በኮምፒዩተር ትምህርት ቋንቋ መሠረት «Recycle Bin» ትርጉሙ ከፍተኛ ነው። አንድን ነገር እንሠራለን
ከሠራንም በኋላ ቦታ እንዳይዝብን በማሰብ እናጠፋዋለን «Delete» እናደርገዋለን። «Delete» ማድረግ በራሱ ችግር አይደለም
ምክንያቱም አንደኛ ቦታ ስለሚይዝብን ኹለተኛም ካጠፋነው የተሻለ ለመሥራት በማሰብ ነውና። በዚያውስ ላይ የጠፉ ፋይሎች የሚታገቱበት
«Recycle Bin» የተባለ የጠፉት መገኛ እያለ ምን ችግር ሊመጣብን ነው። ችግር የሚኾነው «Undo» ብለን ወይም
«Restore» አድርገን መመለስ በማንችልበት መልኩ ፋይሎችን ካጠፋናቸው ነው። ለዚኽም እኮ ነው የ «IT» ተማሪዎች
«Undo» ባትኖር ኖሮ እኮ አንመረቅም ነበር ይላሉ የሚባለው። በስህተት እናጠፋለን በስህተት ያጠፋነውንም ነገር በ«Undo» እና
በ«Restore» እንመልሳቸዋለን።
ነገር ግን በ«Undo» እና በ«Restore» እንዳይመለስ አድርገን «Permanently Delete» ካደረግነው
በራሳችን ስናዝን ከመኖር ውጭ የጠፉትን ኹሉ መመለስ አንችልም። አውቀንም ኾነ በስህተት «CTRL+DEL»ን ከተጫንነው ፋይላችንን
«Recycle Bin» ከተባለው የጠፉት መሰባሰቢያ ካምፕ ላይ አናገኘውም። በዚኽም የተነሣ ለአንድ ቀንም ቢኾን እንኳ ያ ያጠፋነው
ፋይል አስፈላጊ ኾኖ ብናገኘው ጸጉራችንን ከመንጨት ከንፈራችንን ከመምጠጥ ውጭ ነበረን እኮ ከማለት ውጭ «Undo» እና
«Restore» እንኳ ተባብረው ሊመልሱት አይችሉም።
አሁን ስለ ኮምፒዩተር እያስተማርኩ እንዳይመስላችሁ ስለራሳችን ስለሥራችን ስለተግባራችን እንጅ። አንድ ሰው
ወንጀል ሊሠራም ላይሠራም ይችላል፣ በኾነ ምክንያት ብቻ «Permanently Delete» እንዲደረግ ይፈረድበታል። ማን እንደሚፈርድበት
እንኳ አይታወቅም ብቻ የኾነ አካል «Permanently Delete» አድርጎት ዳግም ላናገኘው እንሰናበተዋለን። በዚህ መልኩ በርካታ
ለሀገር ለወገን የሚጠቅሙ በርካታ ሰዎችን አጥተናል። እነ በላይ ዘለቀ፣ እነመንግሥቱ እና ግርማሜ ንዋይ፣ እነ አቡነ ጴጥሮስ፣ እነ
አቡነ ሚካኤል፣ እነ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ እነቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣
እነበዓሉ ግርማ፣ እነ ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ፣ እነ ሳሙኤል አወቀ ወዘተ ወዘተ። በነገራችን ላይ ዘርዝሬ መጨረስ እንደማልችል አውቃለሁ
ግን የተወሰኑትን በየዘመናቱ «Permanently Delete» የተደረጉ ሰዎችን ነው የጠቀስሁላችሁ። እነዚህ ሰዎች በማን
«Permanently Delete» እንደተደረጉ እንዴት እንዲጠፉ እንደተደረጉ የሚታወቅ ነገር የለም። በርግጥ በስቅላት እና በጥይት
ተደብድበው በሰው ፊት በአደባባይ «Permanently Delete» የተደረጉትን ማን እንዳጠፋቸው እናውቃለን። ታሪክም መዝግቧቸው
ስለሚገኝ በዚያ እናውቃለን። አብዛኞቹ ግን በማን እንዴት እንደጠፉ በራሱ አይታወቅም።
እኛ ሰዎች ነን። ዘመናችን ከዚህ እስከ እዚህ ተብሎ የተገደበ፣ ቋሚ ኾኖ ለዘለዓለም የሚኖር ዘላለማዊ ሰው
እንደሌለም እናውቃለን። ታዲያ አንዱ አንዱን ያጠፋው ዘንድ ምን ዓይነት ሰይጣን ነው የመከረው? ይችን አጭር ዘመን መታገስ እንዴት
ያቅተናል? አንተ አጠፋኸውም አላጠፋኸውም አንተም እርሱም በኾነ ዘመን ላይ ሳትወዱ በግድ መጥፋታችሁ አይቀርም እኮ። ታዲያ የኾነ
ጊዜ ላይ ያ ያጠፋነው ሰው ለሰው ለወገን ቢያስፈልግ «Undo» እና «Restore» አድርገን ልንመልሰው እንዴት እንችላለን?
ሰዎች ነንና እናጠፋለን፣ እንሳሳታለን፣ ሕግ ልንጥስ ሥርዓት ልናፈርስ እንችላለን። ነገር ግን ይህ ጥፋት
ኾኖ ቢገኝ እንኳ ማሰር እንጅ መግደል መፍትሔ ይኾናል ብየ አላስብም። የታሰሩ ሰዎች «Recycle Bin» ውስጥ እንደሚገኙ የጠፉ
ፍይሎች ይቆጠራሉ። እነዚኽ በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎች ለሀገር ለወገን አስፈላጊ ኾነው ቢገኙ ባስፈለጉ ሰዓት ከእስር «Undo»
እና «Restore» በማድረግ ፈትቶ ማሠራት ይቻላል። እነ በላይ ዘለቀ፣ እነመንግሥቱ እና ግርማሜ ንዋይ፣ እነ አቡነ ጴጥሮስ፣
እነ አቡነ ሚካኤል፣ እነ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ እነቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣
እነበዓሉ ግርማ፣ እነ ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ፣ እነ ሳሙኤል አወቀ ወዘተ ወዘተ «Recycle Bin» በተባለ እስር ቤት ቢኾኑ ኖሮ
ዛሬ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሀገሪቱ መንግሥት በወሰነበት ጊዜ በቀላሉ ከእስር ፈትቶ ለሀገር ለወገን በጠቀሙ ነበር። ነገር
ግን ዳግም «Undo» እና «Restore» አድርገን እንዳናገኛቸው ኾነው
«Permanently Delete» ተደርገዋልና ከንፈር ከመምጠጥ ጸጉር ከመንጨት ያለፈ ነገር ልናደርግ አንችልም። ዛሬ
አያስፈልገንም ብለን ያጠፋነው ፋይል ነገ እንደሚያስፈልገን ስለምናውቅ «Recycle Bin» ውስጥ እንደምናጠራቅመው ኹሉ ዛሬ አጥፍተዋል
ወንጀለኞች ናቸው የምንላቸውን ሰዎችም ነገ አስፈላጊ ስለሚኾኑ እስር ቤት ውስጥ ብናጠራቅማቸው ይሻላል። ከእስር ቤት ውጡ በሚል
ቃል ብቻ ማስወጣት ይቻላልና «Permanently Delete» የተደረጉ ፋይሎችን ዳግም መመለስ እንደማንችል ኹሉ ማን እንደኾነ
እንዴት እንደኾነ ሳይታወቅ ሰውንም በሞት ማስወገድ ለነገ ቁጭትን የሚፈጥር ስለኾነ እንደ ሰው አስበን ብንኖር መልካም ነው።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፫/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment