Friday, October 12, 2018

ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡ ማቴ ፲፮÷፬፤፲፪÷፴፱----ክፍል ፫


※※※※※※※※
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፫/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※ ※※※※※※※※
ፈውስ
የፈውስ አይነቶች ፪ ናቸው
 ፩. የሥጋ ፈውስ
 ፪. የነፍስ ፈውስ
የሥጋ ፈውስ ማለት ከሰውነት አካላት በሽታዎች መዳን ነው፡፡ የእጅ የእግር የዓይን የጆሮ ወዘተ የነፍስ ፈውስ ስንል ግን የነፍስ ከኃጢአት፣ ከበደል፣ ከአጋንንት ቁራኝነት መዳን ነው፡፡ፈውስ ከማን ይገኛል ያልን እንደሆነ ከእግዚአብሔር በባሕርይው ከቅዱሳን በጸጋ ይገኛል፡፡ መላእክት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ አበው መነኮሳት ነቢያት ካሕናት ይፈውሳሉ፡፡
ፈውስ የት ይገኛል ስንል
፩. በቤተ ክርስቲያን /ሐዋ ፫÷፩-፲/
‹‹ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሏት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማሕፀን ዠምሮ ዐንካሳ የኾነ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየነ ጊዜ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋራ ትኵር ብሎ ወደ ርሱ ተመልክቶ ወደ እኛ ተመልከት አለው። ርሱም አንድ ነገር ከነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን ብርና ወርቅ የለኝም ይህን ያለኝን ግን እሰጥኻለኹ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። ቀኝ እጁም ይዞ ስነሣው በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭሚቱ ጸና ወደ ላይ ዘሎም ቆመ ይመላለስም ዠመር እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከነርሱ ጋራ ወደ መቅደስ ገባ። ሕዝቡም ዅሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት መልካምም በሚሏት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው ርሱ እንደ ኾነ ዐወቁት በርሱም ከኾነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው›› ይላል፡፡ ለዚህ ሰው መዳን ምክንያቱ መልካም በሚሏት ቤተመቅደስ ደጅ መቀመጡ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ጥላ ሥር ስናርፍ ፈውስ ይመጣልናል፡፡ ወርቅ እና ብር ባይሰጡትም እንኳ ወርቅ እና ብር እንዲያገኝ ጤናውን ሰጡት፡፡
፪. በመጠመቂያ ቦታዎች /ዮሐ ፭÷፩-፲/
‹‹ከዚህ በዃላ የአይሁድ በዓል ነበረ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች ዐምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውሃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኛዎችና ዕውሮች ዐንካሳዎችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያዪቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በዃላ በመዠመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይኾን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ዠምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ እስከ አኹን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ ዐውቆ ልትድን ትወዳለኽን አለው። ድውዩም ጌታ ሆይ ውሃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያዪቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለኹ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ ተነሣና ዐልጋኽን ተሸክመኽ ኺድ አለው።ወዲያውም ሰውዬው ዳነ ዐልጋውንም ተሸክሞ ኼደ›› ይላል፡፡ ለዚህ ሰው መደን ምክያቱ በመጠመቂያ ቦታው ላይ በጽናት እና በትዕግስት በመጠባበቁ ነው፡፡ ይህን በማድረጉም ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል ተጣብቆባት የነበረችውን አልጋውን ተሸክሟት ለመሄድ ችሏል፡፡
፫. እግዚአብሔርን በመከተል /ማር ፭÷፳፭-፴፬/
‹‹ከዐሥራ ኹለት ዓመትም ዠምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች ከብዙ ባለመድኀኒቶችም ብዙ ተሠቃየች ገንዘቧንም ዅሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተዃላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። ልብሱን ብቻ የዳሰስኹ እንደ ኾነ እድናለኹ ብላለችና። ወዲያውም የደሟ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደ ዳነች በሰውነቷ ዐወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከርሱ ኀይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ ዐውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሕዝቡ ሲያጋፉኽ እያየኽ ማን ዳሰሰኝ ትላለኽን አሉት። ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ዅሉ ነገረችው። ርሱም ልጄ ሆይ እምነትሽ አድኖሻል በሰላም ኺጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት›› ይላል፡፡ ለዚች ሰው መዳን ምክንያቱ ደግሞ እግዚአብሔርን መከተሏ ነው፡፡
ፈውስ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ተብሎም ይከፈላል፡፡ እውነተኛው ፈውስ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በባሕርይው የሚሰጠን ፈውስ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ በጸጋ የሚገኘውን ፈውስ ማለታችን ነው፡፡ ያ ፈውስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም ሊሆን ይገባዋል፡፡ የመጠመቂያ ቦታዎች ላይ እግዚአብሔር አጋንንትን አሥሮ ያሰቃያቸዋል ለጥቂት ጊዜያት እንኳ ለመቆየት አይችሉምና ከሰዎች ዘንድ ይወጣሉ፡፡ ዳግም ላይመለሱም ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ ፭÷፳፭-፴፬ የተጠቀሰችው ሴት ፲፪ ዓመት ያህል ደም ይፈሳት ነበር የክርስቶስን ልብስ ነክታ ዳነች ዳግም ያ ደዌ አልመጣባትም፡፡ ዮሐ ፭÷፩-፲፰ የምናየው የ፴፰ ዓመት በሽተኛው መጻጉእ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሄዷል፡፡ ሐዋ ፫÷፩-፲ የተገለጠው ሽባ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥ ብለው ፈውሰውታል ዳግም ወደ ሽባነት አልተመለሰም፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያላስገረመው ሰው አሁን ይሠራል (ሠ ጠብቆ ይነበብ)  በሚሉት ነገር ሲደነቁ ልዩ ተአምር ተደረገ እያሉ ሲታለሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ወገኔ ሆይ አትደናገር! አይደለም በሽታ መፈወስ  ቅዱሳኑ ሙት አንሥተዋል እኮ፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት አንሥተዋል፡፡ /መጽሐፈ ነገሥትን ተመልከቱ/ የሰው ልጅ በባሕርዩ ድንቅ በሚባል ተአምር ይታለላል፡፡ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስን እንዲሁም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምራት የምናቃልል ሰዎች ዛሬ ተአምር እናደርጋለን በሚሉ ተኩላዎች አፋቸውን ከፍተው ጉድ ተሠራ እያሉ ሲከተሉ ማዬት አይቶም ዝም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ጭምር ነው፡፡ አጋንንትን የማውጣት ጸጋ የተሰጣቸው ቅዱሳን ጸጋቸው እንዳይገለጥባቸው ያደርጉ ነበር እግዚአብሔር ያስተማራቸው ያንን ነበርና፡፡ እግዚአብሔር በወንጌሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ፈውስ ካደረገላቸው በኋላ ይህንን ተአምር ለማንም እንዳትናገሩ ይላቸው ነበር፡፡ /ማር ፯÷፴፮-፴፯/፣ /ዮሐ ፭÷፲፭/ ቅዱሳን  ፈውስን የሚያደርጉት በነጻ ያለምንም ክፍያ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሐብተ ፈውስን ለሐዋርያት ከሰጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው ለእናንተ ለእጀ ጠባባችሁ ኪስ አይኑራችሁ እኔ በነጻ የሰጠኋችሁን እናንተም እንዲሁ በነጻ ስጡ፡፡ /ማቴ ፲÷፱/ ለዚህም ነው ወርቅና ብር የለንም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣ እያሉ በነጻ ሽባዎችን እየተረተሩ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደርጉ የነበረው፡፡ ሐሰተኛ ፈውስ የምንለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ፈውስ ጊዜያዊ ነው፡፡ በዓይናችን ስናየው እንደነቃለን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተአምር ይመስለናል፡፡ የሰይጣንን ጥበብ ብዙዎቻችን አልተረዳነውም፡፡ ሰው የሚደነቀው በሥጋው መፈወሱን ብቻ ነው ከፈውስ ባሻገር ነፍሱ ምን እንደምትሆን አይረዳም፡፡ ሥጋህ ለምን አይታመም ዋናው እኮ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ የሥጋ በሽታ እኮ በልብሳቸው እና በጥላቸው ይፈውሱ የነበሩት እነ ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስም ነበረባቸው፡፡ ነፍስህን አስብ ትውልዱ!!!!!
በዚህ ዘመን አጋንንትን እናወጣለን የሚሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ነው የሚያወጡ እንላለን፡፡ እውነት ነው የእግዚአብሔር ስም ሲጠሩ እንሰማለን ከእግዚአብሔር ስም በስተጀርባ ምን ይደረጋል እርሱ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ገና ብዙ ነገር ይቀረናል እኮ ምንም አልገባንም ክርስትናው፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራ ስንቱ መጫኛ ያቆማል፣ ድውይ ይፈውሳል፣ የግሉን ገንዘብ ያካብታል መሰላችሁ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡ /ማቴ፯÷፲፭-፲፮/ የበግ ለምድ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ስም፣ ጥምጣሙ፣ ካባው፣ አስኬማው ነው፡፡ ይህ ከላይ የምናየው ለምድ ነው በግ የሚያስመስለው፡፡ ውስጡ ግን እምነቱ፣ ምግባሩ፣ ቅድስናው ወዘተ ተኩላዎች ነጣቂዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያፈሩት ትውልድ ለእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ለራሳቸው መመጻደቂያ፣ ቡና የሚያፈላላቸውን፣ ጫማ የሚያስርላቸውን፣ በየሔዱበት አባቴ አባቴ የሚሏቸውን ነው፡፡ ትውልዱ በዚህ አትደነቅ በመጨረሻው ዘመን ከዚህ የበለጠ ተአምር እንደሚሠራ መጽሐፋችን ይነግረናል፡፡ በምትሀት ፀሐይን እና ጨረቃን ይዞ የሚመጣ ትውልድ የሚነሣበት ዘመን ይመጣል ያን ጊዜ “…ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” ማቴ ፳፬÷፳፬፡፡ አስቡት እንግዲህ የምጡን መጀመሪያ፡፡ ዛሬ በዚህ ተራ በሆነ ቀላል ነገር ሕዝቡ እንዲህ ካመነ ያን ጊዜ ማን ይሆን ጸንቶ የሚቆመው? ማንም ሰው እንዲህ አድርግ እንዲህ አታድርግ ተብሎ የሚመለስበት ጊዜ ላይ አይደለንም ነጻ ፈቃድ የራሳችን ነው፡፡ የፈለግነውን የመከተል መብታችን የራሳችን ነው፡፡ ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል እንዲል መጽሐፉ ተአምራትን ቤተክርስቲያን ገብታችሁ ተመልከቱ፡፡ ጸበል ቦታዎች ሄደን መጽናት ሲደክመን በቀላሉ የተገላገልን እየመሰለን ሰው አንከተል፡፡ አጋንንት የሚወጡት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ሐዋርያት በአንድ ወቅት አጋንንት ያደረበትን ሰው መፈወስ አልችል አሉ፡፡ ኢየሱስም መጣ እና ያንን አጋንንት አስወጣው፡፡ ሐዋርያቱም እኛ ለምን አላወጣነውም ብለው ጠየቁት እርሱም መልሶ እንዲህ አይነቱ መንፈስ በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም አላቸው ይላል ማቴዎስ ወንጌል፡፡ ለዚህም ነው በጸበል ቦታ አጋንንት የሚቃጠሉት እዚያ ላይ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አለ፡፡ አንዳንድ ጸበል ቦታዎች ላይም ተኩላዎች ገብተዋል፡፡ ጸበሉ ማዳን እየቻለ እነርሱ በመስቀል ካልባረክናችሁ ጸበሉ እየፈሰሰባችሁ እኛም መስቀላችንን ካልጫንባችሁ የሚሉ በጸበሉ ስም ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጸበል ልትጠመቅ ከሄድህ ግኙነትህ ከጸበሉ ጋር ይሁን፡፡ ገብተህ ተጠመቅ ቤተክርስቲያን ሄደህ ስገድ ጸልይ አልቅስ ከዚያ ጥሩ መምህር ካገኘህ ተማር ጠይቅ፡፡ ከዚያ ውጭ ዝም ብሎ ማንም እንዲጫወትብህ ቦታ አትስጠው፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ ፈዋሽ እንዴት እናውቃለን ለሚለው የሚከተሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መሟላት አለበት፡፡
፩ኛ. ጸጋ እግዚአብሔር ያደረበት፡፡ ጸጋ ለመሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ሁልጊዜ አብሮን አይኖርም በዚህ ይታወቃል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ሃብተ ትንቢት እንደተነሣው ያለ ማለት ነው፡፡ ኢሳ ፮፥፩-ፍጻ፡፡ ጸጋ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር እጅ ያለ እንጂ በእኛ እጅ ያለ አይደለም፡፡ መርኃ ግብር አውጥተህ ሰዓት ቆርጠህ ቀጠሮ ይዘህ የምትሠራው ሥራ ሳይኾን እግዚአብሔር አድርግ ሲልህ የምታደርገው አታድርግ ሲልህ ደግሞ አልችልም ብለህ የምትተወው ነው ጸጋ፡፡ የዛሬ አጥማቂዎችን ስታይ ግን ዛሬ ኢትዮጵያ ነገ አሜሪካ ከነገ ወዲያ አረብ ከዚያ ወዲያ የኾነ ቦታ የዓመቱን ቀናት ሰዓት አውጥተው ቦታ ወስነው መርኃ ግብር ይዘው ነው የምናያቸው፡፡ መርኃ ግብር ማውጣታቸው ባልከፋ ነበር መርኃ ግብር የሚይዙት በራሱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ብለው አይደለም፡፡ የፈውስ አገልግሎታቸው የጸጋ ሳይኾን የባሕርያቸው አስመስለው ነው የሚይዙት፡፡ ስለዚህ በዚህ እንለይ፡፡ ጸጋ ስለኾነ ሰው ጸጋችንን እንዳያውቅብን እንሸሻለን እንጅ መርኃ ግብር አውጥተን ጠብቁን ጸጋችንን እናሳያችሁ አንልም፡፡ እናሳያችሁ ካልንም ጸጋችን ከሰይጣን የተገኘ እንጂ ከአምላክ የተገኘ አለመኾኑን ያሳያል፡፡
፪ኛ. የሚጾም፣ የሚጸልይ፣ የሚሰግድ፣ በእምነት የጸና መሆን አለበት፡፡ እንዳገኘ እየበላ የላመ የጣመውን እየመረጠ እየተመገበ ጮማ እየቆረጠ ጠጅ እያንቆረቆረ ሃያ አራት ሰዓት እየተኛ እንዲህ ያለ ጸጋ አይገኝም፡፡ ጹሙ ጸልዩ ስገዱ ሲሉ እንጂ እነርሱ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ እነዚህን ሰዎች ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ከእግዚአብሔር ጋር የምንቆጥራቸው? እርሱ የማያውቃቸውን እኛ ግድ እወቃቸው እንዴት እንላለን?
፫ኛ. ለፈወሰበት ጸጋ ገንዘብ የማይቀበል፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው ካላችሁ ሐዋርያትን መምሰል አለባቸው፡፡ ሐዋርያ ሽባ የተረተሩት ሙት ያነሡት ድውይ የፈወሱት በነጻ ነው፡፡ ዛሬ በነጭ ሽንኩርት እያስለፈለፈ ስንት ብር ነው የሚወስደው? የእግዚአብሔር ሰው ከሆንህ በነጻ አገልግል በለው እስኪ፡፡ አጠራቅሞ ቤተ ክርስቲያን ይሠራበታል በጎ አድራጎት ያደርግበታል ወዘተ እንዳትለኝ፡፡ ይህ ከስንት አንዱ እንደሆነ አታውቀውምና፡፡
፬ኛ. ጸጋው በአደባባይ እንዳይገለጥ የሚያደርግ፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ድንቅ ተአምራትን በማድረጋቸው ሰው ከተአምራታቸው መሳተፍ ፈልጎ ሲመጣባቸው ይሰወራሉ ይጠፋሉ ቦታቸውን ለቀው ይሄዳሉ ምክንያቱም ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡ የዛሬዎቹስ ያደርጉታልን?
፭ኛ. ቃለ እግዚአብሔርን ብቻ የሚናገር፡፡ ቃለ እግዚአብሔር የሰይጣን ምስክርነትን አይሰብክም፡፡ ሰይጣንን እውነተኛ አድርጎ ሰይጣን የተናገረውን አያስተምርም፡፡ ሰይጣንን ድምጹን እየቀረጸ አይቸበችብም፡፡ ቃለ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ቃሉ ያቃጥላል፡፡ ቃሉ ይፈውሳል፡፡ ቃሉ ያነጻል፡፡ ቃሉ ይባርካል፡፡ ቃሉ ያጸናል፡፡ ቃሉ ያበረታል፡፡ እነዚህ የዘመኑ ሰዎች የሚያስተምሩት በእውነት እውነተኛ ቃል ነውን? ከየት የተገኘ?
፮ኛ. መፈወስን ሥራው ያላደረገ፡፡ ይህ ጸጋ ነውና አምላክ ሊሰጠንም ሊነሣንም የሚችል በመሆኑ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን አይችልም፡፡ እነ ቅዱስ ጳውሎስ በጥላቸው ቢፈውሱ እግዚአብሔር ጸጋቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ አደረገላቸው እንጅ ዋና መተዳደሪያ ሥራቸው አላደረጉም፡፡ ተአምር አሳይተው የሚበሉትን አልሰበሰቡም ተአምር አሳይተው ለእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑለት አሕዛብን አሳመኑ እንጅ፡፡
፯ኛ. እግዚአብሔር ቅድስናቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ የሚያደርግላቸው መሆን አለበት፡፡ ቅዱሳን ሲበቁ ንጽሕናቸውን ብቃታቸውን ለመግለጽ ሲፈልግ እግዚአብሔር በጸጋ ይጎበኛቸዋል፡፡ በጥላቸው ሙት እንዲያነሱ በልብሳቸው ድውይ እንዲፈውሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ድሜጥሮስ የተባለው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ያደረገው ተአምር እግዚአብሔር ህዝቡን ከሐሜት ለመጠበቅ ያደረገው ነው፡፡ የድሜጥሮስን ንጽሕናና ቅድስናም መስክሮለታል፡፡
፰ኛ. በመርኃ ግብር ዛሬ እዚህ ነገ እዚህ እያሉ የማይሉ ምክንያቱም ፈውስን ማድረግ የጸጋ እንጅ የባሕርይ ስጦታችን ስላልሆነ እግዚአብሔር በፈቀደው እርሱ በወደደው ቦታ እና ጊዜ ድንቅ ሥራውን ያደርጋል እንጅ እኛ በፈቀድነውና እኛ በወደድነው ቦታ እና ጊዜ መፈጸም አንችልምና፡፡
፱ኛ. ሁሉንም በሽታ አድናለሁ የማይል፡፡ ደዌ ዘበጸጋ አለ ለጸጋ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት ከአምላክ የሚሰጠን ደዌ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው በልብሳቸው ሰውን ሁሉ እየፈወሱ እነርሱ ግን በሽታ ነበረባቸው፡፡ ለጸጋ የተሰጣቸው ነውና፡፡
፲ኛ. ሰውን የአጋንንት መነሐሪያ የሚያስመስል፡፡ እንፈውሳለን ብለው ማጥመቅን እንጀራቸው ያደረጉ ሰዎች ሰይጣን ነህ ጋኔን ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሰይጣን ነኝ ወይም ጋኔን ነኝ ይላል ስንት ናችሁ ይላቸዋል፡፡ በጣም ብዙ ነን ከአንድ ሚሊዮን እንበልጣለን ይላሉ፡፡ አንድ ሚሊዮን ሰይጣን አንድ ሰው ላይ ከሰፈረ ያ ሰው ከሰይጣን የተሠራ ነው ማለት ነው፡፡ ብዙ አጋንንት አንድ ሰው ላይ ያድራሉ ይህ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ላይ የሄደው ሰው ሁሉ የሚሊዮን አጋንንት ማደሪያ ይኾናል ብየ አላስብም፡፡ በዚያውስ ላይ ሰይጣን እየተናገረው ያለውን ነገር እውነት ነው ብለን ልንቀበለው እንችላለን ወይ?
፲፩ኛ. ስለራሱ ብዙ የማያወራ፡፡ ተአምሩን ያደረጉት በእግዚአብሔር ስም ከኾነ ማውራት ያለባቸው ስለእግዚአብሔር እንጅ ስለራሳቸው መኾን የለበትም፡፡ ብዙዎችን ተመልከቷቸው እኔ ማነኝ እያሉ ስለራሳቸው የሰይጣንን ምስክርነት ያስደምጣሉ፡፡ አንዳንዶችማ እንዲያውም የሥላሴን የድንግል ማርያምን የቅዱሳን መላእክትን የቅዱሳንን ሁሉ ስማቸውን ያስጠሩ እና አሁን ደግሞ የእኔን ስም ጥራ ይሉታል የእርስዎ ስምስ ያቃጥለኛል ይላል፡፡ አሁን ይህን ሰው በምን ሒሳብ ነው እውነተኛ የምናደርገው? አብዛኞች አጥማቂ ነን ባዮች ከቦታው ይልቅ የራሳቸውን ዝና ነው የሚያስቀድሙት፡፡ እንዲያውም የራሳቸውን ፎቶ የሚሸጡም አሉ፡፡
ከዚህም በላይ እውነተኛውን ከሐሰተኛው የምትለዩበትን መንገድ መፈለግ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ግን ሰውን ለመለየት እነዚህን እጠቀማለሁ፡፡
ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ የተባልነው ያንን የሚሠሩትን ሥራ እንድንገመግም ነው፡፡ በበለጠ ገዳማት ሔዳችሁ ጸበል ቦታዎች ሄዳችሁ እውነተኛ ፈውስ ምን እንደሆነ አረጋግጡ፡፡ በእምነት አትጎስቁሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የዋሃንን ከሚያታልሉ ተኩላዎች ራስህን ጠብቅ መልእክቴ ይህ ነው፡፡
ትውልዱ ለምን አቋራጭ ፈውስን ፈለገ?
ጸበል እንደሚፈውስ ክርስቲያኖች ሁሉ ያምናሉ ግን ዓመት ሁለት ዓመት ደጅ መጽናትን ሊጠይቅ የሚችል ሊሆን ይችላል፡፡ መጾም፤ መጸለይ፤ መስገድ መመጽወት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ግን ወዲያውኑ እንደሄዱ ሐሰተኛውን ፈውስ ይፈጽሙላቸዋል ለነገ የሚያድር ነገር የለም፡፡ ሳይጾሙ፣ ሳይጸልዩ ፣ሳይሰግዱ፣ ሳይደክሙ በቀላሉ ፈውስን አገኙ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው አብዛኛው እንደ በግ ሲነዳ የሚውለው ግን ጊዜያዊ የሥጋ ፈውስ እንጅ ዘላለማዊ የነፍስ ፈውስን አያገኙም፡፡
ፈጸምኩ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ወለወላዲቱ ድንግል፡፡
ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡
※※※※※※※※※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ድረ ገጽ፡-
http://www.melkamubeyene.blogspot.com
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡-
facebook.com/melkamubeyeneB


※※※※※※※※

No comments:

Post a Comment