይልቅ ጌታውን አብልጦ እንደሚወደውና ከእርሱም እንደማይሸሽ ፈጥኖ ተናገረ፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አለው ‹‹እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ›› ጴጥሮስ ግን አሁንም በራሱ እንደተመካ ነበር ‹‹ከአንተ ጋራ መሞት እንኳ የሚስፈልገኝ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ›› አምላኩ የሚነግረውን እንኳ ማመን አቃተው፡፡ እስከሞት ድረስም እንደሚታመን በራሱ አንደበት ተናገረ፡፡
በእውነት ግን ጴጥሮስ በዚያች ሌሊት እስከሞት ድረስ ይታመን ይሆን? እናንተ ማቴ ፳፮ን በሙሉ እያነበባችሁ ተከተሉኝ አሁን ይሁዳ መምህር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ስሞ ለአይሁድ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ወደሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ወሰዱት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ማንም ቢክድህ አልክድህም እስከሞት ድረስ እከተልሃለሁ ያለው ጴጥሮስ እስከዚህ ግቢ ድረስ በሩቅ ሆኖ ነበር የሚከተለው፡፡ የአይሁድ ጭፍሮችን ፈራ ነገር ግን ደግሞ አልክድህም ያለው ቃል አሰረው ስለዚህ በሩቅ ሆኖ መከተሉን መረጠ፡፡ ቁጥር ፷፱ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ከቤቱ ውጭ በዐጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር አንዲት ገረድም ቀርባ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው፡፡ እርሱ ግን የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ፡፡ በተድላና ደስታ ዘመን ምንም መከራ ሳይኖር እስከሞት ድረስ እታመናለሁ ብሎ በአፍ መናገር እስከሞት ድረስ መታመን ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ደግሞ ሌላኛዪቱ እንዲህ ጠየቀቸው አሁንም አላውቀውም ብሎ ካደ፡፡ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ አነጋገርህ ይገልጥብሃልና በእውነት አንተ ከእርሱ ወገን ነህ አሉት ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ለሦስተኛ ጊዜ ካደ፡፡ ከዚህ በኋላ ዶሮ ጮኸ የዚያን ጊዜ ያ ኢየሱስ ክርቶስ የነገረው ቃል ትዝ አለውና መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ አሁን በዚህ በመከራው ሰዓት የ፭ ገበያ ሕዝብ የለም ቢኖር እንኳ ለመስቀል እንጅ እንዳይሰቀል ለመከልከል አይደለም፡፡ ሌሎችም ደቀመዛሙርት እንዲሁ በየፊናቸው ልብሳቸውን ጥለው ሁሉ የሸሹ አሉ፡፡ (ማር ፲፬÷፶፩-፶፪) ታዲያ እስከመጨረሻ የጸናው ማነው?
Ø  እስከመጨረሻው የጸናውን ለማወቅ ወደ ራስቅል ኮረብታ ወደ ቀራንዮ እንውጣ፡፡ ዮሐ ፲፱÷፳፭ ጀምራችሁ ተከተሉኝ፡፡ ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ (እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም) የእናቱም እህት (ሰሎሜ የእናቱ የእመቤታችን እኅት ናት፡፡ ሃና ከሞተች በኋላ የቀለዮጳን ሚስት አግብቶ ወልዷታል)፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም (ማርያም ባውፍሊያ) መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር፡፡ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንች ሴት እነሆ ልጅሽ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው፡፡ ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት ይላል፡፡
እንግዲህ ከ፲፪ ቱ ደቀመዛሙርት መካከል መስቀሉ ስር የተገኘው ዮሐንስ ወንጌላዊ ብቻ ነው፡፡ መከራ ላይ እንዲህ ነው ሁሉም ይሸሻል ሁሉም ይርቃል፡፡ አበርክቶ ሲመግብ የተመገበው ሁሉ ዛሬ ላይ የለም፡፡ ፭ ገበያ ሕዝብ ፬ ገበያ ሕዝብ ከበረከቱ የተመገበው ዛሬ የለም፡፡ ያ መልኩን ለማየት፣ ፈውሱን ለመቀበል፣ ከበረከቱ ለመሳተፍ ይከተለው የነበረው ሁሉ ዛሬ ሸሽቷል፡፡ ከዋለበት የዋሉት ካደረበት ያደሩት ሃብት ንብረታቸውን ቤት ልጆቻቸውን ሥራቸውን ሁሉ ትተው የተከተሉት ደቀመዛሙርቱም ራሳቸው በፍርሐት ተይዘው ሸሹት፡፡ መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉምና፡፡
Ø  እነዚህ ፲ ለምጻሞችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ለምጽ የወጣበት ሰው ኃጢአተኛ ነውና ከከተማ ርቆ ይጣላል፡፡ እንግዲህ እነዚህም እንዲሁ ናቸው፡፡ ዓለም ንቋቸው ሰው ጠልቷቸው የሰው ፍቅር ርቋቸው ከዓለም ሁሉ ተገልለው ለብቻቸው ከከተማ ዳር አውጥተው የጣሏቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አምላካችን ክብር ምስጋና ይድረሰውና ኃጢአተኛን የማይጠላ እውነተኛ አምላክ ስለሰው ፍቅር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሕሙመ ሥጋን በተአምራት ሕሙመ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ሲመጣ እነዚህንም ተገናኛቸው፡፡ ዓለም የናቃቸውን ሰው የጠላቸውን እርሱ ቀረባቸው፡፡ እነርሱም ተገቢ የሆነውን ልመና አቀረቡ፡፡ ‹‹እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን›› አሉ፡፡ እርሱም የኃጥአንን ልመና ሰማ ከዚያም ‹‹ኺዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ›› አላቸው፡፡ ካሕናት እንዲህ ያለ ትልቅ ክብርና ጸጋ አላቸው፡፡ አምላክ ሲሆን እዚያው ላይ ማንጻት ሲቻለው እንዴት ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ ይላቸዋል? ንስሐ ግቡ ራሳችሁን ለካሕናት አሳዩ የማሰር እና የመፍታት ሥልጣንን የሰጠኋቸው ናቸውና፡፡ እነርሱም የአምላክን ቃል አክብረው ራሳቸውን ለካህናት ሊያሳዩ ሄዱ  እነሆም ሲሄዱ ነጹ፡፡ ይህን ከለምጽ መንጻታቸውን ግን ለየግል ጥቅማቸው ተጠቀሙበት፡፡
ዛሬም እንዲሁ ነው ንስሐ እንገባለን ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ እንፈወሳለን ሥጋውን እንበላለን ደሙን እንጠጣለን ነገር ግን ይህን ሁሉ ቸርነት ለኃጢአት እንጠቀምበታለን፡፡ ዲቁና፣ ቅስና፣ ቁምስና፣ ጵጵስናን አምላክ ያድለናል እኛ ግን ላልሆነ ነገር እንጠቀምበታል፡፡ መንጻታቸው ከሰው ጋር እንደሰው የሚያስቆጥራቸው ስለሆነ በዚያው እንደነጹ ያነጻቸውን አምላክ ተመስገን ሳይሉ እንደወጡ ቀሩ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፡፡ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ እርሱም ሳምራዊ ነበር፡፡ ኢየሱስም መልሶ ዐሥሩ አልነጹምን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ፡፡ እርሡም ተነሣና ሂድ እምነትህ አድኖሃል አለው፡፡ እንግዲህ የነጹት ዐሥር ነበሩ መንጻቱን አምኖ ያነጻውን ለማመስገን የመጣ ግን አንድ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ ቅድስናው አምላክ መስክሮለታል ‹‹ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር›› ብሎ ቅዱስ ማለት ልዩ ማለት ነውና፡፡ ከሌሎች አስተሳሰብና አመለካከት ተለይቶ ተገኝቷል፡፡ አንድ ሲሆን በዘጠኙ ሃሳብና ምክር ሳይታለል ያዳነኝ ከለምጽም ያነጻኝ አምላኬን ሳላመሰግነው የትም አልሄድም ብሎ ተመልሶ ስለተደረገለት ምስጋና አቅርቧል፡፡
የቀሩቱ ዘጠኞቹ ግን የተደረገላቸውን ድንቅ ነገር ተጠቅመው ተመልሰው ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡ ታጥቦ ጭቃ የሚባለው እንዲህ አይነቱ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ አምላካችን ያደረገልንን ውለታ ዘንግተን ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከመባል ይሰውረን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB

No comments:

Post a Comment