Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፲፩



የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፬፡- ቅብዐቶች ወልድን ፍጡር ይሉታል እኛ ግን ፈጣሪ ነው እንለዋለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ተዋሕዶ ስንል መለኮታዊ አካል ከሥጋዊ አካል ጋር፣ መለኮታዊ ባሕርይም ከሥጋዊ ባሕርይ ጋር አንድ የኾነበት ምስጢር ማለታችን ነው። ትልቁ ልዩነታችንም እዚህ ላይ ያለ ነው። እኛ የምንለው ቃል ከሥጋ ጋር፤ ሥጋም ከቃል ጋር ተዋሕዶ አንድ በኾነበት ጊዜ ትስብእትን ክቡር አምላክ አድርጎታል ነው። ቅብዐቶች ግን አካላዊ ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ ሥጋን ማክበር አልተቻለውም በዚህም ምክንያት ወደ ቀደመ አምላክነቱ ለመመለስ ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ አስፈለገው ይላሉ። በቀላል ምሳሌ ብናስረዳ ፍሕም የከሰል እና የእሳት አንድነት ውጤት ነው። እኛ የምንለው ከሰል ፍሕም ለመኾን እሳት ይበቃዋል ባይ ነን። ከሰል ከእሳት ጋር ሲገናኝ አንድነት ይፈጥርና ፍሕም ይኾናል ባይ ነን። ቅብዐቶች ግን ከሰል ከእሳት ጋር ሲዋሐድ ከሰል ፍሕም ለመኾን ከእሳቱ ሌላ ተጨማሪ ነገር ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለቅብዐቶች አስተምህሮ በቂ ምላሽ የሚሰጥ አንድ ምሳሌ ላሳያችሁ። ፍሕምን ውኃ ውስጥ ስታስገቡት «ቲሽ» የሚል ድምፅ አሰምቶ ፍሕምነቱ ይጠፋል። በውኃው ምክንያት ፍሕሙ ጠፍቷል ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ከሰሉ ፍሕም አልባ መኾኑን አይተው ውኃ የሳበውን ከሰል ወደ እሳት ያስገቡታል። ያን ጊዜ እንደገና ፍሕምነቱ ይመለስለታል። የቃልን ከሥጋ ጋር መዋሐድም ልክ እንደዚህ ነው የሚያስቡት። እነርሱ ከዚህ የሚለዩት ጊዜውን ማሳጠራቸው ብቻ ነው።
እኛ ግን ሙሴ በደብረ ሲና እንዳየው ሐመልማል ከነበልባል ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ፤ ሐመልማሉ ነበልባሉን ሳያጠፋው ነበልባሉም ሐመልማሉን ሳያቃጥለው በመጠባበቅ በአንድነት መታየቱን ነው። ይህ የሚኾነው ደግሞ በተዋሕዶ ካልኾነ በቀር በሌላ በምንም ሊኾን አይችልም።
ቅብዐቶች ወልድን ፍጡር ነው ወደ ማለት ያደረሳቸው መሠረታዊ ስህተታቸውም ተዋሕዶ አንድነትን አመጣ እንጅ ክብርን አላሳለፈም ማለታቸው ነው። ቅብዐቶች ወልድን ፍጡር ይላሉ ስንል ግን የራሳቸውን መጽሐፍ እየጠቀስን ነውና መጽሐፋቸው ላይ የጻፉትን ላሳያችሁ።
ወልደ አብ ገጽ ፻፳፯፡-
እንደ ዘርአ ብእሲ የኾነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ #ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የኾነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው ይላል። ወልድ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯል ይልልሃል ሎቱ ስብሐት!
ወልደ አብ ገጽ ፻፴፩፡-
«ወልድንም በሰውነቱ #ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ ቄርሎስ ስምዓት ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ አካል ማድረግ ኃደረ በብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው» ይላሉ።
እዚህ ላይ እንዲያውም ወልድን #ፍጡር ነው ብሎ የማያምን ሰው እንደ ንስጥሮስ ኹለት አካል ኹለት ባሕርይ ወደሚል ክህደት ይገባል ይላሉ። ይህ ስህተት ንስጥሮስ ምን ብሎ እንደካደ ካለማወቅ እና የተዋሕዶን ረቂቅ ምስጢር ካለለመረዳት የሚመጣ በሽታ ነው። ሥጋን ፈጣሪ ኾነ ስላልን የግድ አካላዊ ቃልን ፍጡር ማለት አለብንን? አዎ ካሉ እዚህ ላይ ነው ንስጥሮሳዊነት የሚታየው ምክንያቱም አንዱን አካል ለኹለት አንዱንም ባሕርይ ለኹለት ከፍለውታልና ንስጥሮሳዊነት ነው።
በግዕዝ ጽፈው በደረቁ ያለፏትን ነገር ከመጽሐፉ ብንመለከተው መልካም ነው። ሃይማኖተ አበው መጽሐፋችን ላይ ስምዐት ፻፳፬÷፲፱ ላይ «ለሊሁ ፍጡር ወለሊሁ ፈጣሪ ንብሎ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት» የሚል ነው። ወልደ አብ ላይ የተጠቀሰውን ጥቅስ እና መጽሐፉ ላይ ያለውን የጻፍኹላችሁን ጥቅስ አመሳክሩት ቆርጦ ቀጥሉ በእውነት ማነው?
ወደ አማርኛ ሲመለስም «እርሱ ሰው ነው እርሱም አምላክ ነው። እግዚአብሔር ስለኾነ ፈጣሪ እንለዋለን ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለተወለደ ሰው እንለዋለን» ይላል። «ፍጡረ- ሰው ኾነ» ተብሎ ተተርጉሞ ነው የምንመለከተው። መጻሕፍት «ፍጡረ» የሚለውን ቃል «ፍጡር ሥጋን» በማለትም እያቀኑ ይተረጉማሉ እንጅ በቀጥታው ወልድን ፍጡር ነው ሲሉ አይገኙም። ያማ ቢኾን ኖሮ አርዮስስ ምን ዕዳው ነበራ? ለምን ተወገዛ? አርዮስ ወልድን ፍጡር ያለው በመለኮቱ ነው እኛ ቅብዐቶች ግን ወልድን ፍጡር የምንለው በሰውነቱ ነው ትሉኝ ይኾናል። በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከኾነ በኋላ ይህ ፍጡር ነው ይህ ደግሞ ፈጣሪ ነው ትለው ዘንድ እንዴት ይቻላል? ፍሕምን ይህ ከሰል ነው ይህ ደግሞ እሳት ነው ብለህ ትከፍለው ዘንድ እንዴት ትችላለህ? 
እነርሱ የሚሉት ሥጋን በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው ካልነው መለኮትንም በሥጋ ርስት ፍጡር እንለዋለን ነው። እኛ ግን በተዋሕዶ አንድ ኾኗልና ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ሥጋ ይህ መለኮት ብለን አንከፋፍለውም። አምላክ ሲኾን ሰው ሰው ሲኾን አምላክ ኾኗል እንላለን እንጅ። ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው እንለዋለን። መለኮትን በሥጋ ርስት ሰው ኾነ እንለዋለን ሰውም ስለኾነ የማይዳሰሰውን መለኮት ዳሰስነው፣ ዘመን የማይቆጠርለትንም መለኮት ዘመን ቆጠርንለት፣ ምሉዕ የኾነውንም መለኮት በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ አየነው። ሥጋንም በመለኮት ርስት አምላክ ኾነ እንለዋለን። አምላክ በመኾኑም ሥጋ የሚዳሰሰው የማይዳሰስ የሚጨበጠው የማይጨበጥ መለኮት ኾኗል ዘመን የሚቆጠርለት ዘመን የማይቆጠርለት ዘለዓለማዊ ኾኗል እንላለን።
ሥጋን በመለኮት ርስት በጠራንበት መለኮትንም በሥጋ ርስት የግድ መጥራት አለብን ብሎ እንደ ቅብዐቶች ያለ ስህተት ላይ መውደቅ አይገባም። ሥጋን በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው ካልን የግድ መለኮትንም በሥጋ ርስት ፍጡር ነው ማለት አለብን ብለው የማያባራ ክህደታቸውን ካዘነቡብን እስኪ ይህንን ይመልሱልን እንጠይቃቸው።
ሥጋን በመለኮት ርስት ጻድቅ ነው ስላልን መለኮትን በሥጋ ርስት ሐሳዊ ነው ልትሉት ነውን?
ሥጋን በመለኮት ርስት ቅዱስ ነው ስላልን መለኮትን በሥጋ ርስት ኀጥእ ነው ልትሉት ነውን?
ወልደ አብ ገጽ ፪፻፴፫ ላይ ደግሞ፡-
ቅብዓቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው ይላሉ።
ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ምን ጎድሎበት ነው ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተስተካከለ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚሉት? ይህ ኹሉ የሚያሳየን አካላዊ ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ፍጡር ኾነ ማለታቸውን ነው። ፍጡር ደግሞ ማክበር አይችልምና መንፈስ ቅዱስ አክብሮ አምላክ አደረገው ማለታቸው ነው። እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ የገዛ ያዘዘ አምላክ የኾነ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ቅብዐትን ለቃልም ለመለኮትም ይቀጽላሉ። ፍጡር ነው የሚሉት እኮ ወልድን ነው። ወልድ ደግሞ ፈጣሪ እንጅ ፍጡር አይደለም። ሥግው ቃልን ፍጡር ነው ካሉማ እኛ የምንበላው ሥጋ የምንጠጣው ደም የፍጡር ሥጋና ደም ነውና የዘላለም መንግሥትን አያሰጥም ማለት ነዋ!
ወልደ አብ ገጽ ፪፻፲፱ ላይ፡-
«ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰» በማለት ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ለይተው ዝቅ ሲያደርጉት ይታያሉ። በምስጢረ ሥላሴ ትምህርታችን አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመግዛት አንድ ናቸው፡፡ ይህ የመግዛት አንድነት ወልድ ሥጋን በለበሰ ጊዜ የተቋረጠ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአገዛዝ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድነት ያለው ወልድ ሥጋን ሲዋሐድ ሥጋ ኹሉን የመግዛት ሥልጣንን አምላክ የመኾን ክብርን ከወልድ ያገኛል እንጅ ሌላ ሰጭን አይፈልግም አያስፈልገውምም፡፡ አብ ለወልድ የመግዛት ስልጣንን የሚሰጠው፤ ወልድም የመግዛት ስልጣንን ከአብ የሚቀበል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወልድ በአገዛዝ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት የተለየበት ጊዜ ስለሌለ፡፡ ምናልባት በግልጽ አልጻፈላቸው ይኾናል እንጅ ጸሐፊው «ገብረ መድኅን እንዳለው» ወልድ አምላክነቱን ለዓይን ጥቅሻ ታህል አጥቷል ብሎ ያምናል፡፡ ሎቱ ስብሐት!
አሁንም በግእዝ ጠቅሰው ለማወናበድ «ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰» ይላሉ ትርጉሙን እንመልከት «እኔ እግዚአብሔር ነኝ - ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም» የሚል ነው ቆርጠው ስላስቀሩት ነው እንጅ፡፡ እስኪ አስተውሉ ወገኖቼ! «ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር» ለሚለው «ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም» የሚለው ማስረጃ ሊኾን የሚችለው በምን ሒሳብ ነው? ወይስ ደግሞ ግእዝ ስለኾነ የተጠቀሰው ኹሉ ማስረጃ ይኾናል ማለት ነው? የመጽሐፈ ኑፋቄው ደራሲ ገብረ መድኅን እንዳለው በእውነት መጽሐፍ የተማረ አይደለም ማለት ነው እንጅ እንዲህ ባላለም ነበር፡፡ ከመጻሕፍተ ሊቃውንት የወሰዳቸው ቃላት «እንዲል»«አንድም» የሚሉትን ብቻ ነው እንጅ እውቀታቸውን ትምህርታቸውን አልወሰደም፡፡ በራሱ ደስ እንዳለው የሚጽፍ የልብ ወለድና የፈጠራ ጸሐፊ ነው፡፡
ቅብዐቶች ወልድን ፍጡር ይላሉ እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን ወልድን ፈጣሪ ነው እንላለን ይህ ልዩነታችን ቀላል የሚመስለው ካለ ራሱን ይፈትሽ። የመርፌ ቀዳዳ የማታህል ልዩነት ይዘህ ለምን ትደክማለህ የሚሉ ድምፆች በውስጥ መስመር ይመጣሉ። እኔን ከሚያስገርሙኝ በቀር ከዚህ ሥራዬ ወደኋላ እንድል አያደርጉኝምና አትድከሙ። ልዩነታችን የመርፌ ቀዳዳ ያህል ሳይኾን የሰማይ እና የምድርን ያህል ከዚያም በላይ የተራራቀ ነው። ዶግማ ላይ በመለያየታችን አይደል እንዴ በዓለም ላይ ለቁጥር አዳጋች የኾነ እምነት የተፈለፈለው?
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፪/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment