Tuesday, October 9, 2018

«ፍኖተ ሕይወት» በአባ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘሀገረ ካናዳ ---ክፍል ፫



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አባ ማትያስ የጻፉት #ፍኖተ_ሕይወት መጽሐፍ ገጽ ፪፻፲፱ ላይ «ሥጋን በቃልነቱ ፈጣሪ እንዳሉ ቃልን በሥጋነቱ ፍጡር ማለት ይገባል? ንብሎ ፈጣሬ በእንተ ከመ እግዚአብሔር ወአምላከ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ በሥጋ በእንተ ዘተወልደ እምብእሲት እንዳለ #ቂርሎስ፤ ቃልንስ በሰውነቱ ፍጡር ካላሉ ሥጋን በቃልነቱ ፈጣረሪ ማለት አይገባም» ይላሉ።
ገብረ መድኅን እንዳለው የጻፉት #ወልደ_አብ ገጽ ፻፴፩ «ወልድንም በሰውነቱ #ፍጡር ብሎ ማመን ይገባል። ለሊሁ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ እምብእሲት እን ቅዱስ #ቂርሎስ ስምዓት ፲፱ ሥጋ በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው። መለኮት በሥጋ ርስት ፍጡር ነው። ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ አካል ማድረግ ኃደረ በብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው» ይላሉ።
እዚህ ላይ እንዲያውም ወልድን #ፍጡር ነው ብሎ የማያምን ሰው እንደ ንስጥሮስ ኹለት አካል ኹለት ባሕርይ ወደሚል ክህደት ይገባል ይላሉ። ይህ ስህተት ንስጥሮስ ምን ብሎ እንደካደ ካለማወቅ እና የተዋሕዶን ረቂቅ ምስጢር ካለመረዳት የሚመጣ በሽታ ነው። ሥጋን ፈጣሪ ኾነ ስላልን የግድ አካላዊ ቃልን ፍጡር ማለት አለብንን? አዎ ካሉ እዚህ ላይ ነው ንስጥሮሳዊነት ነው የሚታየው ምክንያቱም አንዱን አካል ለኹለት አንዱንም ባሕርይ ለኹለት ከፍለውታልና ንስጥሮሳዊነት ነው።
በግዕዝ ጽፈው በደረቁ ያለፏትን ነገር ከመጽሐፉ ብንመለከተው መልካም ነው። ሃይማኖተ አበው መጽሐፋችን ላይ ስምዐት ፻፳፬÷፲፱ ላይ «ለሊሁ ፍጡር ወለሊሁ ፈጣሪ ንብሎ ፈጣሪ በእንተ ከመ ውእቱ አምላክ ወእግዚአብሔር ውእቱ ወዓዲመ ንብሎ ፍጡረ እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት» የሚል ነው። ወልደ አብ እና ፍኖተ ሕይወት ላይ የተጠቀሰውን ጥቅስ እና ሃይማኖተ አበው ላይ ያለውን የጻፍኹላችሁን ጥቅስ አመሳክሩት ቆርጠው ነው የቀጠሉት።
ወደ አማርኛ ሲመለስም «እርሱ ሰው ነው እርሱም አምላክ ነው። እግዚአብሔር ስለኾነ ፈጣሪ እንለዋለን ወዲህም ከድንግል በሥጋ ስለተወለደ ሰው እንለዋለን» ይላል። «ፍጡረ- ሰው ኾነ» ተብሎ ተተርጉሞ ነው የምንመለከተው። መጻሕፍት «ፍጡረ» የሚለውን ቃል «ፍጡር ሥጋን» በማለትም እያቀኑ ይተረጉማሉ እንጅ በቀጥታው ወልድን ፍጡር ነው ሲሉ አይገኙም። ያማ ቢኾን ኖሮ አርዮስስ ምን ዕዳው ነበራ? ለምን ተወገዛ? አርዮስ ወልድን ፍጡር ያለው በመለኮቱ ነው እኛ ቅብዐቶች ግን ወልድን ፍጡር የምንለው በሰውነቱ ነው ትሉኝ ይኾናል። በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከኾነ በኋላ ይህ ፍጡር ነው ይህ ደግሞ ፈጣሪ ነው ትለው ዘንድ እንዴት ይቻላል? ፍሕምን ይህ ከሰል ነው ይህ ደግሞ እሳት ነው ብለህ ትከፍለው ዘንድ እንዴት ትችላለህ? 
እነርሱ የሚሉት ሥጋን በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው ካልነው መለኮትንም በሥጋ ርስት ፍጡር እንለዋለን ነው። እኛ ግን በተዋሕዶ አንድ ኾኗልና ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ሥጋ ይህ መለኮት ብለን አንከፋፍለውም። አምላክ ሲኾን ሰው ሰው ሲኾን አምላክ ኾኗል እንላለን እንጅ። ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው እንለዋለን። መለኮትን በሥጋ ርስት ሰው ኾነ እንለዋለን ሰውም ስለኾነ የማይዳሰሰውን መለኮት ዳሰስነው፣ ዘመን የማይቆጠርለትንም መለኮት ዘመን ቆጠርንለት፣ ምሉዕ የኾነውንም መለኮት በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ አየነው። ሥጋንም በመለኮት ርስት አምላክ ኾነ እንለዋለን። አምላክ በመኾኑም ሥጋ የሚዳሰሰው የማይዳሰስ የሚጨበጠው የማይጨበጥ መለኮት ኾኗል ዘመን የሚቆጠርለት ዘመን የማይቆጠርለት ዘለዓለማዊ ኾኗል እንላለን።
ሥጋን በመለኮት ርስት በጠራንበት መለኮትንም በሥጋ ርስት የግድ መጥራት አለብን ብሎ እንደ ቅብዐቶች እና እንደ አባ ማትያስ ያለ ስህተት ላይ መውደቅ አይገባም። ሥጋን በመለኮት ርስት ፈጣሪ ነው ካልን የግድ መለኮትንም በሥጋ ርስት ፍጡር ነው ማለት አለብን ብለው የማያባራ ክህደታቸውን ካዘነቡብን እስኪ ይህንን ይመልሱልን እንጠይቃቸው።
ሥጋን በመለኮት ርስት ጻድቅ ነው ስላልን መለኮትን በሥጋ ርስት ሐሳዊ ነው ልትሉት ነውን?
ሥጋን በመለኮት ርስት ቅዱስ ነው ስላልን መለኮትን በሥጋ ርስት ኀጥእ ነው ልትሉት ነውን?
ይህ በአባ ማትያስ የተጻፈው ፍኖተ ሕይወት ከወልደ አብ ጋር ያለውን ልዩነት እስኪ ተመልከቱት ምንድን ነው ልዩነቱ? ታዲያ ወልደ አብ ይወገዝልን ብለን ፊርማ ስንሰበስብ ኖረን ዛሬ በራሳችን ሱቅ እንዴት ሊከፋፈል ይችላል? ይህ የዘወትር ጥያቄዬ ነው። ወልደ አብን አሳጥረው የገለበጡት አባ ማትያስ ማን እንደኾኑ ግን የምታውቁ ሰዎች ብታሳውቁን መልካም ነው። ሊቃውንቱ መነሻ ሃሳብ እንዲኖራቸው የተጻፈ ነው። መጽሐፉን የሚያከፋፍሉ የማኅበረ ቅዱሳን ሱቆችም ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ የተጻፈ ነው።
ማመሳከር እንድትችሉ ፍኖተ ሕይወት ላይ ያለውን እና ወልደ አብ ላይ ያለውን ጽሑፍ ከዚህ ጋር አብሬ አያይዠላችኋለሁና አንብቡት።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፳፯/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment