፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
እስካሁን ባየናቸው ተከታታይ ክፍሎች ቅብዐት የተባለው እምነት ወደ ሀገራችን እንዴት እንደገባ ታሪካዊ አመጣጡን ከታሪክ ድርሳናት አገላብጠን ተመልክተናል። ከዚህ ክፍል ጀምረን ግን ወደ ዋና ጉዳያችን እንገባለን። ቅብዐት የተባለው ምንፍቅና እንዲህ ብሎ የሚያምን ስለኾነ እንዲህ ብለን ከምናምን ተዋሕዶዎች በዚህ መልኩ ይለያል እያልሁ ስናገር የቅብዐቶችን መጽሐፍ በእጄ ይዤ ስለኾነ ማንኛውም የቅብዐት አማኝ ሰከን ባለ መንፈስ ሐሳቤን በሐሳቡ ሊሞግተኝ መብቱ ነው።
ኹላችንም የምንቀበለውን መጽሐፍ እንደ ማስረጃ ስለማቀርብ ያን ማስረጃ መሞገትም መብታችሁ እንደኾነ እንድታውቁ እውዳለሁ። ከዚህ ባለፈ ግን እኔን ያሸማቀቃችሁ መስሏችሁ አፋችሁን ለስድብ ብትከፍቱ ከ፶ ሺህ በላይ የኾነው አንባቢዬ ይታዘባችኋልና ራሳችሁን ለመግዛት ሞክሩ።
ቅብዐት እና ተዋሕዶ የሚለያዩበት ነገር በጣም ቀላል የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው። እንዲያውም ቅብዐት እና ተዋሕዶ ልዩነቱ ምንድን ነው ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ቅብዐቶች ድንግል ማርያምን ተቀባት ይላሉ ተዋሕዶዎች ደግሞ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዷታል ይላሉ ብለው ነው የሚመልሱልን። ይህ ግን የጨዋ ክርክር ነው። ቅብዐቶችም ኾኑ ተዋሕዶዎችም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ተዋሕዷል ብለው ማመናቸው ላይ ምንም ልዩነት የለንም። መሠረታዊ ልዩነታችን ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው የቀኖና እና የዶግማ ልዩነት ነው።
#ቀኖና
ቃሉ የግሪክ ሲኾን ትርጒሙም ሥርዓት ማለት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፬÷፵ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ «ነገር ግን ኹሉን በአገባብና በሥርዓት አድርጉ» ይላል። ስለዚህ ለማንኛውም ሥራችን አግባብ እና ሥርዓት ያስፈልገዋል ማለት ነው። በእምነታችን ለመጽናት እምነታችንን ጠብቀን ለመቆየት ሥርዓት ያስፈልገናል። ኹሉም የመሠለውን የሚያደርግበት መኾን የለበትም። ሥርዓት እንደ አስፈላጊነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ እየታየ ሊጨመርበት፣ ሊሻሻል፣ ሊቀነስ የሚችል ነው። ለምሳሌ ያህል ጥምቀትን በ፵ እና በ፹ ቀናችን የምንጠመቅበት ሥርዓት አለን ነገር ግን ሕጻኑን ለሞት የሚያበቃ ነገር ካገኘው ከዚያም ቀድሞ በሞግዚት ገብቶ እንዲጠመቅ ሥርዓት አለን። ይህ እንግዲህ ቀኖና ስለኾነ ነው። ዶግማ የምንለው ጥምቀቱን ሲኾን ሥርዓተ ጥምቀቱን ደግሞ ቀኖና እንለዋለን ማለት ነው። ዐርብ እና ረቡዕን ከዓመት እስከ ዓመት እንጾማለን ነገር ግን በበዓለ ሃምሳ፣ ገናና ጥምቀት በሚውሉባቸው ዕለታት እንዳንጾም ታዝዘናል በዚህም መሠረት ዐርብና ረቡዕ መኾናቸውን እያወቅን እንበላለን ይህ ቀኖና ነው። በቤተክርስቲያን የቅዳሴ ሥርዓት ላይ ፭ ቀዳስያን ያስፈልጋሉ ነገር ግን ከባድ በኾነ ችግር አምስት ካልተገኘ ከአምስት በታች ሁነው ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ ይህ ቀኖና ነው። ሰው የታወቀ ደዌ ቢኖርበት በአጽዋማት ቀን እንዲጾም አይገደድም በምትኩ ሲሻለው ግን ይጾማል ይህ ቀኖና ነው። ነገር ግን እዚህም ቢኾን እኛ እንደፈለግን የምናሻሽለው የምንለውጠው የምንጨምረው የምንቀንሰው አይደለም ምክንያቱም መሠረታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና።
ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው የቀኖና ልዩነታችን የሚከተሉት ናቸው።
-
አጽዋማት መግቢያ እና መውጫ ላይ ያለ ልዩነት።
(በተለይ ጾመ ነቢያት እና ጾመ ሐዋርያት መቼ ይገባሉ የሚለው ጉዳይ)
-
በዓላት አከባበርን በተመለከተ ያለ ልዩነት
(በተለይ የገና በዓል ታኅሳስ ፳፰ ሊከበር ይችላል አይችልም የሚለው ጉዳይ)
-
ጥምቀትን በተመለከተ ያለ ልዩነት።
(ኹለተኛ ተጠመቁ ተብሏል የሚለው ጉዳይ)
#ዶግማ
ቃሉ የግሪክ ሲኾን ትርጒሙም እምነት ማለት ነው። ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፣ አይቀነስለትም፣ አይሻሻልም፣ አይለወጥም። ከጊዜው ጋር ስላልሄደ፣ ስላልተስማማ፣ አስቸጋሪ ስለኾነ ወዘተ በሚል ማንኛውም ምክንያት መሻሻል መለወጥ መጨመር መቀነስ የለበትም።
ለምሳሌ ያህል በተዋሕዶ ሃይማኖት ውስጥ የእግዚአብሔርን ህልውና እናምናለን። ሥላሴ አንድ ሲኾን ሦስት፣ ሦስት ሲኾን አንድ ብለን እናምናለን። አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ተወለደ ብለን እናምናለን። ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል ብለን ስለምናምን የልጅነት ጥምቀትን እንጠመቃለን። ጥምቀታችንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደኾነ እናምናለን። ሥጋዬን ያልበላ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም የሚለውንም አምላካዊ ቃል አምነን ኅብሥቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት ነው ብለን በማመን እንቆርባለን ወይም ሥጋና ደሙን እንቀበላለን። በመጨረሻም የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን። ሙታን ኹሉ እንደየሥራቸው ትንሣኤ ዘለክብር ወይም ትንሣኤ ዘለሐሳር ይነሣሉ ብለን እናምናለን። እንዲሁም የእመብርሃን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና እና አማላጅነት እንዲሁም የመላእክትን ተራዳኢነት የቅዱሳኑን ምልጃና ጸሎት ኹሉ እናምናለን። ከዚህ እምነታችን ማንም ሊያናውጠን አይችልም። ቅብዐቶቹ ግን በዚህ ኹሉ ከእኛ የተለዩ ናቸው። ይህን ልዩነታቸውን ግን ጥቂቶች ካልኾኑ በቀር ብዙዎች አያውቁትም።
ወደፊት በሰፊው ከቅብዐቶች መጽሐፍ እየጠቀስን የምናብራራው የዶግማ ልዩነታችን የሚከተሉት ናቸው። እነዚህን የዶግማ ልዩነታችንን ግን አብዛኛው የቅብዐትም ኾነ የተዋሕዶ ልጆች በሰፊው አያውቁትም። ብዙ ቅብዐቶች ይህን የምትለውን ኹሉ አንቀበለውም እንደምትሉኝ አውቃለሁ ምክንያቱም መምህሮቻችሁ እውነቱን ደብቀው ስለሚነግሯችሁ ነው። እኔ ግን እውነቱን ከመጽሐፋችሁ ጠቅሼ አሳያችኋለሁ።
-
ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ነው ይላሉ።
-
በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ይላሉ።
-
ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ይላሉ።
-
ለመስቀል አይሰገድም ይላሉ።
-
ሥጋ ወደሙ
የተጣመመ ትምህርት አላቸው።
-
ወንጌል
በአሚን ብቻ ታድናለች ይላሉ።
ይህ ኹሉ የቀኖና እና የዶግማ ልዩነት እያለን እነርሱ ግን ልዩነታችን የቀኖና ብቻ አስመስለው የዋሐንን ያታልላሉ። ልዩነታችን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ገናን ታህሳስ ፳፰ ቀን ማክበራችን ብቻ የሚመስላቸው በጣም ብዙዎች ናቸው። ግን አይደለም መሠረታዊው ልዩነት ዶግማችን ላይ ያለ ልዩነት ነው።
በነገራችን ላይ ይህን የዶግማ ልዩነታችንን ደብቀው የቀኖና ልዩነት ብቻ አስመስለው በማቅረብ ብዙዎችን እያደናገሩ ናቸው። እነዚህን ከላይ ያየናቸውን የዶግማ ልዩነቶች ቅብዐት ነኝ ለሚል ምእመን እውነቱን ገልጠው አይነግሩትም። እውነቱን ከተናገሩማ ማን ይከተላቸዋል ታዲያ። እናንተ ይህን የምታነብቡ ሰዎች ለሌሎችም መልእክቱን በማድረስ ሳያውቁ የጠፉ ነፍሳትን እንድትመልሱ አደራ አለባችሁ።
የቀኖና እና የዶግማ ልዩነታችንን ደብቀው ከተዋሕዶ በምንም አይለዩም እያለ የዋሐን እንዲከተላቸው የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም መካከል።-
የግዕዝ ቋንቋን በመጠቀም ማታለል። በመጻሕፍት ተጽፎ የማይገኝን ነገር ኹሉ ያለቦታው በግዕዝ በመጥቀስ ማታለላቸው።
የቤተክርስቲያናችንን ሥዕላት እና ሌሎች ንዋየ ቅድሳትን መጠቀማቸው።
በቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ስም መጠቀማቸው (መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን…) እነዚህን ሊቃውንት የሚጠቅሷቸው የዋሐኑን ምእመን ለማታለል እንጅ እነዚህ ሊቃውንት በሚያምኑት እምነት የሚያምኑ ኾነው አይደለም። «ወልደ አብ» እና «መሰረተ ሐይማኖት» በተሰኙ መጽሐፎቻቸው ላይ እነዚህን ሊቃውንት እየደጋገሙ ያነሧቸዋል። ኾኖም ግን ትምህርታቸውን አይቀበሉትም። ይህንንም ወደፊት በሰፊው የምናየው ኾኖ አሁን ግን ከቅብዐቶች መጽሐፍ የተገኘውን ማስረጃ በፎቶ ከሥር እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።
ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ያልተጻፈን ነገር እየቆረጡ እና እየቀጠሉ እንዲህ ይላል እያሉ ማሳሳት።
መጻሕፍትን ያለትርጓሜያቸው በመተርጎም ምእመናንን ግራ ማጋባት።
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመናቅና በመንቀፍ ቆርጠውታል እንዲህ አድርገውታል ወዘተ እያሉ በሊቃውንቱ ዘንድ አመኔታ እንዳይኖረን ለማድረግ መጣራቸው።
እኛ የምንጠቅሰው ብራና ስለኾነ እምነታችንም ማስረጃችንም ጥንታዊ ነው በማለት ማታለላቸው። ወዘተ በዋናነት የሚጠቀሱ ነጥቦች ናቸው።
ከቀጣዩ ክፍል ጀምረን የቀኖና እና የዶግማ ልዩነቶቻችንን መጽሐፎቻቸውን እየጠቀስን ሊቃውንቱን ምስክር እያደረግን በማስረጃ ላይ ተመሥርተን በዝርዝር እንመለከታለን።
#ጾመ_ሐዋርያት_ሰኞ_ግንቦት_ሃያ_ይጀምራል_የቅብዐቶች__ከሳምንት_በኋላ_ይገባል_አንድ_ልዩነት_ይህ_ነው።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፰/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment