የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፮፡- ቅብዐቶች ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ይላሉ እኛ ግን አሚን ያለምግባር ብቻውን አያድንም እንላለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አሁን አሁንስ ቅብዐቶች አልመስልህ እያሉኝ ነው። ምናልባት ፕሮቴስታንቶች ይኾኑ እንዴ በቅብዐት ስም ወደ ቤተክርስቲያን የገቡት። በርግጥ ሄኖክ የተባለው የቅባቶች ሊቅ ጥላሁን መኮንን በተባለ የተሐድሶ መናፍቅ «ከተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውጡ ጳጳስ እኔ ከእስክንድርያ አመጣላችኋለሁ እንዲያውም እርስዎን የቅብዐቶች የመጀመሪያ ጳጳስ እንድትኾን አደርጋለሁ» ብሎ ለሦስት ወራት ያህል የተሐድሶ ሥልጠና ሰጥቶ ስለላከው እንዲህ ያለውን ነገር ቢጽፍ የሚፈረድበት አይመስለኝም። ወልድን ፍጡር አሉ፣ ለቅዱሳን እና ለመስቀል ስግደት አይገባም አሉ፣ ዛሬ ደግሞ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች አሉን ነገ ደግሞ ሥጋ ወደሙ ላይ የተወላገደ ትምህርቱን እናያለን። በዚህ ኹሉ የፕሮቴስታንቶች እጅ እንዳለበት እንረዳለን። ያም ኾነ ይህ ግን ቅብዐቶች እንደሚሉት «ወልደ አብ» የተባለው መጽሐፍ ከጥንት ጀምሮ በብራና ተጽፎ የነበረ ነው። ያ ማለት ደግሞ ቅብዐቶች እውነት ነው ያሉትን የሚያምኑበትን እምነታቸውን ጽፈውታል ማለት ነው።
ስለዚህ ቅብቶች በአጽዋማትና በበዓላት ላይ ያላቸውን የተዛባ ትምህርት ወደ ጎን አድርገን ዶግማው ላይ ብቻ ብንነጋገር ብዙ ልዩነቶች እንዳሉን እንመለከታለን። ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ከማለት የበለጠ ምን ልዩነት ሊመጣ ነው? ለቅዱሳን እና ለመስቀል ስግደት አይገባም ከሚል ልዩነት በላይ ምን ልዩነት ሊመጣልን ነው? ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ከማለት በላይ ምን የባሰ ልዩነት ሊመጣ ነው? ይህን የዶግማ ልዩነት እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት እንኳ ስለጾ ነቢያት እና ስለጾመ ሐዋርያት ብሎም ስለልደት በዓል አከባበር ሽንጣቸውን ገትረው ሊከራከሩ የሚንፈራፈሩ ቅብዐቶች መኖራቸው ያሳዝነኛል። ወልድን ፍጡር እያሉ ልደቱ መቼስ ቢከበር ምናቸው ነው? ጾም ቢጾምም አይጠቅምም ባይጾምም ኩነኔ የለውም እያሉ ጾም መቼስ ቢገባ መቼስ ቢወጣ ምናቸው ነው? ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች እያሉ ክርስቲያናዊ ምግባራት ላይ መከራከር እንዴት ይችላሉ? ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ለመስቀሉም ስግደት አይገባም እያሉ ስለቅዱሳን እና ስለመስቀሉ ምን አከራከራቸው?
ቅብዐቶች ወልደ አብ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፺፫ ላይ፡-
«ዳግመኛም ኦሪት ጀምሮ የፈጸማትን ታድን ነበረ እንጅ እንደ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም ነበረ» ይላሉ።
በእውነት ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለችን? አዎ ካላችሁ ለምን ትጾማላችሁ? ለምን በዓላትን ታከብራላችሁ? ለምን ትመጸውታላችሁ? ለምን ትሰግዳላችሁ? ለምን ምግባር መሥራት አስፈለጋችሁ? አረ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም ካላችሁ ግን ለምን ቅብዐት ትኾናላችሁ? ለምን «ወልደ አብ» የተባለውን ምናምንቴ መጽሐፍ ትቀበላላችሁ? ለምን በተዋሕዶ እምነት አታምኑም? ለምን ወደ ተዋሕዶ እናታችሁ አትመለሱም?
ይህ ትምህርት ፍጹም ፕሮቴስታንታዊ ነው። «ኢየሱስን ካመንህ በቃ ድነኃል የምን ንስሐ ነው? የምን ጾም ነው? የምን ስግደት ነው? የምን ምጽዋት ነው? የምን ምንኲስና ነው? የምን ብሕትውና ነው? የምን ስለኃጢት ማዘን ነው?» የሚለው የፕሮቴስታንቱ ትምህርት ነው ቅብዐቶች ላይም እያየነው ያለነው። እኔ የማዝነው እናቴ የአባቴ ነው እያለ እስካሁን ድረስ ቅብዐት ነኝ እያለ ቁጭ ያለው ሰው ነው። ይህንን ልዩነት ቢያውቀው ኖሮ ማን በቅብዐት ይጨማለቅ ነበር? አረ ማንም።
ለማንኛውም እምነት ብቻውን አያድንም። የቆማችሁ የመሰላችሁ ቅብዐቶች «እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ» ፩ኛ ቆሮ፲÷፲፪ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ውድቀታችሁን አታፋጥኑ በጊዜ ራሳችሁን ፈልጉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል «…ሥራኽን አውቃለሁ ሕያው እንደመኾንህ ስም አለኽ ሞተኸማል» ራእ ፫÷፩። ስም ያለን መስሏችሁ የሞታችሁ የከፋ ሥራችሁ የከረፋ እምነታችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀው እናንተ ቅብዐቶች ሆይ ወደ ልቡናችሁ ተመለሱ።
ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ካላችሁ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ ምን እንደጻፈ ልንገራችሁ እስኪ።
ያዕ ፪÷፲፬ ላይ «ወንድሞቼ ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?» ብሎ ይጠይቀናል። እኛ ለሐዋርያው የምንመልስለት መልስ ሊያድነው አይችልም ብለን ነው ቅብዐቶች ግን አዎ ያድነዋል ብለው ነው ማለት ነው። ስለዚህ ወንጌል በአሚን ብቻ አታድንም። አሚን ያለሥራ የሞተ ነው እንላለን አብነታችንም ሐዋርያው ያዕቆብ ነው። ያዕ ፪÷፲፯ «ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው» ይለናል። ስለዚህ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች የሚለው የቅብዐት እምነት በራሱ የሞተ ነው ማለት ነው። የሞተን እምነት የሚከተል ሰው ደግሞ በራሱ የሞተ ነው። ስለዚህ ከሞት ለመውጣት ከቅብዐት እምነት ዛሬውኑ መውጣት ያስፈልጋል ማለት ነው።
ቅብዐቶች በአጽዋማት ላይ ሲከራከሩ ለምን በዚህ ቀን አንጀምርም ለምን ጾሙ አጠረብን ወዘተ ብለው እንዳልኾነ ልብ ማለት ተገቢ ነው። ዋና ምክንያታቸው ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለችና ጾም አይጠቅምም የሚለው ትምህርታቸው ነው። በመጀመሪያዪቱ የቅብዐቶች መጽሐፍ በመሰረተ ሐይማኖት ላይ እኮ ጾምን ሸክም ነው ብሎታል። ቀጥሎ ደግሞ ቢጾምም አይተቅምም ባይጾምም ኩነኔ የለውም ብለዋል ስለዚህ በአሚን ብቻ የምትለዋ ናት ዋና ትምህርታቸው። ወደ ምእመኑ ጾም አያስፈልግም ብሎ መግባት አይቻልም ጿሚ ምእመን ስላለ እንዴት ብሎ መጠየቃቸው አይቀርም። ወደ ዋና ጉዳያቸው ጾም አያስፈልግም አሚን ብቻዋን ታድናለች ወደሚለው ኑፋቄ ለመግባት ቀስ ብለው መጀመር ስላለባቸው ነው በአጽዋማት መግቢያ ላይ እንዲከራከሩ ያደረጓቸው።
ስለዚህ ይህን እውነታ ለምእመናን ማድረስ ግዴታችን ይኾናል።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፬/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment