Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፰



የቀኖና ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፩፡- የአጽዋማት መግቢያና መውጫ ቀናትን የተመለከተ
ጾመ ሐዋርያትን የተመለከተ ልዩነት
እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም አደረሳችሁ።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ቅብዐቶች ስለ ጾመ ሐዋርያት «መሰረተ ሐይማኖት» በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፵፱ ላይ እንዲህ ይላሉ «የሐዋርያት ጾም ዋዜማ። ይህጾም ጰራቅሊጦስ ከገባ ጀምሮ ይጾማል አይጾምም ስለሚለው ከወዲሁ አራት ቀንና ወይም አምስት ቀን ጭማሪ ተደርጎ ይጾማል። ምክንያቱም #ቢጾም_ዋጋ_አለው_ባይጾም_ኩነኔ_የለውም» ይልና «በመሰረቱ ግን በትክክለኛ መንገድ ከሔድን ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 እንዲህ ይላል በዓለ ሃምሳን አክብራችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ሌላ ሰባት ቀን በዓል አድርጉ።ምክንያቱም ለእኛ በተሰጠችን በእግዚአብሔር ስጦታ ደስ ሊለን ይገባልና። ለሐዋርያት #ጰራቅሊጦስ_መንፈ_ጽእቅ_ጌታ_አምላክ_ኢየሱስ_ክርስቶስ እፍ ባለባቸው ጊዜ ሀዲስ ቋንቋዎችን ተናግረዋልና። ይኸም የደስታ ቀን ስለኾነ ከበአለ ሃምሳ ቀን ጀምራችሁ ሰበባት ቀን አክብሩ አሉ። ጾም ቢኾን ኖሮ የመከራ ቀን ነውና ጹሙ ባሉ ነበር» ይላል።
እኛ ግን እንዲህ አንልም። ጾም ባይጾም አይጎዳም ቢጾምም ኵነኔ የለውም አንልም በፍጹም። ጾም በመጾሙ ይጠቅማል ባለመጾሙም ይጎዳል። ለዚህም ቀላሉ ማስረጃችን የነነዌ ሰዎችን ታሪክ በጾም ለመጠቀማቸው ሰዶምና ገሞራን ባለመጾማቸው ለመጎዳታቸው መጥቀስ ይቻላል። በነገራችን ላይ መጽሐፍ ይዘው ስለኾነ የቀኖና ጥሰት የጀመሩት እኛም ያንኑ የጠቀሱትን መጽሐፍ ማስረጃ አድርገን መርታት ይኖርብናልና ወደ ዋና ጉዳያችን እንግባ።
ቅብዐቶች ለማሳሳት እንደጠቀሱት እኛም ለማስረዳት እንደምንጠቅሰው በፍትሐ ነገሥት ፲፱÷፯፻፴፰ ላይ እንዲህ የሚል ንባብ ይገኛል፡-
«በዓለ ሃምሳን አክብራችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ሌላ ሰባት ቀን በዓል አድርጉ ለእኛ በተሰጠችን በእግዚአብሔር ስጦታ ደስ ሊለን ይገባልና» ይላል።
ወደ ቁም ነገሩ ከመጡ አንቀጽ ፲፱ የሚያወራው ስለበዓላት እንጂ ስለአጽዋማት አይደለም። ስለ አጽዋማት በሚገባ ይህንንም ቃል ጨምሮ በግልጽ አብራርቶ የምንመለከተው አንቀጽ ፲፭ ላይ ነው። ስለጾም ለማውራት አንቀጽ ፲፭ን ዘሎ አንቀጽ ፲፱ን መጥቀስ ደግሞ አይቻልም። ምክንያቱም አንቀጸ ጾም የሚባለው አንቀጽ ፲፭ ነውና። በዓል አድርጉ ማለት ብሉ ጠጡ ማለት አይደለም። በመጾም በዓላትን ማድረግ ይቻላልና ይህንንም አንቀጽ ፲፭ ላይ በማብራራት ጽፎት እናገኘዋለን። ይህንንም ከታች  ጽፈነዋልና እዚያ ላይ ታገኙታላችሁ። በዚህም አለ በዚያ ግን እኛ የተዋሕዶ አማኞች እንጹም ስንል ቅብዐቶች ደግሞ እንብላ ሲሉ ነው እየተመለከትን ያለነው። የድኅነት ጐዳና ደግሞ ጾም እንጂ መብል አይደለምና በዚህ እናሸንፋቸዋለን።
በነገራችን ላይ ስለምስጢረ ሥጋዌ እና ምስጢረ ሥላሴም የክሕደት ቅርሻት ሲያቀረሽ አስተውለናል። የጸሐፊ አልያም ሳይታሰብ በስሕተት የተደረገ ከኾነ እንዲያስተካክል እንነገረዋለን። አውቆት ተጠንቅቆ የጻፈው ከኾነ ግን መነጋገራችን ሳይበጅ አይቀርም። ደራሲው ስለሐዋርያት ጾም ሲገልጽ፡-
«ለሐዋርያት ጰራቅሊጦስ መንፈ ጽእቅ ጌታ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እፍ ባለባቸው ጊዜ ሀዲስ ቋንቋዎችን ተናግረዋልና» በማለት የተናገራት ንግግር ብዙ ኑፋቄ አለባት።
ከጥንቃቄ ጉድለት የተፈጠረ ስሕተት እንደሚኾን እገምታለሁ ካልኾነ ግን ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ የሚባለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይኾን መንፈስ ቅዱስ እንደኾነ እንናገራለን። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሰ ጽድቅ ጰራቅሊጦስ ነው ብሎ መናገር አካላትን ኹለት ማድረግ ነውና ምስጢረ ሥላሴን ያናጋል። በዚያውስ ላይ ወልድ ለሐዋርያት የእውነት መንፈስን እልክላችኋለሁ በማለት ተናገረ እንጂ እኔ ተመልሸ ላጽናናችሁ እመጣለሁ ብሏቸዋልን? አላለም። ምናልባት ከጥንቃቄ ጉድለት የመጣ ሊኾን ስለሚችል እንደ ደራሲው ኹሉ እኔም ነገር መደረቴን ልተወውና ወደ መሠረታዊው ጉዳይ እንግባ።
ጾመ ሐዋርያት
=========
ጾመ ሐዋርያት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጾም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለትምህርት ወደ ዓለም ከመሄዳቸው አስቀድመው ለሥራቸው ኹሉ መዠመሪያ አድርገው የጾሙት ነው። ይህንን ሲገልጽ ፍትሐ ነገሥት ፲፭÷፭፻፹፮ ላይ፡-
«ዳግመኛም ስለ ሃምሳኛው ቀን አከባበር ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን ሕገ ኦሪት ለሕዝቡ ከማስተማር በፊት እንደጾመ ጌታችንም በርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ የርሱን ሕግ ለሕዝብ ከማስተማሩ አስቀድሞ እንደዚሁ ጾመ። ሐዋርያትም በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሕገ ወንጌልን ለሕዝብ ከማስተማራቸው አስቀድሞ እንደዚሁ ጾሙ። እኛም በዚህ በእነርሱ ተመራን» ይላል።
ስለዚህ ጾም መግቢያና መውጫም ፍትሐ ነገሥት ፲፭÷፭፻፷፱ ላይ፡-
«ከዚህም ቀጥሎ ከበዓለ ሃምሳ ቀጥሎ ያለ የሐዋርያት ጾም ነው። ፋሲካው በጴጥሮስና በጳውሎስ በዓል ሐምሌ ቀን ነው» ብሏል።
አባቶቻችን እንደሠሩልን ሥርዓት መሠረት የዚህ ጾም መዠመሪያ በዓለ ሃምሳ እንደተፈጸመ የመዠመሪያው ሰኞ ነው። ይህም ማለት አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ከጰራቅሊጦስ በዓል ቀጥሎ ባለው የመዠመሪያው ሰኞ ይጀመራል ማለት ነው።
ነገር ግን ቅብዐቶች ለመብላት ካላቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ የፍትሐ ነገሥቱን ትእዛዝ በሙሉ ሳያነቡ ለራሳቸው እንደሚገባ አድርገው ተርጒመው ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሌላ ቀናትን ይበላሉ። ይህንንስ ከየት አግኝተውት ነው ቢሉ ፍትሐ ነገሥት ፲፭÷፭፻፹ እና ፲፱÷፯፻፴፰  ላይ፡-
«በዓለ ሃምሳን ከጨረሳችሁ በኋላ ዳግመኛ ሰባት ቀን ሌላ በዓል አድርጉ ከዚህም ቀጥሎ ከአረፋችሁ በኋላ ጹሙ» የሚለውን ይዘው ነው።
ነገር ግን በዓልን በማድረግ የሚጾሙ አጽዋማት አሉና በዓል አድርጉ አለ እንጂ ብሉበት አላለም። ይህንም ሲያስረዳ ቊጥር ፭፻፹፩ ላይ፡-
«እግዚአብሔር ይቅር ይበለውና ይህን መጽሐፍ ከሰበሰበው የተመረጠ ከኾነው መምህር ቃል የተገኘ ነው። የዚህ ሳምንት ምልክት ግን ልንበላበት እንደማይገባ እነሆ ረቡዕንና ዓርብን እንድንጾም ያዘዘበት አንቀጽ አለ ዳግመኛም በዓለ ሃምሳ ልደት ጥምቀት ቢውልባቸው አትጹሙ ብሎ ያዘዘበት አንቀጽ አለ። ስለዚህ ሳምንት ግን አልተናገረም። ሊበሉባቸው በሚገባ ቀኖች ውስጥ ሊጾሙባቸው የማይገባ ቢኾን ኖሮ እንደነዚያ መልሶ በተናገረ ነበር» ይላል።
ረቡዕ እና አርብን ከዓመት እስከ ዓመት ጹሙ ነገር ግን ጥምቀት፣ በዓለ ልደት እና በዓለ ሃምሳ ካልዋሉባቸው በቀር ብሎ ተናግሮ ነበርና ቊጥር ፭፻፷፮ ላይ፡-
«ዳግመኛም በየሳምንቱ ኹሉ ዓርብና ረቡዕን መጾም ነው። በዓለ ሃምሳ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልኾነ በቀር እንደተጻፈው እስከ ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው»
ረቡዕ እና ዓርብ መቼ እንደሚበላባቸው ጠንቅቆ ጽፏል። ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለው ሳምንትም የማይጾም ቢኾን ኖሮ ከዚህ ጋር አብሮ ይጽፈው ነበር። ነገር ግን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በዓል አድርጉ አለ እንጂ ብሉበት አላለም። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለው ሳምንት የማይጾም ቢኾን ኖሮ ግን በዚህ ቊጥር ላይ «በዓለ ሃምሳ እና ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት» ባለ ነበር።
በመጾም በዓል ማድረግ እንደሚገባ እዚሁ አንቀጽ ላይ  ቊጥር ፭፻፹፪ ላይ፡-
«ዳግመኛም እንዳንጾምባቸው እንዳንሰግድባቸው የታዘዝንባቸው ቀኖች እንደ እሁድ እንደ ሰንበት እንደ ጌታ በዓላት ያሉ ቀኖች አሉና ከእነርሱ ጋር ይህን ሳምንት አልተናገረም። ዳግመኛም የሰሙነ ሕማማትን ሥራ ሳይሠራ ላለፈበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ስለርሷ መጾም መስገድ ይገባ ዘንድ ታዘዘ። ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የሚውለው ሳምንት ይህ ቢኾን ኖሮ ከሃምሳ ቀኖች በኋላ ይበሉበት ዘንድ የሚገባ ቢኾን እንደገና ብሉበት በተባለ ነበር። በዓል አድርጉ ከማለቱ በቀር ብሉበት አላለምና» ይላል።
እዚህ ቊጥር ላይ የምንመለከተው ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለው ሳምንት እንድንጾምበት እንጂ እንድንበላበት አይደለም። እንደዚሁም ቊጥር ፭፻፹፫ ላይ፡-
«ይህስ በውስጡ ያሉትን የዓርብንና የረቡዕን ጾም ያስረዳል። እነርሱንም ይፈጽሟቸው ዘንድ አያስረዳም እነሆ ባስልዮስና አፈወርቅ እንዲህ አሉ። በዓል ማክበር በመብል አይደለምና ዳግመኛም በጾም በዓል ማክበር እንዲገባ የታወቀ ነው። ይኸውም ለበዓሉ የሚስማማው እንዲነበብ ነው እንጂ ሊበሉበት አይደለም። ኤጲስ ቆጶስ በተሾመ ጊዜ ቀን እንድናከብር እነሆ ቀኖና አዘዘችን። በጾም ቀን እንኳ ቢኾን በእነዚህ በ፫ ቀኖች እንዳንበላ የታወቀ ነው በዓል ማክበር በመብል አይደለም»
በማለት በማያሻማ እና በማያወላዳ መልኩ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን ሳምንት እንድንጾም ያስረዳል። ነገር ግን ለመብል ራሳቸውን የሰጡ ወገኖች ይህንን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ያለውን ቀን ይበሉበት ዘንድ በዓል አድርጉ ተብለናል ይላሉ።
ከላይ እንደተመለከትነው በዓል የሚደረገው በመብል በመጠጥ ብቻ አይደለም በጾምም ጭምር ነው እንጂ። የሚበላበት ቢኾን ኖሮ  ቊጥር ፭፻፹፰ ላይ፡-
«አንድ ሰው በባሕር ቢኖር ሰሙነ ሕማማትን ባያውቅ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ይጹም። ይኸውም ሰሙነ ሕማማትን የሚጠብቅ አይደለም። ምሳሌውን ብቻ ነው እንጂ ስለእርሱ መጾም ይገባዋል»
ብለው ባላዘዙም ነበር። ነገር ግን መጾም እንዲገባ ጹሙ ብለው አዘዙ እንጂ። አባቶቻችን ይህን ያዘዙን እነርሱ ሳይጾሙ አይደለም ጾመው ነው እንጂ ለዚህም  ቊጥር ፭፻፹፭ ላይ፡-
«ዳግመኛም ከተሰበሰቡት ወገን ቊጥራቸው ኸያ የሚኾኑት ጹመውታልና ከእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት ወገን ከዚህ ቊጥር ቊጥራቸው እስከበዙት ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ በዚህ ሳምንት እነሆ ይህን ጾም ጾምን። የማኅበሩን ትእዛዝ ብንተላለፍ ይህን ማኅበር እንዲነቀፍ ብናደርግ ደግ አይደለም። ይልቁንም የሕጋችንን ትሩፋት በተቃወመ ጊዜ። ይኸውም ስለመብል ስስትን በመግለጽ የሚደረግ ክፋት ነው» ብለዋል።
ስለዚህ ከአባቶቻችን አንበልጥምና በእነርሱ መንገድ እንጓዝ ዘንድ ይገባል። ይህን ኹሉ ብለው አልሰማ ላላቸው ግን ኹሉን ሊጠቀልል የሚችል ትእዛዝ እነሆ ሰጡን። ቊጥር ፭፻፹፬ ላይ፡-
«ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢኾን መጾም ይገባል። ከመብላት በጣም ይሻላል» ብለው አዘዙን።
በጾም ምክንያት ክርክር ከተፈጠረ መጾም ይገባል ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ አረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ እወቁ። ስለዚህ የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት ነው እንጂ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሌላ አንድ ሳምንት ከበላን በኋላ ባለችው ሰኞ ነው ማለት አይደለም።
ቅብዐቶች ለዚህ ማስረጃ ካላቸው ሊያቀርቡልን ይችላሉ። አንዱ የቀኖና ልዩነታችን ይህ ነው።
እኛ የተዋሕዶ ልጆች ነገ ሰኞ ጀምረን ጾመ ሐዋርያትን እንጀምራለን ቅብዐቶች ግን አንድ ሳምንት ከበሉ በኋላ ይጀምራሉና አንድ የቀኖና ልዩነት ይኼ ነው። እኛ ነን ወይስ ቅብዐቶች ናቸው ጥፋተኞች? ለዚህ ዳኛችን ፍትሐ ነገሥት ነው በእርሱ የሚዳኝ እውነተኛ ኅሊና መልሱን ያውቀዋል።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፱/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment