Tuesday, October 9, 2018

«ፍኖተ ሕይወት» በአባ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘሀገረ ካናዳ ---ክፍል ፩



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አባ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው። በውጩ ሲኖዶስ ሥር ያሉ ይመስለኛል። ይመስለኛል የምለው በሀገር ውስጡ ሲኖዶስ ሥር ቢኾኑ ኖሮ ስማቸው ከፓትርያርኩ ስም ጋር ተመሳሳይ ሊኾን አይችልም ነበር። በዚኹ በሀገር ውስጡ ሲኖዶስ ሥር ናቸው ከተባለ ግን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሦስተኛው ፓትርያርክ በደገኛው መናኝ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተወግዘው ስለነበር ስማቸው ተሠርዞ ለሌላ ጳጳስ ስምነት ውሏል የሚለው የአንዳንድ ሰዎች ታሪካዊ መረጃ ሚዛኑ የደፋ ይኾናል ማለት ነው።
በዚህም አለ በዚህ ግን «ፍኖተ ሕይወት - የሕይወት መንገድ» የተሰኘው መጽሐፍ የተደረሰው በካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአባ ማትያስ እንደኾነ መጽሐፉ ይናገራል። ይህ መጽሐፍ በ፫፻፰ ገጾች የተዘጋጀ በምእራፍ ሳይኾን በቁጥሮች ብቻ በ፳፱ ርእሶች የተከፋፈለ ነው። በሽፋን ገጹ ላይ የቅድስት ሥላሴ ሥዕል ያለበት ነው። ይህ ሥዕል ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚያሳትመውን ሥዕለ ሥላሴ ይመስላል። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር ሲያጥኑ የሚያሳይ ነው። በጀርባ ሽፋኑ ላይ ደግሞ የራሳቸው የመጽሐፉ ደራሲ የአባ ማትያስ ፎቶ አለበት። ይህ ኹሉ ሲኾን ግን የታተመበት ዘመን መቼ እንደኾነ አልተገለጠም። ሚሊኒየም ማተሚያ ቤት እንደታተመ ግን በጀርባ ሽፋን ገጹ ላይ ተገልጧል።
ስለመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት ጥቂት ልበላችሁ። ይህን መጽሐፍ እንዳነበባችሁ እርግጠኛ ነኝ። መጽሐፉ ከኹለት መጻሕፍት ላይ በቀጥታ የተገለበጠ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተሰኘው የታላቁ ሊቅ የአለቃ ኅሩይ (፲፰፻፶፭-፲፱፻፵፰) መጽሐፍ ነው። አለቃ ኅሩይ በጎንደር ክፍለ ሀገር በበጌምድር የሊቃውንት ምንጭ የድጓ ማስመስከሪያ የሊቃውንት መነሃሪያ በሆነችው በቤተልሔም የተወለዱ ስመ ጥር ሊቅበሩ:: የእኒህን ታላቅ ሊቅ «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተሰኘውን መጽሐፍ ለኅትመት እንዲበቃ ብዙ ሥራ የሠሩት መምህር ልዑለቃል አካሉ እንደኾኑ በመጽሐፉ መቅድም ገጽ ላይ ተገልጧል። ይህ «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተባለው መጽሐፍ በመጠኑ አነስተኛ ቢኾንም ምስጢረ ሥላሴን በሚገባ ይተነትናል። መጽሐፉ ለንባብ ተስማሚ የማይጎራብጥ የማይሻክር ደስ የሚል ነው። እንዲያውም በልማድ «እንዲህ ነው» እያልን ከመሳሳት የሚጠብቅ ብርቅዬ መጽሐፍ ነው። ይህን መጽሐፍ ሙሉውን በ፳፻፱ ግንቦት ወር ላይ በፌስቡክ እና በብሎግ አድራሻዬ ጽፌዋለሁ።
«ፍኖተ እግዚአብሔር»ን በተመለከተ መምህር ልዑለቃል አካሉ የጻፉትን መቅድም ገጽ እናንተም እንድትመለከቱት ከዚህ ላይ ብጽፍላችሁ ደስ ይለኛል። ነገር ግን አንባቢን ላለማሰልቸት ዋና ፍሬ ነገሩን ብቻ እጽፈዋለሁ። ሙሉውን ከመጽሐፉ እንድትመለከቱ እየጋበዝሁ ማለት ነው።
«ይህ በታላቁ ሊቅ በአለቃ ኅሩይ የተዘጋጀው «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተሰኘው ትምህርተ ሃይማኖት አሥራ አምስት አናቅጽ (መክፈያ ክፍሎች) ያሉት፤ የራሱ የሆነ መግቢያ እና መቅድም ኖሮት እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ አንቀጹ ስፋትና መጠን አልፎ አልፎ አንቀጾችን የሚከፍሉ ክፍላት (ክፍሎች) ያሉት ሆኖ የተዘጋጀ በጣም ጠቃሚ የሆነ መድበል ወይም ምዕላድ ነው:: መጽሐፉ በገጽ ብዙም ባይሆን ከፍተኛ የሆነ ትምህርተ መለኮት በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸበት፤ የቀደሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አስተምህሮ እና የሃይማኖት ርቃቄ የሚያሳይ ነው:: ሊቁ አለቃ ኅሩይ እንዳሉት «በቅጥነተ ሕሊና» የሚታየውን ትምህርተ ሥላሴ የሚያራቅቅ፣ ከመናፍቃን ኑፋቄ የሚጠብቅ ትምህርት ይዟል:: መጽሐፉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከልዩ ልዩ መጻሕፍተ ሊቃውንት መረጃዎችን በመጥቀስ በመረጃ የታገዘ ብስል መጽሐፍ ነው:: የመጽሐፉ ዋና ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን መግለጽ ነው:: ስለ «ስመ አካል»፣ ስለ «ስመ ኲነት»፣ ስለ «ስመ ግብር» በግልጽ ያስተምራል:: ይህ መጽሐፍ «ወላዲ መለኮት» ፤ «ተወላዲ መለኮት»፤ «ሠራጺ መለኮት» ማለት እንደማይገባ ይናገራል:: (አንቀጽ አንድ) በአንድ መለኮት ሦስት ኲነት እንዳለ ይናገራል:: የመለኮት አንድነት አካላትን እንደማይጠቀልል የአካላትም ሦስትነት መለኮትን እንደማይከፍል ያስረዳል:: ይህ መጽሐፍ ሥላሴ በመለኮት አንድ የሚሆኑበትን ምሥጢር ያሳያል:: ከዚህም በተጨማሪ ሥላሴ በግብር በአካል በባሕርይ የሚጠሩበትን ስም ለይቶ ያሳያል:: ስለ ስመ ተረክቦ እግዚአብሔርም ማለት መለኮት ከማለት ጋር አንድ ሲሆን ልዩነት እንዳለው ይናገራል:: እንዲሁም የሥላሴ መንግሥት በአካል ከሦስት የማይከፈል አንድ መሆኑን ይናገራል:: «አብ» ማለት እና «ወላዲ» ማለት «ወልድ» ማለት እና «ተወላዲ» ማለት «መንፈስ ቅዱስ» ማለትና «ሠራጺ» ማለት ልዩ ልዩ እንደሆነ ይናገራል:: ወልድ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሲሆን በተለየ አካሉ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ያሳያል:: መለኮት የሚለውን ቃል በልዩ ልዩ ሥልት ተርጉሞ ያሳያል:: «ኃይል» «ክሂል» «ሥልጣንም” በአካል ከሦስት የማይከፈሉ መሆናቸውን ያስተምራል:: በአጠቃላይ ይህ መጽሐፍ ለትምህርተ መለኮት ደቀ መዛሙርት እና በሃይማኖት ለማደግ በትምህርተ ሥላሴ ለመራቀቅ በሃይማኖት ትምህርት ለመላቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ግሩምና ድንቅ መልዕክት የያዘ መጽሐፍ ነው:: እኔም ይህን ጽሑፍ ለማንበብ ባገኘሁት ጊዜ ለንባብ በሚያዳግት ታይፕ ተጽፎ አንድ መቶ ገጽ ያለው ሆኖ አገኘሁት:: በአነበብኩት ጊዜ በጣም የበሰለ «ትምህርተ መለኮት» የተገለጠበት ትምህርተ ሊቃውንት ሆኖ አገኘሁት:: በመሆኑም የቀደሙት ሊቃውንት አስተምህሮ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደገና አቅንቼ ጽፌ ለአንባቢ በሚመች መንገድ አቅርቤዋለሁ» በማለት መምህር ልዑለቃል አካሉ ይናገራሉ።
በአባ ማትያስ የተዘጋጀው «ፍኖተ ሕይወት» የተሰኘው መጽሐፍም ከገጽ ፩ እስከ ገጽ ፸፭ ድረስ ይህንን ደገኛ «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተሰኘ መጽሐፍ ሙሉውን በቀጥታ ገልብጦታል። ምናልባት ሲገለብጡ የሐሳብ ማቀዳደም ሊኖር ይችላል እንጅ ሙሉው ተገልብጧል። ገጽ ፭ ላይ ግን ሲገለብጡ የጽሕፈት ስህተት ተሠርቷል። ይኸውም «አንድ መለኮት በሦስት መለኮትና በሦስት አካላት ህልው ኾኖ» የሚል ነው። ፍኖተ እግዚአብሔር ላይ ግን «አንድ መለኮት በሦስት አካላት ህልው ኾኖ» ሲል ይገኛል። «ፍኖተ ሕይወት» ላይ የተሠራው መለኮትን ሦስት የማድረጉ ስህተት ሆን ተብሎ የተሠራ እንዳልኾነ ግን አስባለሁ።
«ፍኖተ እግዚአብሔር»ን ገልብጠው ሲጨርሱ ትንሽ የምስጋና መደምደሚያ አክለዋል። ፍኖተ እግዚአብሔር ሲጨርስ ከተጠቀመበት መደምደሚያ ፍኖተ ሕይወት ላይ በትርፍነት የተጨመረው «ሦስተኛም ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ በነፍስ በሥጋ የምታድነን እግዝእትነ ማርያምን በማኅፀነ ሐና ፈጥሮና ከአንስተ ዓለም መርጦ የሰጠን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን አሜን» የምትለዋ ብቻ ናት። ስለዚህ «ፍኖተ ሕይወት» የተሰኘው መጽሐፍ እስከ ገጽ ፸፭ ድረስ «ፍኖተ እግዚአብሔር» የተሰኘውን የአለቃ ኅሩይን መጽሐፍ የያዘ ነው።
ከዚህ በመቀጠል እዚሁ ገጽ ፸፭ ላይ የሚጀምረው አዲስ ርእስ «የሥላሴ ዘላለማዊ ህልውና» የሚለው ሀሳብ ደግሞ «ወልደ አብ» ገጽ ፷፰ ላይ የሚጀምረው ሀሳብ ነው። «ወልደ አብ» የተባለው መጽሐፍ በቅብዐቶች የታተመ እና በ፳፻፲ ዓ.ም የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘ መጽሐፍ ነው። «ፍኖተ ሕይወት» ላይ አባ ማትያስ የገለበጡት ከ«ወልደ አብ» ይኹን ወይም «ወልደ አብ» ከአባ ማትያስ «ፍኖተ ሕይወት» የተገለበጠ ይኹን ግን የሚታወቅ ነገር የለውም። ምክንያቱም ኹለቱም መጻሕፍት የታተሙበት ዘመን የተገለጠ ስላልኾነ ይህ ነው ማለት ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን ኹለቱ መጻሕፍት የሚያመሳስላቸው ባሕርይ እስካለ ድረስ ከየትም ይገልበጥ ከየት ችግሩን መዘርዘር ግድ ይላል። «ፍኖተ ሕይወት» ከ«ወልደ አብ» መጽሐፍ ላይ ሲገለብጥ አንዳንዶችን ከ«ወልደ አብ» ውጭም አስፍቶ ጽፏል አንዳንዶችን ደግሞ ከ«ወልደ አብ» አጥብቦ ጽፏል።
ገጽ ፸፰ ላይ «ቅጥነተ ሕሊናሆሙ ለመንፈሳውያን በኀበ ቅጥነቶሙ ለሥላሴ ከመ ሥጋ ገዚፍ እንዳለ አረጋዊ መንፈሳዊ» እስከሚለው ድረስ ከ«ወልደ አብ» ከወሰዱ  በኋላ «ሥላሴ ቅድመ ዘመን ይመሰገኑ ነበር ካሉ» ብለው ከ«ወልደ አብ» ተለይተው አዲስ ሃሳብ ጀምረዋል። የሀሳብ መቀዳደም ግን እንዳለ አስተውያለሁ። «ወልደ አብ» ዘግይቶ የጻፈውን «ፍኖተ ሕይወት» አስቀድሞ፣ «ወልደ አብ» አስቀድሞ የጻፈውን «ፍኖተ ሕይወት» አዘግይቶ ሲጽፍ ብዙ ቦታዎች ላይ ተመልክቻለሁ። ሥነ ፍጥረትን የተመለከተው የ«ፍኖተ ሕይወት» ማብራሪያ ከ«መጽሐፈ አክሲማሮስ» የተወሰደ ስለኾነ ደስ ይላል። «ወልደ አብ» የተባለው የቅብዐቶች መጽሐፍ ሥነ ፍጥረትን ርእሱን ጽፎ አንድ ገጽ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ ወደ ሌላ ርእስ ይገባል። «ፍኖተ ሕይወት» ግን እዚህ ላይ በየዕለቱ የተፈጠሩ ፍጥረታትን ከሰፊ ማብራሪያ ጋር ይዟል።
ከዚህ በኋላ ገጽ ፻፺፯ ላይ የሚጀምረው «አምስቱ አእማደ ምስጢር» የሚለው ርእስ «ወልደ አብ» ገጽ ፭ ላይ የሚጀምረው ሀሳብ ነው። ከዚያ በኋላ «እንናገራለን» ብለው ከጨረሱ በኋላ ወደ «ወልደ አብ» መቅድም ገጽ ተመልሰው መቅድም ገጹን ሙሉውን ወስደውታል። በነገራችን ላይ «ወልደ አብ» የቅብዐቶች ስለኾነ ከቅብዐቶች መጽሐፍ ለምን ይገለብጣሉ? ማለት አይቻልም። ምክንያቱም እውነት የኾነውን የእኛ ትምህርት ይዘው ቅብዐቶች የጨመሩት ሥርዋጽ ሊኖርበት ስለሚችል እንጅ «ፍኖተ ሕይወት» ላይ እስከዚህ ገጽ ድረስ የተሳሳተ አነጋገር አላየሁበትም። ከቅብዐቶች ጋራም የምንለያየው ምስጢረ ሥጋዌ ላይ እንጅ ስነ ፍጥረት ላይ ስላልኾነ አምስቱ አእማደ ምስጢር መግቢያ ላይም የከፋ ስህተት አላየሁም።
«ፍኖተ ሕይወት» እና «ወልደ አብ» አንድ ኾነው የሚገናኙት ምስጢረ ሥጋዌን ሲጀምሩ ነው። «ፍኖተ ሕይወት» ገጽ ፪፻፲ ላይ «የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምንድን ነው ቢሉ ማንጻት፣ መክፈል፣ ማዋሐድ፣ መፍጠር፣ ማጽናት ነው» ሲል «ወልደ አብ» ግን ገጽ ፻፳፩ ላይ «ማጽናት» የሚለውን «ቅብዕ መኾን» ብሎ መዝግቦታል። በዚህ ሃሳብ ላይ ከ«ወልደ አብ» በተሻለ «ፍኖተ ሕይወት» ጥሩ ጽሑፍ ጽፏል። «መፍጠር» የሚለው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ «ሥግው ቃል ተፈጥሯል» በሚለው ሀሳብ ላይ «ወልደ አብ»ም «ፍኖተ ሕይወት»ም አንድ ኾነው ይገኛሉ። «ፍኖተ ሕይወት» ገጽ ፪፻፲፰ ላይ «ሥግው ቃል እንደተፈጠረ» አብራርቷል። ይህ ደግሞ አርዮሳዊነት ነውና ይህንን በተመለከተ ወደፊት በሰፊው የምናብራራ ስለሚኾን ያን ጊዜ እንመለከተዋለን። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ «ቅብዕ መኾን ነው» የሚለውን ሀሳብ በዚህ ገጽ ላይ ባይጽፉትም ወደፊት በሚያብራሩት ጽሑፍ ላይ ግን አልፈው አልፈው ጣል ሲያደርጉ ይታያሉ።
እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ስለዚህ መጽሐፍ በሰፊው የምንመለከት ይኾናል። ይህን መጽሐፍ የምታከፋፍሉ የምትሸጡ ግን ቆም ብላችሁ ልትመረምሩት ይገባል። መጽሐፉ መገኘት በሌለበት ቦታ እንኳ እየተሸጠ እንደኾነ በውስጥ መስመር ብዙዎች ጠቁመውኛል። ለምሳሌ ደብረ ብርሃን እና ድሬዳዋ ማዕከላት ላይ በማኅበረ ቅዱሳን ሱቅ ዋናውን ማዕከል ጨምሮ እየተሰራጨ እንደኾነ ይታወቃል። መጽሐፉ ችግር የለበትም የምትሉ ካላችሁ ግን እኔ ተሳስቼ ከኾነ ልታርሙኝ ሙሉ መብት አላችሁ። በዚሁ አጋጣሚ ሊቃውንተ ቤተክርትስቲያንም ይህን መጽሐፍ እንድትመረምሩት በትሕትና እጠይቃለሁ። ማኅበረ ቅዱሳን እንዲህ ያለ ስህተት ሲሠራ አይቸ አላውቅም። ኢዲቶርያል ቦርዱ አይቶ ተመልክቶ ገምግሞ የሚያስቀር እና የሚያሳልፍ ስለኾነ ከዚያ እውቅና ውጭ በተወሰኑ ግለሰቦች የገባ ሊኾን እንደሚችል አስባለሁ።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፳፪/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment