፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ታሪኩን ጨርስልን የሚሉ ድምፆች ስለሚበዙ በተከታታይ ሦስት ክፍሎች ታሪኩን እጨርስና ወደ ዋናው ጉዳያችን እንገባለን ማለት ነው። በነገራችን ላይ ታሪኩ ውስጥም የምንመለከተው የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት አለ። ይህንንም በሊቃውንቱ ክርክር መካከል የምናገኘው የመከራከሪያ እና የመርቻ ሐሳብ ነው።
*****
እስካሁን ካየነው ታሪክ እንደተረዳነው የቅብዐት እምነት ምንጩ ባህሉ የካቶሊክ እምነት እንደኾነ ነው። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የቅብዐት እና የጸጋ እምነት በሀገራችን ብቅ ማለት የጀመሩ። ከዚህ በኋላ ይህን የቅብዐት እምነት በማስፋፋት ብዙ ተከታዮችን ማፍራት እንደቻለ እናውቃለን። ተከታዮችን ማፍራትም ብቻ ሳይኾን በሀገራችን ሑከትና ብጥብጥ ሲፈጥር ኖሯል። ከአቡነ ስምዖን በጦርነቱ መካከል መገደል በኋላ አንድ ግብጻዊ ጳጳስ ህዝቡን ሲቀስጥ ተይዞ በደቅ ተግዞ ነበር። ዐፄ ፋሲልም ከግብጽ ጋር ተነጋግረው አቡነ ማርቆስ የተባሉትን ጳጳስ ወደ ሀገራችን አስመጡ። ይህ ጊዜ ቅብዐትና ጸጋ የተስፋፉበት ወቅት ስለነበር አዲሱን ጳጳስ ጉባኤ ሥሩልን ከተዋሕዶዎች ጋር መከራከር እንፈልጋለን ብለው ቅብዐትና ጸጋዎች በአንድነት ተነሡ። ንጉሡና ጳጳሱ በሚገኙበት ቀኑ ተቆረጠና በዚያ ቀን በዘኢየሱስ የተወከሉ ቅብዐቶች በአዳም እምፍራዝ ከተወከሉ ተዋሕዶዎች ጋር ተከራክረው ተዋሕዶዎች አሸነፉ።
የውጮቹ ዓላማ ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብላ በአንዲት ሃይማኖት የምታምን የምታሳምን የምታስተምር የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መከፋፈልና የህዝቡን አንድነት አሳጥተው እነርሱ እፎይ እንዲሉ ነበር። ያም ተሳክቶላቸው እነርሱ በተከሏቸው እሾኾች ወንድም እና ወንድም ተለያይቷል ደም መፋሰስም ኾኗል።
ከዚህ በኋላ በነገሡት በዐፄ ዮሐንስ ቀዳማዊ ዘመነ መንግሥትም ቅብዐቶችና ተዋሕዶዎች ክርክር አድርገዋል። ንጉሡ ጉባኤውን ፈቅደው ተዋሕዶዎች በአንድ ወገን ቅብዐትና ጸጋዎች በሌላ ወገን ኾነው ክርክር አድርገዋል። በዚህ ክርክር በጣም የሚደንቅ ጥያቄ ከተዋሕዶዎች ተወካይ ቀርቧል። ጥያቄውም «ሃይማኖት አንዲት ናት ወይስ ኹለት» የሚል ነበር። የቅብዐት እና የጸጋዎች ተወካይ «አንዲት ናት ብል ለምን ኹለት ኾናችሁ መጣችሁ ሊሉን ነው ኹለት ብል ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት ሃይማኖት ብሎብሃል ብሎ ይረታኛል» ብሎ ዝም አለ። ንጉሡ ግን ከቅብዐት እና ጸጋዎች ጋር ወግነው ስለነበር ጣልቃ ገብተው ይህን ተወውና ሌላ ጥያቄ ጠይቅ ብለውታል። የተዋሕዶዎች ተወካይም ሌላ ቀን ይቀጠርልኝ በማለቱ ስምንት ቀን ተሰጠ። እርሱም በንጉሡ የተዛባ ዳኝነት ተናዶ ተማሪዎቹን ይዞ ወደ አክሱም ሄደ። ቅብዐትና ጸጋዎች በየመንገዱ «ዛሬ ንጉሡ ባያደሉልን ኖሮ ተረትተን ነበር» ይሉ ነበር። ይህም ቅብዐቶችና ጸጋዎች በቤተመንግሥቱ ላይ ተቀባይነት እንደነበራቸው ያስረዳል።
በዚህ ዘመን ቅብዐቶች በጎጃም ጸጋዎችም በጎንደርና በሸዋ በጣም ተስፋፍተው ስለነበር ሊቃውንቱ እርስ በርሳቸው ይተማሙ ነበር። በልጃቸው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ግን ቅብዐቶች ወደ ቤተመንግሥት የሚያስጠጋቸው አላገኙም ነበርና የሃይማኖት ክርክር ሳይነሣ ኖሯል።
በዐፄ ተክለሃይማኖት ዘመነ መንግሥት ግን ንጉሡ እና ጳጳሱ በተገኙበት ክርክር እንዲደረግ ተወስኖ በጉባዔውም ድሉ ለተዋሕዶዎች ኾነ። ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስም ከዚህ በኋላ «ክርስቶስ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» የሚሉትን ኹሉ አወግዛለሁ አሉ። ቅብዐት በብዛት ተስፋፍቶ የነበረው በጎጃም አካባቢ ስለነበር ለዚህ ጉባኤ ከጎጃም አካባቢ የመጡት ኹሉ ታሰሩ። ይህ አካሄድ ጅምላ ፍረጃ ነው። አንድን አካባቢ በሙሉ እንዲህ ነህ ማለት አስፈላጊ አይደለም። ከአምስቱ ጣቶቻችን መካከል አንዷ ብትቆረጥ እጁ ጣት የሚባል ነገር የለውም ሊባል አይገባም። ከአምስቱ አንዲቷ ናትና የጎደለች። ይህ ቅብዐት እምነት በብዛት በጎጃም ተስፋፍቶ ይገኛል የሚለው እውነት ቢኾንም ሙሉ ጎጃም ቅብዐት እምነት ተከታይ ነው ብሎ መናገር ግን አያስደፍርም። ጎጃም ኾኖ ቅብዐት የሚባለው እምነት ምን እንደኾነ በስም ደረጃ እንኳ የማያውቀው ብዙ ነው። ለዚህ ጉባኤ ከጎጃም የመጡ ሊቃውንት በሙሉ ቅብዐት ናችሁ ተብለው መታሰራቸው ያሳዝነኛል። የታሪክ ጸሐፊው ተክለጻድቅ መኩሪያ ዐፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘ መጽሐፋቸው ቅብዐቶች በጎጃም በተለይም ደግሞ በደብረ ወርቅ አካባቢ በብዛት ተስፋፍተው ይገኛሉ ብለው ይጽፋሉ። ገጽ ፻፶፮
ከዐፄ ተክለ ሃይማኖት በኋላ የነገሡት ዐፄ ቴዎፍሎስ ግን የጎጃሞችን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ እንደቀደምቱ ነገሥታት ጉባኤ ሳያዘጋጁ ክርክር ሳያስደርጉ «ክርስቶስ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ ኾነ» የሚል አዋጅ አወጁ። ይህን ዐዋጅ ሲያውጁ የተዋሕዶ ሊቃውንት ምነው ንጉሥ ሆይ «እንደ አባቶችዎ ጉባኤ ሳይዘረጉ ክርክር ሳያዳምጡ ይህን ዐዋጅ ዐወጁ ብለው ጠየቋቸው። እርሳቸውም ጎጃሞችን ስለምወድ ነው አሉ ይባላል። ጅምላ ፍረጃው አሁን ድረስ እንደዘለቀ ያሳያል። ጎጃሞችን ስለወደዱ የቅብዐትን ባህል ከተቀበሉ እኮ ሙሉ ጎጃም ቅብዐት እንደኾነ ነበር የሚረዱት ማለት ነው።
ዐፄ ዮስጦስ የተባሉ በ፲፯፻፲፬ ዓ.ም የነገሡት ንጉሥ ደግሞ የጦር መሣሪያ ለመቀበል ሲሉ ሦስት ሚሲዮኖችን በወልቃይት ዐይነ እግዚእ በሚባል ቦታ ደብቀው ያማክሯቸው ነበር። ይህ ምስጢር የወጣው ንጉሡ ከሞቱ በኋላ ነበር። እነዚህ ሚሲዮናውያንም ሚካኤል፣ ሳሙኤል እና ዳዊት የሚባሉ የኦስትሪያ እና የሮም ተወላጆች ነበሩ።
ከኹለት ዓመት በኋላ ዐፄ ዳዊት አብራክ ሰገድ ንግሥናውን ሲረከቡ አባ መዝሙር በዐፄ ዮስጦስና በነዚህ ሦስት ሚሲዮናውያን መካከል የነበረው ግንኙነት የተደበቀውም ምስጢር ይገለጥ ዘንድ እነዚህ ሰዎች እንዲቀርቡ ለንጉሡ አመለከቱ። ከዚያም ንጉሡ ፈቅደው ጉባኤ አድርገው ሦስቱ ሰዎች ቀረቡ። ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው ተብለው ተጠየቁ እነርሱም ካቶሊካውያን ነን አሉ። እናንተማ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ወገኖቻችንን ደም ያፋሰሳችሁ አይደላችሁምን ብለው በሞት ቀጧቸው።
ከእነዚህ ሚሲዮናውያን መገደል በኋላ ውስጥ ውስጡን እንደ ሰደድ እሳት የተስፋፉት ቅብዐትና ጸጋዎች ጉባኤ እንዲያዘጋጁላቸው ንጉሡን ጠየቁ። ንጉሡም ጉባኤውን ፈቀዱ። የንጉሡ ቢትወደድ የቅብዐቶች ደጋፊ ስለነበር ቅብዐቶች ተስፋ ሰንቀው የጉባዔውን መድረስ ይጠባበቁ ነበር። ንጉሡም እጃቸው ያለበት በሚመስል ሁኔታ በዚህ ጉባኤ እንደማይገኙ በአንጻሩ ግን እርሳቸውን ወክሎ እንዲገኝ ቢትወደዳቸው ዘጊዮርጊስን ወደ ጉባኤው እንዲሄድ ትእዛዝ መስጠታቸውን አሳወቁ። ይህን የሰሙት የተዋሕዶ ሊቃውንት የቢትወደዱን ቅብዐት መኾን ያውቁ ነበርና ተቃወሙ። ይህን ተቃውሞ የሰሙት ንጉሥ ዳዊት «ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ እንጂ አስተዳደራዊ ጉዳይ አይደለምና እኛን አይመለከትም ከጳጳሳችሁ ጋር ጨርሱ» ብለው ጉዳዩን ለጳጳሱ ክሪስቶዶሉ (ገብረ ክርስቶስ) መሩት። ንጉሡ ይህን ያደረጉት ራሳቸውን ከሀሜት ለማዳን ነበር።
ጳጰሱ ግን አድር ባይና ፈሪ ስለነበሩ የንጉሡን እና የቢትወደዱን አቋም ዓይተው ፈሩ። ፍርሐታቸውም መባል የማይገባውን ነገር እንዲሉ አደረጋቸው። ጳጳሱ «ሃይማኖትዎ ምንድን ነው» ተብለው ሲጠየቁ «ሃይማኖቴማ እንደ ቀደሙ አባቶቼ እንደ አባ ማርቆስ እንደ አባ ሲኖዳ ነው» ብለው መለሱ። ጳጳሱ «ሃይማኖቴ ተዋሕዶ» ነው ብለው ቢመልሱ ኖሮ መልካም በኾነ ነበር ዳሩ ግን የንጉሡን እና የቢትወደዱን አቋም ስለተመለከቱ በፍርሐት እና በአድር ባይነት ይህን መልሰዋል።
ቅብዐቶችም ይህን የጳጳሱን ቃል ይዘው ለንጉሡ ነገሩት። ንጉሡም የአባ ማርቆስ እና አባ ሲኖዳ ሃይማኖት ምን ነበር ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም በውሸት እና በድፍረት ቅብዐት ነዋ ብለው መለሱ። ንጉሡም ይህማ ከኾነ «በተዋሕዶ የባሕርይ ልጅ የሚሉት ተረቱ በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ የሚሉት ረቱ» ብላችሁ ዐዋጅ ዐውጁ አሉ ዐዋጁም ወዲያው ታወጀ። በዚህ ነገር ያዘኑ የተዋሕዶ ሊቃውንት ጳጳሱን ለብቻቸው ይዘው ሃይማኖትዎ ምንድን ነው ብለው ጠየቋቸው በዚህ ጊዜ ብቻቸውን ስለነበሩ «ሃይማኖቴ ተዋሕዶ ነው» አሏቸው።
በዚህ በጳጳሱ መልስ የተደሰቱ የተዋሕዶ ሊቃውንትም ወደ ዕጨጌው ቤት አዘዞ ሄደው «ንሴብሖ» እያሉ እንደ እስራኤላውን ከፍ አድርገው ዘመሩ። ይህ የደስታ ዝማሬ ጎንደር ለንጉሡ ዐፄ ዳዊትና ለቢትወደዱ ዘጊዮርጊስ በወሬ አቀባዮች ፈረስነት ተጭኖ ደረሳቸው። ይህን የሰሙት ንጉሡ እና ቢትወደዳቸውም ይህን መዝሙር የዘመሩ የተዋሕዶ አርበኞችን ዐዋጃችንን ጥሰዋል ሕጋችንን ተላልፈዋል በሚል እስላሞችንና አረማውያንን መሣሪያ በማስታጠቅ በዕጨጌው ቤት የተሰበሰቡትን በሙሉ አንድ እንኳ ለምስክር ሳያስተርፉ ፈጇቸው። ዕጨጌ ተክለሃይማኖትንም እግራቸውን ከከብት ጭራ ጋር አስረው ራቁታቸውን መሬት ለመሬት ሲጎትቷቸው ዋሉና ገደሏቸው። ይህ በተዋሕዶዎች ላይ የደረሰው ግፍ ቀላል የሚባል አይደለም። የተዋሕዶ አርበኞችም ይህን ያህል ተጋድሎ ፈጽመው ሳለ የፈጸሙትን ገድል ያህል አይወራላቸውም አልተወራላቸውምም። አድር ባዩ እና ፈሪው ጳጳስም በንጉሡና በቢትወደዱ ጫና «በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ ኾነ» ብለው ዐወጁ።
ከዚህ በኋላ በዘመነ መሳፍንት ዐፄ ቴዎድሮስም ኢትዮጵያን ከተዋሕዶ ሃይማኖት ለይተው አያዩም ነበር ዐፄ ዮሐንስ አራተኛም ለተዋሕዶ ሃይማኖት ዘብ በመቆም አገራችን በሚሲዮናውያኑ ትምህርት እንዳትከፋፈል በብርቱ ሠርተዋል። በዚህም የተነሣ የቅብዐት እና የጸጋ እምነቶች እንደ ቀድሞው ማበብና ማፍራት አልተቻላቸውም ነበር። እንደ ውኃ እናት ግን ጊዜውን እያዩ ብቅ ጥልቅ ማለታቸው አልቀረም ነበር። ወሩን ዓይቶ ጊዜውን ተመልክቶ እንደሚፈካና እንደሚፈነድቅ አበባ እነርሱም የቤተመንግሥቱን እና የቤተክህነቱን ወቅታዊ ሁኔታ እየቃኙ ብቅ ሲሉ ኖረዋል። በዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ መንግሥት አክሱም ላይ በተዋሕዶዎችና በቅብዐቶች መካከል ክርክር ተካሂዷል። በዚህም ጉባኤ የ«ተቀብዐ» ትርጓሜ ተዋሐደ ሰው ኾነ ማለት ነው እንጂ ሌላ ክብርን ማግኘት እንዳልኾነ ተዋሕዶዎች አመስጥረው አራቀው ቅብዐቶችን ረቷቸው።
የቅብዐቶች ነገር በዚህ መልኩ አልቆለት የተቀበረ ቢኾንም በሸዋ አካባቢ ጸጋዎች እንደ አዲስ በመነሣታቸው ተዋሕዶዎችን አስቸገሩ። ቤተክርስቲያናችን እፎይ ብላ እረፍት ያገኘችበት ጊዜ እንደሌለ በዚህ እንረዳለን። በጸጋዎች በአዲስ መነሣት እና መስፋፋት የተነሣ ለመጨረሻ ጊዜ በተዋሕዶ ሊቃውንት ጉድጓድ ተምሶ የተቀበሩት በ፲፰፻፸፰ ዓ.ም በተካሄደው የቦሩ ሜዳው ክርክር ነበር።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፭/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment