የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፲፡- እነርሱ «አብ ዳግመኛ ወልድን በሥጋ ወልዶታል» እኛ ደግሞ «የቃል ልጅነት ለሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ ኾነ እንጂ ዳግም በሥጋ አልወለደውም»
እንላለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ወልደአብ የተሰኘው የክህደት መጽሐፋቸው ገጽ ፪፻፲፮-፪፻፲፯ ላይ «የጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ ኹለት
ነው። እንዴት ኹለት ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን
በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ሦስት አይደለምን እንደምን ኹለት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ
በማኅጸን በሥጋ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ
ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ
አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ
ኹለት ልደት አይባልም። ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ
ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ዳግመኛ በአንድ ዘውድ
ኹለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም» ይላል። እዚህ ጽሑፍ ላይ በዋናነት ሦስት መሠረታዊ ስህተቶችን እንመለከታለን፡፡
፩ኛ. በመጻሕፍት ተጽፎ የማናገኘው «አብ ወልድን በማኅጸነ ማርያም በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው» የሚል
ስህተት አለበት፡፡
፪ኛ. መጻሕፍት «ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱም አባት አትሹለት» እያሉ እዚህ ላይ ግን «ለምድራዊ
ልደቱ አባት ሽተውለታል» ስለዚህም ኹለተኛ ስህተት ብለን ቆጠርነው፡፡
፫ኛ. የተቀመጠው ምሳሌ «ሦስት ጊዜ የተቆጠረውን ልደት ኹለት» ብለን እንድንቀበለው የሚያደርግ ማስረጃ
አለመሆኑ፡፡
በእነዚህ ቅደም ተከተሎች በማስረጃ እያስደገፍን የዚህን ስህተት እናጋልጣለን፡፡ «ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ
ከበረ» የምንል ክርስቲያኖች የምናምናቸው ልደታት ኹለት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
፩ኛ. ቅድመዓለም ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል ሳይቀድም ሳይከተል በዚህን ጊዜ ተወለደ በማይባል
ረቂቅ ጥበብ ወልድ ከአብ ያለ እናት የተወለደው ቀዳማዊው ልደት ነው፡፡
፪ኛ. የአዳምን በደል ለማጥፋት ከሴት የሚወለድበት ዘመን በደረሰ ጊዜ በኅቱም ድንግልና በግብረ መንፈስ
ቅዱስ በተዋሕዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው ደኃራዊው ልደት ነው፡፡
ሊቃውንቱ «ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ» ይላሉ፡፡ ኹለቱም ልደታት ከሰው ኅሊና በላይ ከመመርመርም
እጅግ የራቁ ናቸው፡፡ ማንም እነዚህን ልደታት መርምሮ አይደርስባቸውም በረቂቅ ምስጢር የተከናወኑ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን
የምትቀበላቸው የምታምናቸው የምታስተምራቸው በመጻሕፍት የጻፈቻቸው የጌታ ልደቶች ቅድመ ዓለም ያለእናት ከአብ በመለኮት የተወለደው
ልደት እና ድኅረ ዓለም ያለአባት ከቅድስት ድንግል ማርያም መለኮት በሥጋ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በቅብዐቶች ዘንድ
«ወልድ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወልዷል» የሚለው ሦስተኛው ልደት በየትኛውም የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት
ዘንድ ተመዝግቦ አናገኘውም፡፡ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎችን ማሳየት ይቻላል።
ቤተክርስቲያናችን ኹለት ልደት ብላ ቆጥራ የምታስተምረውን እነርሱ ግን ባለመረዳት ሦስተኛ ልደት አምጥተዋል።
ይህ «ሦስተኛው ልደት» ከየት መጣ ስንል አንድ የሚጠቅሱት ጥቅስ አለ እርሱም መጽሐፈ ምስጢር ምእራፍ ፫ ቁጥር ፵፮ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዚህ መጽሐፉ ላይ የጻፈው እንዲህ የሚል ነው፡፡ «ነገርነኬ
በእንተ ህላዌ መለኮቱ ወትስብእቱ እምድኅረ ስጋዌሁ ኢንቤሎ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወወልደ እጓለእመሕያው በትስብእቱ፤ ድንግልኒ
ወለደት ዘኢዚአሃ መለኮተ በዘዚአሃ ሥጋ ምስለ ዘዚአሃ ሥጋዌ ፤ አብኒ ወለደ ዘኢዚአሁ ሥጋ በዘዚአሁ መለኮት ምስለ ዘዚአሁ ኃይል
ዘህሉና አምላክ - ስለመለኮቱ እና ስለ ትስብእት ህልውና እነሆ ተናገርን፡፡ ሰው ከመሆኑ በኋላ በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ በሰውነቱም
የሰው ልጅ አንለውም፡፡ ድንግልም ለእርሷ በተገባ ሥጋዌ የእርሷ በኾነ ሥጋ የእርሷ ያልኾነውን መለኮት ወለደችው ፤ አብም የባሕርይው
ያልኾነውን ሥጋ የባሕርዩ ከኾነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በኾነ መለኮት ወለደ» የሚል ነው፡፡ ከዚህ ትምህርት መካከል
ቅብዓቶች አብ በማኅጸነ ማርያም ወልዶታል ለሚለው ክህደታቸው ቆርጠው የወሰዱት «አብም የባሕርይው ያልኾነውን ሥጋ የባሕርዩ ከኾነ
የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በኾነ መለኮት ወለደ» የሚለውን ነው፡፡
ሊቁ ወደ ምስጢር ሄዶ «አብም የባሕርይው ያልኾነውን ሥጋ የባሕርዩ ከኾነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ
በኾነ መለኮት ወለደ» ብሎ ተናገረ፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብም ለቃል ገንዘቡ እንደኾነ እናምናለን፡፡
ስለዚህ ቃል ከሥጋ ጋራ በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ «ወልደ አብ ቃለ አብ» መባልን ገንዘቡ አደረገ ማለት ነው፡፡ ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ኾነ
ቀዳማዊ አምላክ በመሆኑም ወልደ አብ ተባለ ማለትም ሥጋ የአብ ልጅ ተባለ ማለት ነው፡፡ ለወልድ አባቱ የኾነ አብ ለክርስቶስም
(ለሥግው ቃል) አባቱ ተባለ ማለት እኮ ነው፡፡ ቃል ከአብ በመለኮት የተወለደበት ልደት ለሥጋም ገንዘቡ ኾነ ሲል ነው። ስለዚህ
ሥጋ ወልደ አብነትን (የአብ ልጅ መባልን) ገንዘቡ አደረገ አለ ሊቁ፡፡ ይህን ምስጢር አርቀቆ የተናገረበት ግሩም ትምህርት እንደኾነ
በዚህ እንረዳለን፡፡
ቅብዐቶች ከላይ እንደጻፍነው «እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ
እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ሦስት አይደለምን እንደምን ኹለት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ
የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ኹለት
ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው
አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ
ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም» ይላሉ፡፡ ይኼ ለማንም ለሚያይ ለሚሰማ ኹሉ እንደ ግንባር ግልጥ የኾነ የተሸሸገ ነገር የሌለው አይደለምን? እዚህ ላይ በግልጥ የምንመለከተው ሦስት
ልደታትን ማመናቸውን ነው፡፡ መጻሕፍት «ኹለት ልደታትን እናምናለን» ብለው ስላጠሩባቸው ለመንፈራገጥ አልመች ቢላቸው ሦስት ጊዜ
ቆጥሮ ኹለት ማለት ይገባል ብለው ተናገሩ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው በግልጥ የተቀመጡት የጌታ ልደቶች እነዚህ ናቸው፡፡
፩ኛ. እምቅድመ ዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደት
፪ኛ. በማኅጸን በሥጋ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት
፫ኛ. ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ በማለት ሦስት ልደታትን አስቀምጠውልናል፡፡
ከእነዚህ ልደታት መካከል
፪ኛው ልደት በየትኛውም መጽሐፍ ተጽፎ እንደማይገኝ ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች በማስረጃ በማስደገፍ ጽፈናል፡፡ እነርሱ እንደሚሉት
፩ኛ እና ፪ኛ ላይ የተገለጡት ልደቶች አንድ ተብለው ይቆጠራሉ እንጅ ኹለት አይባሉም ይላሉ፡፡ ለምን ለሚለው መልስ ሲመልሱ «ኹለት
ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው
አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ
ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም» ይላሉ፡፡ በእውነት ምንም የማይመስል የማይገናኝ ከንቱ ነገር ነው፡፡ «እምቅድመዓለም
በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም» ማለት ምን ማለት ነው? እዚች
ላይ ያዝ አድርጓት እስኪ፡፡ የቀደመ ልደቱ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ሳይቀድም ሳይከተል ያለእናት በመለኮት በረቂቅ
ምስጢር የተደረገ ነው፡፡ የዛሬው ልደቱ ደግሞ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ በመለኮት አይደለም ምክንያቱም አብ የወለደው
በሥጋ ነው ብለውናላ፡፡ በመለኮት ነው ካሉ ወልድ በመለኮቱ ስንት ጊዜ ተወለደ ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ በሥጋ ነው የወለደው ካሉን
ደግሞ መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን መለኮታዊ ባሕርይም ሥጋዊ ባሕርይን ይወልድ ዘንድ ይቻላልን ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ አዎን
ሊወልድ ይቻለዋል ካሉን የቀደመው ልደቱ ከአብ በመለኮት ነው የዛሬው ልደቱ ደግሞ ከአብ በሥጋ ነውና ኹለት ብለን እንቆጥረዋለን
እንጅ አንድ ልደት አንለውም ብለን በዚህ እንረታቸዋለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ መረታትን ስለማይሹ «ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት
መንፈስ ቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም» ብለው መከራከራቸው
አይቀርም፡፡ ነገር ግን ወላዲው አብ ይኹን ተወላዲውም ወልድ ይኹን አይቀየር አይለወጥ እንጅ ልደቱ ግን ለየቅል ነው እንላቸዋለን፡፡
ምክንያቱም «የቀደመው ልደት በመለኮት የዛሬው ልደት በሥጋ» ነውና ልደቱ በጣም ይለያያል እንላቸዋለን፡፡ አብ በመለኮት ቅድመ ዓለም
የወለደው ልደት እና ዛሬ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው የሚሉት ልደት እጅግ የተለያየ እንደኾነ ልብ ማለት ተስኗቸዋል፡፡
ለዚህም እኮ ነው ይች «ዛሬ አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው» የምትለዋ ተጨማሪ የፍልስፍና ልደት ትቅር መጽሐፍ
አይደግፋትም የምንለው፡፡ የጻፉትን ነገር ስትመለከቱት ፈራሽ ነገር ነው፡፡
ቀጥለው ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ይሉናል፡፡ ልብ በሉ! ሦስት ልደት ቆጥረው ኹለት ልደት ነው ላሉበት የተሰጠ
ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ምሳሌው «ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ
ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም።
ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ኹለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት
ዘውድ አይባልም» እነዚህን ምሳሌዎች ዘርዘር አድርገን ፍትፍት ብትንትን አድርገን እንመልከታቸውማ!
=========================================
፩ኛ. የአዲሱ ሸማ ጉዳይ ከልደቱ ጋር እስኪ ይዛመድ፡፡
=========================================
#ምሳሌነቱ፡- ሸማው ወልድ ነው፡፡ ለባሹ አብ ነው፡፡ ስለዚህ ለበሰ ለሚለው ቃል አቻው ወለደ የሚለው ይኾናል
ማለት ነው፡፡ ከረጢቱ የድንግል ማርያም ማኅጸን ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ ልብ በሉ አስተውሉ ወገኖቼ!!! የጌታ ልደት እንደዚህ በከረጢት
ገብቶ እንደመውጣት ያለ ተራ ነገር አድርገው ማሰባቸውን፡፡ ያም ኾነ ይህ ግን ሸማው ወልድ መጀመሪያ በለባሹ (አብ) ተለበሰ (ተወለደ)
ቀጥሎ በከረጢት በተመሰለው የድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ (ተዋሐደ) ከዚያ ከዚህ ከረጢት ለባሹ (አብ) አውጥቶ ለበሰው (ወለደው)
ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ለባሹም ልብሱም አልተቀየረም አልተለወጠም ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ስንት ጊዜ ለበሰው ብለን ብንጠይቅ
ለባሹ እና ልብሱ ስላልተለወጡ ስላልተቀየሩ አንድ ጊዜ ለበሰው ሊባል ይችላል እንዴ? ኹለት ጊዜ ስለተለበሰ ኹለት ሸማ ሳይኾን አንድ
ሸማ ይባላል የሚለው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን በሸማው የተመሰለው ወልድ አይለወጥ አይቀየር እንጅ ኹለት ጊዜ ተወልዷል ማለት ነው፡፡
ለዚህ ነው ይህ ምሳሌ «እምቅድመዓለም ከአብ የተወለደውንና በማኅጸነ ማርያም ከአብ የተወለደውን ኹለት ልደት ኹለት ብለን እንድንቆጥር
እንጅ አንድ ብለን እንድንቆጥር አያደርግም እና የወልድ ልደቶች ሦስት ናቸው እንደሚሉ ጥሩ ምሳሌ ነው» የምንለው፡፡
=========================================
፪ኛ. የዘውዱ ጉዳይ ከልደቱ ጋር ያለው ምሳሌነት ሲዛመድ፡፡
=========================================
«ዳግመኛ በአንድ ዘውድ
ኹለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም»
#ምሳሌነቱ፡- ዘውዱ አብ ነው፡፡ ነጋሹ ወልድ ነው፡፡ ንግሥናው የልደት ምሳሌ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአንዱ
ዘውድ (በአብ) ብዙ ነገሥታት (ልጆች) ይነግሡበታል (ይወለዱበታል) ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይኼ ምኑ ነው ሦስት ልደት ብለው የቆጠሩትን
ኹለት እንድንል የሚያሳምነን? ምናልባት እዚህ ላይ «ዘውዱ» እንደ ልደት ተቆጥሮ ከኾነ ነጋሹ ወልድ አንጋሹ አብ ናቸው ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በአንዱ ዘውድ ኹለት ሦስት ነገሥታት እንደሚነግሡበት ኹሉ በአንዱ ልደትም ኹለት ሦስት ልጆችን ወለደ ያሰኝባቸዋልና ይህም
የተዋረደ ከንቱ ምሳሌ እንደኾነ በዚህ እንረዳለን፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ ያልተጻፈ በሊቃውንት በመምህራን ያልተነገረ እንግዳ የኾነ ትምህርትን ዝም ብላችሁ መቀበል
እንደማይገባችሁ ለኹሉም የቅብዐት እምነት ተከታዮች ኹሉ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ መሰዳደቡን መጨቃጨቁን ትተን እውነትን ወደ
መመርመር እንግባ፡፡ እኛ ከተሳሳትን መጽሐፍ ጠቅሳችሁ ሊቃውንቱን አብነት አድርጋችሁ እውነቱን አሳዩን እናንተ ከተሳሳታችሁ ግን
እኛን ምሰሉን!!!
ተሰፍረው ተቆጥረው በሊቃውንት የተነገሩት የጌታ ልደታት በመጽሐፎቻቸው እንዲህ እንመለከታለን።
፩ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘሄሬኔዎስ ፯÷፳ «ከንጽሕት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን እንደተወለደ እንደሚነግሩን
ቀድሞም ከአብ እንደተወለደ እንዲሁ ከአባት ያለእናት ከእናት ያለአባት ለመወለድ መዠመሪያ እርሱ እንደኾነ ለፍጥረት ኹሉ ይነግሩናል»
ይላል።
፪ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ፳፫÷፪ «ለመወለዱ ጥንት በሌለው አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በመለኮቱ
ከአብ በተወለደ ዳግመኛም እኛን ለማዳን በኋላ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በእግዚአብሔር ልጅ እናምናለን የቀኑ ቀጠሮ
ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከድንግልም ተወለደ ያለ ብፁዕ ሐዋርያ እንዳስተማረን» ይላል።
፫ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ፴፬÷፮
«ዳግመኛ ለወልደ እግዚአብሔር ኹለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል፤ አንዱ ከዘመን ኹሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ
የተወለደው ልደት ነው፤ ኹለተኛውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ልደት ነው» ይላል።
፬ኛ. ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ፴፭÷፲፯ «በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ በሰማያዊ ልደቱም እናት
አለችው አትበሉ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው በሰማይም እናት የሌለችው ነው» ይላል።
፭ኛ. «ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር - በሰማይ እናት በምድርም አባት የለውም» አንቀጸ ብርሃን
ዘቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ።
ከላይ የተዘረዘሩትን የሊቃውንቱን ማስረጃዎች ስትመለከቱ ቅብዐቶች ካነሡት ሦስተኛ ልደት ጋር የሚገናኝ ነገር
የለውም። በርካታ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል በርግጥ አንባቢን ላለማሰልቸት ነው እንጂ።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፴/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment