Tuesday, October 9, 2018

«ፍኖተ ሕይወት» በአባ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘሀገረ ካናዳ ---ክፍል ፬



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
በመጀመሪያ ክፍል ጽሑፌ ላይ አባ ማትያስ የውጩ ሲኖዶስ አባል ይመስሉኛል ብየ ነበር። ይመስሉኛል ለማለት የተነሣሁት ፓትርያርካችን አቡነ ማትያስ ስለሚባሉ ስማቸው ተመሳሳይ ለምን ኾነ ብየ ስላሰብሁ ነበር እንጅ ትልቁ ምስጢር ጠፍቶኝ አልነበረም። የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ አባል ናቸው ከተባለ ግን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሦስተኛው ፓትርያርክ በአቡነ ተክለሃይማኖት ተወግዘው ስለተለዩ ጳጳስ እንዳልኾኑ ስለተቆጠረ የተሰጣቸው ስም ነው የሚለው ያመዝናል ብየ ገልጨ ነበር። አሁን ብዙዎቻችሁ በውስጥ እየገባችሁ አቡነ ማትያስ የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ አባል ናቸው ትሉኛላችሁ አዎ እርሱ እኮ ልክ ነው። የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ አባል እንደኾኑ የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፌን ወዲያውኑ እንደለጠፍሁት ብዙዎች ነግረውኝ እውነት ነው ብዬ ተቀብየዋለሁ።
አቡነ ማትያስ ተብለው በፓትርያርኩ ስም የተሰየሙትም ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተወግዘው ስለተለዩ እንደኾነ በሚገባ ታሪኩን ተረድቻለሁ። የእርሳቸው በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ አባል መኾን አለመኾን ሊያከራክረን አይገባምና ወደ ዋናው ጉዳይ ብናተኩር መልካም ነው።
ከዚህ በፊት «ወልድ ፍጡር» በሚለው የፍኖተ ሕይወት እና የወልደ አብ አገላለጥ ላይ አንድ ክፍል ጽፌያለሁ። አሁንም ቢኾን «ወልድ ፍጡር» አልልም ምንም ማስረጃ ብታቀርቡልኝ በዚህ መቼም ቢኾን የምስማማ አይደለሁም። «መጻሕፍት እንዲህ ሲሉ ነው» እያልን እያቀናን ልንተረጉመው እንችል ይኾናል እንጅ በቁሙ «ወልድ ፍጡር» የሚል አስተምህሮ አላውቅም።
«ፍጹም አካሉን ፈጠረ»፣ «ሥጋን ፈጥሮ ተዋሐደ»፣ ሥጋን ፍጥሮ ሲዋሐድ ማንም አላገዘውም ራሱ ፈጠረው እንጅ» ወዘተ እያሉ በሃይማኖተ አበው ውስጥ የተገለጡ ጥሬ ቃላት አሉ። እነዚህ ጥሬ ቃላት አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐድ፣ የዕለት ጽንስ ሲኾን፣ ደመ ድንግልናዋን ሲከፍል በጊዜ ተዋሕዶ የተደረገውን ሕዋሳት መቅረጽ ያደረገውን ሥራ «ፈጠረ» በሚል መጻሕፍት ጽፈውት እናገኛለን። «ፈጠረ» ሲል አንድም «ፍጡር ሥጋን ተዋሐደ» በማለት ምትሐት አለመኾኑን ሲያስረዳ ነው። አንድም «ሕዋሳትን ቀረጸ ማለትም ዓይን ጆሮ እግር እጅ አፍንጫ ወዘተን ቀረጸ» ሲል ነው እንጅ ዛሬም በየማኅጸኑ አዲስ ፍጥረት ይፈጥራል ሲል አይደለም። «ፈጠረ» ሲል አንድም ሰው ኾነ ሲል ነው።
እስካሁን ያየነው «ፈጠረ» የሚለው ቃል በጊዜ ተዋሕዶ ብቻ የምንናገረው ቃል እንጅ ከተዋሕዶ በኋላም በቃል እና በሥጋ ርስት እያልን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋው ፍጡር በመለኮቱ ፈጣሪ እያልን የምንናገረው አይደለም። ታዲያ በሥጋው ፍጡር በመለኮቱ ፈጣሪ ካልነው ተዋሕዶው የት አለ? የእኔ ጥያቄም ይኸው ነው። መጻሕፍትን ጠቅሳችሁ ለምትከራከሩኝ ኹሉ «ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋው ፍጡር ነው በመለኮቱ ፈጣሪ ነው» ልንለው እንችላለን ወይ? የሚለውን መልሱልን።
በማኅፀን የሠራውን ሥራ ከማኅፀን ውጭም እንዳደረገው አድርገን ተዋሕዶውን ከዘነጋነው ችግር ነው። ደመ ድንግልናዋን ሲከፍል፣ ቃል ሥጋን ሲዋሐድ፣ ሥጋ አምላክ ሲኾን (ሲከብር)፣ ሲጸነስ፣ ሕዋሳትን ሲቀርጽ (በመጻሕፍት አገላለጥ ሲፈጥር) አንድ ጊዜ ነው መቀዳደም የለም። ከዚህ በኋላ ግን «ፈጠረ» «ተፈጠረ» የሚለውን አገላለጥ ልንጠቀመው አንችልም። ክርስቶስን «ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው» እንለዋለን እንጅ «ፍጹም ፍጡር» የሚባል አገላለጥ አይቼ ሰምቼ ተምሬ አላውቅም። «ፍጹም ፍጡር» የሚል አገላለጥ አለ ካላችሁ አሳዩኝ። ለምሳሌ በዘመነ ሥጋዌው ማለደ፣ ጸለየ፣ ለመነ ወዘተ እያልን የተጠቀምንባቸውን ቃላት በመስቀል ላይ ቤዛ ኾኖ ደሙን አፍስሶ ነጻነትን ከሰጠን በኋላ ልንጠቀምባቸው አንችልም። ዛሬ ድረስ «ይማልዳል» «ይለምናል» «ገንበስ ቀና እያለ ይሰግዳል» ወዘተ እያሉ የተሳሳቱት እኮ ይህን ከመስቀል በፊት የተገለጠውን አነጋገር ዛሬ ድረስ እየተጠቀሙበት ስለኾነ ነው። ታዲያ «ፈጠረ» ላይ ያለውንስ እንደዚህ ያያችሁት አይመስላችሁምን?
ወደ ዛሬው ጉዳይ እንግባና ጥቂት እንበል። «ፍኖተ ሕይወት» ላይ የጌታ ጽንሰት የሚለው ርእስ እና «ወልደ አብ» ላይ ነገረ ማርያም የሚለው ርእስ በብዙ ነገራቸው ይመሳሰላሉ። ነገር ግን «ወልደ አብ» በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ብሎ ይደመድማል «ፍኖተ ሕይወት» ግን በተዋሕዶ ከበረ ብሎ ያስራል። በዚህ ርእስ ላይ ከወልደ አብ ይልቅ «ፍኖተ ሕይወት» በጥሩ መልኩ በተዋሕዶ ከበረ ማለትን አስረድተዋል።
«ፍኖተ ሕይወት» ገጽ ፪፻፴፭ መጨረሻ አካባቢ «ጌታም ለአብሥሮተ ድንግል ገብርኤልን መስሎ ሲወጣ ሲወርድ ስለታየ «ወረደ እምሰማያት» አለ እንጅ ሰማይን ለቆ ወረደ ሲል አይደለም። ያበሠራት ጌታ ነውን? ቅዱስ ገብርኤል አይደለምን? ቢሉ ገብርኤልን መስሎ ሲወጣ ሲወርድ ስለታየ ገብርኤል ነው እንላለን እንጅ እርሱ ቃለ እግዚአብሔር አብሥሮ አደረባት» ይላል። ይኸው አገላለጥ «ወልደ አብ» ገጽ ፻፲፯ ላይ ተጽፎ ይገኛል። ከታች ኹለቱንም በፎቶ ስላያያዝኩላችሁ ተመልከቱት።
የእኔ ጥያቄ ያበሠራት ገብርኤል ነው ወይስ አካላዊ ቃል ነው? የሚለው ነው። «ይኩነኒ» ስትለው ወዲያኑ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ወዲያውኑ ተጸነሰ እንላለን። ይህ ወዲያኑ መደረጉ የፍጡር ብሥራት ቢኾን ኖሮ በዘገየ ነበር የሚሉ ስላሉ ያበሠራት አካላዊ ቃል ራሱ ነው ሊባል የሚችልበት ነገር ያለ አይመስለኝም። ምናልባት መጽሐፍ ላይ ያገኛችሁት ነገር ካለ አሁንም ልታስረዱኝ ትችላላችሁ። እኔ የማውቀው ያበሠራት ቅዱስ ገብርኤል እንደኾነ እንጅ አካላዊ ቃል ገብርኤልን መስሎ ራሱ አብሥሮ አደረባት የሚል ትምህርት አላውቅም። የምታውቁ ካላችሁ ደግሞ መጽሐፍ ጠቅሳችሁ አስረዱኝ። ይኩነኒ ስትለው ወዲያውኑ ማደሩን ሲገልጡ ፍጥነቱን ሲገልጡ እንዲህ ይሉ እንደኾነ እንጅ ያበሠራት ራሱ አካላዊ ቃል ነው የሚለውን ግን አላውቅም።
አባ ማትያስ በተዋሕዶ ከበረ ማለት እና በተዋሕዶ ተቀባ ማለት አንድ ናቸው በማለት ገጽ ፪፻፵-፪፻፵፩ ላይ የገለጡት እና ያብራሩት ነገር በጣም ጥሩ አገላለጥ ነው። «ቀብዐ» ማለት «አከበረ» ማለት ስለኾነ ትርጉሙም ይስማማል። ወልድ ራሱ ቀባዒ ራሱ ተቀባዒ ራሱ ቅብዕ ለመኾኑም የገለጡበት አገላለጥ የሰጡት ማስረጃ በጣም ደስ የሚል ነው። መጽሐፉ በዚህ የጌታ ጽንሰት በሚለው ጽሑፉ ላይ በእኔ አመለካከት እና አረዳድ በውሱን እውቴ በጥቂት ትምህርቴ ከብሥራተ ገብርኤል ውጭ ይህ ነው የሚባል ስህተት አላየሁበትም። እንዲያም የሚያምር እና ጥሩ የኾነ አገላለጥን የያዘ ነው። ወልደ አብ ላይ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ እያለ ሲያላዝን ፍኖተ ሕይወት ግን አብ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ ቢልም አንድ ነው ይላል። ወልድን ቀባዒ ተቀባዒ እና ቅብዕ ነው ብሎም ወልደ አብ ላይ ያለውን ወልድ ቅብዕ በተዋሕዶ ከበረ ማለት ኑፋቄ ነው የሚለውን ይሞግታል። የተጠቀሱት ማስረጃዎች የቀረቡት ትንታኔዎችም በጣም ደስ የሚል ነው። በመንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት ኑፋቄ እንደኾነ እና የተወገዘ ትምህርት መኾኑንም የያዘ መጽሐፍ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የምናገኘው ተዋህዶ የሚል ርእስ ነው እርሱንም እንዲሁ ወደ ፊት እንመለከተዋለን።  
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፳፱/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment