፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አንድ ሰው ከቅብዐት እምነት ወደ ተዋሕዶ ቢመለስ መጠመቅ አለበት ወይስ የለበትም?
የሚል ጥያቄ ከብዙዎች ዘንድ ይመጣል። ስለዚህ ይህን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋልና ወደዚያው እናምራ።
ጥምቀት የሚፈጸምለት ለአመነ ሰው
ኹሉ ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ማር ፲፮÷፲፮ ላይ «ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል» እንዳለ።
ስለዚህ ከመዳን አስቀድሞ መጠመቅ
ከመጠመቅም አስቀድሞ ደግሞ ማመን ይገባል ማለት ነው። ይህ ጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን የምናገኝበት ነው። በመኾኑም፡-
«ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ
ተዉ አትከልክሏቸው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና» ማር ፲÷፲፬
እንዳለ ጌታ በወንጌሉ ሕፃናት በአርባ
በሰማንያ ቀናቸው ይጠመቃሉ። የአባት የእናታቸው ሃይማኖት የእነርሱም እምነታቸው ነውና። ይኸውም በአባታችን አዳምና በእናታችን ሄዋን
የተፈጸመ ነው። አዳም በተፈጠረ በአርባ፣ ሔዋንም በተፈጠረች በሰማንያ ቀናቸው ወደ ገነት ገብተዋልና እኛም ይህን አብነት አድርገን
ወንዶችን በተወለዱ በአርባ ቀን ሴቶችንም በተወለዱ በሰማንያ ቀናቸው እንዲጠመቁ እናደርጋለን። ይህንን የምናገኘው በመጽሐፈ ኩፋሌ
ላይ ነው። መጽሐፈ ኩፋሌ ፬÷፱-፲፪ እና ዘሌዋውያን ፲፪÷፩-፯ ላይ እንደተጻፈ።
ይህ የሕጻናት ጥምቀት ወላጆቻቸው ሲፈቅዱ
በተለይም ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ከኾኑ ነው የሚፈጸመው። ኾኖም ግን በአርባ እና በሰማንያ
ቀኑ ያልተጠመቀን ከአሕዛብነት ከኢአማኒነት የተመለሰን ሰው ባለበት የዕድሜ ዘመን ተምሮ አምኖ ይጠመቃል። ስለዚህ ከአርባ እና ከሰማንያ
ቀናቸው ውጭም አምነው ለሚመለሱ የሚፈጸመው ጥምቀት የልጅነት ጥምቀት ነው ማለት ነው።
አንድ ሰው በማንኛውም የዕድሜ ክልል ካለማመን ወደ አሚነ ሥላሴ ሲመለስ የልጅነት ጥምቀት ይጠመቃል። የሚጸለየው ጸሎት
የሚፈጸመው ሥርዓት በ፵ እና በ፹ ቀናቸው ከሚጠመቁ ሕፃናት የተለየ አይደለም። በ፵ እና በ፹ ቀናቸው ለመጠመቅ ዕድል ያላገኙ ኹሉ በተዋሕዶ ሃይማኖት እና ሥርዓት
አምነው ከተገኙ የልጅነት ጥምቀት በማንኛውም የዕድሜ ዘመን ይጠመቃሉ። እዚህ ላይ ምንም ዓይነት የዕድሜ ገደብ የለውም ያመነ ኹሉ ይፈጸምለታል እንጂ። የልጅነት ጥምቀት ከ፵ እና ከ፹ ውጭ አይፈጸምም ተብሎ አይከለከልም ያመነ
የተጠመቀ ይድናል ሲል ወንጌላዊው የዕድሜ ክልልን አላስቀመጠምና።
እዚህ ላይ በሰዎች ዘንድ ግርታን የሚፈጥረው የቄደር ጥምቀት ነው። የቄደር ጥምቀት ልጅነትን ለማግኘት ሳይኾን የቀደመ ልጅነትን ለመመለስ የሚፈጸም
ጥምቀት ነው። የልጅነት ጥምቀት ተፈጽሞለት ይኖር የነበረ ሰው በብዙ ምክንያቶች ልጅነቱን (በኃጢአት) ያሳድፋል። ርትዕት ከኾነች ከተዋሕዶ ሃይማኖት ወጥቶ ሌላ
እምነት ድርጅት ውስጥ ሊገባ ይችላል። አታድርግ የተባለውን ትእዛዘ እግዚአብሔር ዘንግቶ ሕግ ሊጥስ ይችላል። ኾኖም ግን እግዚአብሔር ልቡን ሲመልስለት
አእምሮውን ሲያድስለት በንስሐ መመለስ ይፈልጋል። በንስሐ የተመለሰ ሰው ይህ የቄደር ጥምቀት ይፈጸምለታል። ጥምቀቱም ከኃጢአት ያነጻዋል ወደ ቀደመ ልጅነቱም
ይመልሰዋል። ስለዚህ የቄደር እና የልጅነት ጥምቀት ሊቀላቀሉብን አይገባም።
የልጅነት ጥምቀት è ልጅነትን ለማግኘት ይፈጸማል።
የቄደር ጥምቀት è በኃጢአት ያደፈ ልጅነትን
ለመመለስ ይፈጸማል።
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፡- አንድ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ከተዋሕዶ ሃይማኖት ውጭ የኖረ ሰው የተዋሕዶ ሃይማኖትን ተምሮ ወደ ተዋሕዶ ሃይማኖት ለመመለስ
ቢፈልግ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ቢኾን የሚፈጸምለት የልጅነት ጥምቀት ነው። ነገር ግን በመዠመሪያ በተዋሕዶ ሃይማኖት አምኖ ወይም በሕፃንነቱ በወላጆቹ ሃይማኖት
ምክንያት በ፵ እና በ፹ ቀን የተጠመቀ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ከተዋሕዶ ሃይማኖት ቢወጣ ልጅነቱን በኃጢአት ቢያሳድፍ እና እንደገና
ወደ ቅድስት ተዋሕዶ እምነቱ ቢመለስ (በንስሐ ማለት ነው) የሚፈጸምለት የቄደር ጥምቀት ነው።
ሥርዓተ ጥምቀት የሚፈጸመው በካህናት እጅ ነው። ይኸውም ከላይ ከፓትርያኩ
እስከ ታች ቄሱ ድረስ ማለት ነው። ዲያቆን አያጠምቅም፣ ሕዝባዊም አያጠምቅም፣ ሴትም አታጠምቅም። ስለዚህም አጥማቂው ሥልጣነ ክህነት
ያለው ማለትም ቄስ፣ ቆሞስ፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስ፣ ፓትርያርክ ሊኾን ይችላል ማለት ነው። ሐናንያና ሰጲራ ከሸጡት መሬት እኩሌታውን ገንዘብ አስቀርተው የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ለማታለል
በልባቸው አሰቡ። በዚህም የተነሣ በሦስት ሰዓታት ልዩነት ባልና ሚስት ተቀስፈዋል። ሐዋ ፭÷፩-፲፩። ይህን ገጸ ምንባብ
ያላንዳች ነገር ወደዚህ አላመጣሁትም። መንፈስ ቅዱስን ማታለል እንደማይቻል ለማሳየት ፈልጌ እንጂ።
በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ሥልጣነ ክህነት የሚሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ጳጳሳት ናቸው። ክህነቱን የሚቀበለው ግን ተምሮ የተገኘ ተጠይቆ የመለሰ ጉባኤ ቤት እየተማረ እንደኾነ የሚያስረዳ
ደብዳቤ የያዘ ኹሉ ነው። ሃይማኖት በውስጥ ናት ልብ አምኖ አፍ ሊክድ ይችላል እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ አፍ አምኖ
ልብ ሊክድ ይችላል እንደ አርዮስ። ታዲያ አርዮሳውያን በአፋቸው አምነው ክህነት ሊያሰጥ የሚችለውን ነገር ኹሉ አሟልተው ከተገኙ
ክህነቱን ለመቀበል ምን ያግዳቸዋል? እንደ ሰው ሰውኛው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ (ክህነቱ የእግዚአብሔር ነውና) ይመስላቸዋል።
ዳሩ ግን በሐሰት ያውም ያለሃይማኖት (በተዋሕዶ ከበረ ብለው ሳያምኑ) መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ ማድረግ ክህነትን ማግኘት አይቻልም።
በነገራችን ላይ ሌሎች ከተዋሕዶ ሃይማኖት ውጭ ያሉ እምነቶች ክህነትን ሊቀበሉ ወደ እኛ ጳጳሳት
የሚሄዱት የቅብዐት እና የጸጋ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ናቸው። እነዚህ እምነቶች በተዋሕዶ ገንዘቦች የሚያጌጡ ናቸውና ነው። ለዚህም
ነው እነዚህ እምነቶች አሉ በሚባልበት አካባቢ የሚገኙ ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት ሲሰጡ «ከተዋሕዶ ሃይማኖት ውጭ ለኾነ ኹሉ ክህነት አልሰጠውም
(ክህነቱ አይደርበት)። የቅብዐት እና የጸጋ ሃይማኖት ተከታይ ካለ አውግዣለሁ። ሥልጣነ ክህነትንም አልሰጠውም። ይህን ተላልፎ ክህነት
እቀበላለሁ ብሎ የመጣ ካለ ውጉዝ ይኹን» ብለው ሥልጣነ ክህነቱን የሚሰጡት። ቅብዐቶች እና ጸጎች በዚህ መልኩ ነው ሥልጣነ ክህነትን
ተቀብለናል የሚሉት። ለጊዜው ሥልጣነ ክህነቱን ይቀበሉና ከወንዝ ሲደርሱ ሰውነታቸውን ታጥበው «ቃለ ውግዘቱን ታጠብሁት ከዚህ ወንዝ
በኋላ አይከተለኝም» እያሉ የማይታለለውን መንፈስ ቅዱስ ያታለሉ መስሏቸው፤ እግዚአብሔር ልብ ያጤሰውን ኩላሊት ያመላለሰውን የማያውቅ
አድርገው በመቊጠር፤ በእግዚአብሔር ላይ በመሳለቅ ሥልጣነ ክህነት የሚያገኙ የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው።
ክህነቱ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ቢኾንም ቅሉ ሥርዓተ ሲመቱ የሚፈጸመው በጳጳሱ ነውና ጳጳሱ «ክህነቱ አይደርበት» ያሉት ሰው ክህነቱ
አያድርበትም ብለን እናምናለን። የሐናንያንና የሰጲራን ታሪክ አስቀድሜ ያመጣሁት ለዚህ ነው። መንፈስ ቅዱስን አታልላለሁ ብሎ መነሣት
ቅስፈት ነው የሚከተለው። ስለዚህም ጥምቀት መፈጸም ያለበት ሥልጣነ ክህነት ባለው ሰው ብቻ ነው።
የቅብዐት እና የጸጋ ሃይማኖት ተከታዮች ሥልጣነ ክህነት የላቸውም። ክህነቱ ሊኖራቸው የሚችለው
በተዋሕዶ ሃይማኖት አምነው ከተጠመቁ ብቻ ነው። ያላመነ ሰው ክህነት እንዴት ሊኖረው ይችላል? አይችልም። ሳጥናኤል አሐዜ መንጦላዕት አቅራቤ ስብሐት የመላእክት ኹሉ አለቃ ነበረ
ግን እኔ ፈጣሪ ነኝ ብሎ ስቷል። ታዲያ መልአክ በመኾኑ ብቻ ልንቀበለው እንችላለንን? አንችልም። ይሁዳ
ቊጥሩ አልጫ የነበረ ዓለምን በትምህርታቸው ጨውነት ካጣፈጡ ዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት መካከል ነበር ነገር ግን አምላኩን በሠላሳ
ብር ሸጠው። ታዲያ ይሁዳ ቊጥሩ ከሐዋርያት መካከል ስለነበር ብቻ ልንቀበለው እንችላለንን? አንችልም። ታዲያ
እነዚህን የመሳሰሉ በክሕደት ውስጥ ያሉ ወገኖች ያጠመቁት ጥምቀት ልጅነትን ያሰጣልን? አያሰጥም።
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምስጢር ፳፱÷፭ ላይ እንዲህ ይላል፡-
«የመንፈስ ቅዱስ ጥላ እንደማይደርሳቸው እንደ እንቁራሪትና አርጃኖ
እንደ ጉማሬም በውኃ ብቻ ተጠመቅህ። በሃይማኖት ዮርዳኖስ ወንዝ ግን አልተጠመቅህም። እርሱም የጥምቀታችን ጸጋ ጰራቅሊጦስ ነው»
ይላል።
ክህነት በሌላቸው በመናፍቃን ዘንድ መጠመቅ እንደ እንቁራሪትና አርጃኖ እንደ ጉማሬም በውኃ ተዘፍቆ
ከመኖር ውጭ መንፈስ ቅዱስን የሚያሳድር የልጅነት ጥምቀት እንደማይኾን በዚህ ተረዳን።
ጥምቀት አትደገምም አትሠለስም አንዲት
ናትና። ጥምቀት አንዲት ናት ስንል የልጅነት
ጥምቀትን የምናገኝባትን ጥምቀት ማለታችን ነው። የቄደር ጥምቀት ከዚህ የተለየ እንደኾነ ከዚህ በፊት ተመልክተናል። የቄደር ጥምቀት እንደአስፈላጊነቱ የሚደገም የሚሠለስ
ነው። ይህንንም ሠለስቱ ምዕት በጸሎተ ሃይማኖት «ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ
ኃጢአት - ኃጢአት በሚሠረዪባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን» ብለዋል ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ፲፯÷፲፪። ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ ኤፌ ፬÷፭ ለይ «ጥምቀትም አንዲት ናት» ይላል። ስለዚህ ጥምቀት አንዲት እንደኾነች እንደማትደገም እንደማትሠለስ በዚህ እናውቃለን።
ጥምቀት አትደገምም አትሠለስም አንዲት
ናት ስንል አጥማቂው ቄስም ኾነ ቆሞስ፣ ኤጲስ ቆጶስም ኾነ ጳጳስ፣ ሊቀ ጳጳስም ኾነ ፓትርያርክ ኹሉም የሚያጠምቋት ጥምቀት አንዲት
ናት ማለት ነው። ቄስ አጥምቆናል ብለን ቆሞስ ስላገኘን ዳግመኛ አንጠመቅም። ቆሞስ አጥምቆናል ብለን ኤጲስ ቆጶስ ስላገኘን ዳግመኛ
አንጠመቅም። ኤጲስ ቆጶስ አጥምቆናል ብለን ጳጳስ ስላገኘን ዳግመኛ አንጠመቅም። ጳጳስ አጥምቆናል ብለን ሊቀ ጳጳስ ስላገኘን ዳግመኛ
አንጠመቅም። ሊቀ ጳጳስ አጥምቆናል ብለን ፓትርያርክ ስላገኘን ዳግመኛ አንጠመቅም። በማዕርግ ደረጃ አንዱ ከፍ አንዱ ዝቅ ቢሉም
ኹሉም የሚያጠምቋት ጥምቀት አንዲት ናት።
ከዚህ በተጨማሪም በማንኛውም ወር
በማንኛውም ቀን በማንኛውም ዕለት ብንጠመቅ ልዩነት የላትም አንዲት ናት እንጂ። በክረምትም ኾነ በበጋ፣ በጸደይም (በበልግም) ኾነ በመፀው (በመከር) የምትፈጸመው ጥምቀት አንዲት ናት። በገጠርም ኾነ በከተማ የምትፈጸመው ጥምቀት አንዲት ናት። ገጠር ስለተጠመቀ ከተማ ሲገባ
ዳግም ተጠመቅ አይባልም። ከተማ ስለተጠመቀም ገጠር ሲገባ ዳግም ተጠመቅ አይባልም። በዚህ ኹሉ ጥምቀት አንዲት ናት ይባላል።
ጥምቀት አንዲት ናት ስንል አጥማቂው
ሥልጣነ ክህነት ያለው እንደኾነ ብቻ ነው። ሥልጣነ ክህነት የሌለው
ሰው ቢያጠምቅ ያ እንደ ጥምቀት አይቈጠርም ምክንያቱም ልጅነትን አያስገኝምና ነው። እስካሁን ድረስ እንደተመለከትነው የቅብዐት ሃይማኖት
ኑፋቄ እና ክሕደት እንደኾነ ተገንዝበናል። ክህነታቸውም ክህነት
እንዳልኾነ ዓይተናል። ስለዚህም በቅብዐት ካህናት የተጠመቁ ሰዎች አማኒ ሊኾኑ አይችሉም። ይህንንም፡-
& ፍትሐ ነገሥት
፫÷፳፬ ላይ «ወለእመቦ ብእሲ ዘተወክፈ ጥምቀተ እምዓላውያን
ኢኮነ ምእመነ - ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኒ አይደለም» ይላል። ስለዚህ ልጅነትን ለማግኘት አማኒ ለመኾን በተዋሕዶ ሥርዓት ጥምቀት ሊፈጸምለት ይገባል ማለት ነው።
ይህ ማለት ግን ጥምቀት ተደገመ ተሠለሰ ማለት አይደለም። በመናፍቃን የተጠመቀው
ጥምቀት አንድ ተብሎ አይቈጠርምና ጥምቀትን ተደገመ ተሠለሰ አያሰኘውም። ይህንንም ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው እንዲህ ብለዋል።
& ረስጠ ፵፬ ላይ «ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን የመናፍቃንን
ጥምቀት ወይም ቊርባናቸውን የተቀበለ ቢኖር ከሹመቱ (ከክህነቱ) ይሻር» ብለዋል።
& ሠለስቱ ምዕት በቀኖና ፲፱ «በእንተ እለ ይበውኡ ውስተ ሕግነ እምሰብአ አላውያን አዘዙ ጉባኤ ቅዱሳን
ከመ ይወስኑ ሎሙ በኵሉ እመቦ ዘኮነ አሐዱ እመናፍቃን
ዘውእቶሙ ሰብአ ጳውሎስ ሳምሳጢ እመቦ ዘቦአ እምኔሆሙ
ውስተ ሕግነ ይጠመቅ ዳግመ እስመ ጥምቀቱ ከመ ወኢምንት ወአኮ ርቱዕ ወዘኮነ ካህነ እምኔሆሙ ጊዜ ግብዓቶሙ ኀቤነ አኮ ክህነቱ
ክህነት ውእቱ እስመ ግብሮሙ ግብር እኩይ ውእቱ ወኢኮነ ርቱዓ ወኢይደሉ ንንግር እምነ ግብሮሙ ምንተኒ ወዘኮነ እምኔሆሙ ሠናየ
ምግባር ወትሑተ እምድኅረ ተወክፈ ጥምቀተ እምኔነ ይትወከፍ ካዕበ ክህነተ እምኤጲስ ቆጶስ በቤተ ክርስቲያኑ ለወልደ እግዚአብሔር
ሕያው» ብሎ ያሳርፈናል።
ከኑፋቄ ተመልሶ ወደ ተዋሕዶ ሃይማኖት ለሚመጣ ኹሉ «ይጠመቅ ዳግመ» ብሎ
ዳግመኛ መጠመቅ እንደሚገባ ተናግሯል። ከዚህ በፊት በመናፍቃን የተጠመቀው ጥምቀት ልጅነትን ስለማያስገኝ ነው። «ይትወከፍ ካዕበ ክህነተ እምኤጲስ ቆጶስ» ብሎ ዳግመኛ ክህነቱን ከኤጲስ ቆጶስ ዘንድ መቀበል እንዳለበት ይናገራል። ይህ ትእዛዘ ሐዋርያት ነው ከዚህ ማለፍ ከዚህም ማትረፍ ሐዋርያትን
እንዳለመቀበል ይቈጠራል።
& የሐዋርያት ሥራ ፲፱÷፩-፮ «ከዚህም በኋላ አጵሎስ በቆሮንቶስ
ሳለ ጳውሎስ ላይ ላዩን ሄዶ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም ጥቂት ደቀ መዛሙርትን አገኘ። ካመናችሁ ጀምሮ በውኑ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን
አላቸው፤ እነርሱም፡- አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እርሱም እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ
አላቸው፤ እነርሱም፡- በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም፦ ዮሐንስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ እየሰበከ
የንስሐ ጥምቀትን አጠመቀ አላቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው
ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደ ያንጊዜም በሀገሩ ኹሉ ቋንቋ ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ» ይላል።
ታዲያ የጌታ መንገድ ጠራጊ በኾነው በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቁት ሰዎች እንደገና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
እንዲጠመቁ ከተደረገ በመናፍቃን በከሃድያን እጅ በቅብዐት ካህናት የተጠመቁ ሰዎችማ እንዴት አይጠመቁም ይባላል?
& መጽሐፈ ምስጢር
፲፩÷፯ ላይ ታላቁ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አንጢዲቆማርያጦስ
ወይም ፀረ ማርያም የተባሉ መናፍቃንን በገሰጸበት ተግሳጹ ላይ እንዲህ ይላል፡-
«ቦ ዘተመይጠ እምሃይማኖቶሙ ውስተ ሃይማኖትነ ይደሉ ከመ ያጥምቅዎ ዳግመ እስመ ኢኮነ
ጥምቀቶሙ ከመ ጥምቀተ ክርስቶስ - ከሃይማኖታቸው ወጥቶ ወደ ሃይማኖታችን የተመለሰ እንኳ ቢኖር ያጠምቁት ዘንድ ይገባል።
ጥምቀታቸው በክርስቶስ ጥምቀት አይደለምና» ይላል።
ድንግል ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ከወለደችው በኋላ ዮሴፍ አውቋታል ያሉ አንጢዲቆማርያጦስ ያጠመቁት
ሰው ወደ እኛ ሃይማኖት ሲመለስ መጠመቅ ይገባዋል ካሉ ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር የሚሉ ቅብዐቶች ያጠመቁትማ ወደ እኛ ሲመለስ አይጠመቅም
ሊባል እንዴት ይቻላል?
ስለዚህ «በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» ብለው በሚያምኑ ካህናት እጅ የተጠመቀ ኹሉ ልጅነት አያገኝም።
ስለዚህም ልጅነትን ለማግኘት የግድ በተዋሕዶ ካህናት አባቶች እጅ መጠመቅ ይኖርበታል። በተዋሕዶ አባቶች የሚፈጸምለት ጥምቀትም ዳግመኛ
ወይም ኹለተኛ ነው አይባልም።
በመዠመሪያ በቅብዐት ካህናት የተፈጸመው ጥምቀት አንድ ተብሎ አይቈጠርምና። ስለዚህ «ጥምቀት አንዲት ናት» የሚለው አይፋለስም።
በአንድ ጥምቀት ኹለት ሃይማኖት ሊመሠረት አይችልም በአንድ ቤተክርስቲያን ኹለት እምነቶች
ሊፈጸሙ አይቻልም። ቅዱስ ጳውሎስ ጥምቀት አንዲት ናት ብቻ ብሎ አልቀረም አንዲት ሃይማኖትም ብሏል እንጂ። ስለዚህ በአንዲት ጥምቀት አንዲት ሃይማኖት ብቻ
ናት ልትሠራ የምትችለው። ይህች ሃይማኖትም የያዕቆብ ወንድም ሐዋርያው ይሁዳ በመልክእቱ እንዲህ ተብላ ተጽፋለች።
«ወንድሞቻችን ሆይ ስለምንካፈለው ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ
ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ኾነብኝ» ይላል ይሁዳ ፫ ላይ።
ስለዚህ ሃይማኖታችን በአምላካችን ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የሰጣት ናት ማለት ነው። ታዲያ
አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለቅዱሳን የሰጣት ሃይማኖት በአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ጥምቀት ልጆቿ ታደርገናለች እንጂ በሌሎች የተጠመቁትን ኹሉ
ልጆቿ አታደርግም።
የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነትን በዚህ እፈጽማለሁ። ከዚህ በበለጠ በሰፊው በደብረ አሚን እንገናኛለን።
አነሣስቶ ያስጀመረንን ለፍጻሜም ያበቃንን አምላክ አመሰግነዋለሁ።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፲፩/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment