Tuesday, October 9, 2018

«ፍኖተ ሕይወት» በአባ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘሀገረ ካናዳ ---ክፍል ፪



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
«ወልደ አብ» ገጽ ፻፳፮ እና «ፍኖተ ሕይወት» ገጽ ፪፻፲፭ ያላቸው ዝምድና ምንድን ነው? ፍኖተ ሕይወት ገጽ ፪፻፲፭ ላይ «መፍጠርስ እንዴት ነው? ቢሉ ነፍስ የሚኾነውን ባሕርየ ሥጋ ማድረግ ነው። ፈጣሪ ማለት ዓይን ጆሮ አፍንጫ ከንፈር እጅና እግር የቀረጸ ማለት ነው። ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእመቤታችን ደመ ድንግልናዋን ከፍሎ ተዋሕዶ ተወልዷልና እንደ ዘርዐ ብእሲ የኾነ ወልድ ነው፤ ሳይዋሐድ አልፈጠረም ተዋሕዶም ሳይፈጠር አልቆየም ሲዋሐድ ሲፈጠር ፩ ጊዜ ነው። የዘርዐ ብእሲስ ደምነቱን ለቆ አንድ አካልና አንድ ባሕርይ ይኾናል። የወልድና የደመ ድንግልና ተዋሕዶ ግን አካሉ ሳይጠፋ ነው» ይላሉ። የፊደል ግድፈቶች ራሱ አለመስተካከላቸው የወልደ አብን ሶፍት ኮፒ ተረክበው አሳጥረው የወሰዱት ይመስለኛል።
ከላይ «ፍኖተ ሕይወት» ላይ ተጽፎ የምናገኘው ምንፍቅና ወልደ አብ ገጽ ፻፳፮ እና ፻፳፯ ላይ በተከታታይ የተጻፈ ነው። «እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው» ወልደ አብ ገጽ ፻፳፯፡፡   ወልደ አብ ገጽ ፻፳፮ ላይ ደግሞ ሲፈጠር እና ሲዋሐድ አንድ ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ  “… ተዋሕዶ ተፈጠረ ሳይዋሐድ አልተፈጠረም፡፡ ተዋሕዶ ሳይፈጠር አልቆየም፡፡ ሲዋሐድ ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ተዋሕዶ ቀደመ ባሉ ጊዜ ከቅብዓትም ተዋሕዶ ቀደመ ማለት ይሆናል” ወዘተ በማለት ይጽፋሉ።
ሙሉውን ከኹለቱም መጻሕፍት እያነጻጸራችሁ እንድትመለከቱ እጠቁማችኋለሁ። «ተዋሕዶ ተፈጠረ» በሚለው የመጀመሪያው ስህተት ላይ «ፍኖተ ሕይወት» «ደመ ድንግልናዋን ከፍሎ ተዋሕዶ ተወልዷልና» በማለት ሲጽፍ ወልደ አብ ላይ «ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና» በማለት ጽፈዋል። በዚህ በመጀመሪያው የክህደቱ መግቢያ ላይ «ፍኖተ ሕይወት» የተሻለ ነገር ይዟል። «ተዋሕዶ ተፈጠረ» በማለት ፈንታ «ተዋሕዶ ተወልዷልና» ስላለ ይሻላል። ነገር ግን ቀጣይ በሚመጡ ጽሑፎች ላይ «ተዋሕዶ ተፈጠረ» ማለቱ ስላልቀረ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አልቀረፈም ክህደቱንም ሙሉ በሙሉ አላስወገደም። ምክንያቱም በሚቀጥለው ጽሑፉ ላይ «ሳይዋሐድ አልፈጠረም ተዋሕዶም ሳይፈጠር አልቆየም ሲዋሐድ ሲፈጠር ፩ ጊዜ ነው» ብሏልና። አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐደው ሥጋ ክቡር አምላክ ኾኗል እንላለን እንጅ በተዋሐደ ጊዜ ተፈጠረ አንልም። ቃል ሲዋሐደው ፍጡሩ ሥጋ ከብሮ አምላክ ኾነ ይባላል እንጅ ቃል ስለተዋሐደው የሥጋ ፍጡርነት ቃልን ፍጡር ያደርገዋል ሊባል እንዴት ይቻላል?
በነገራችን ላይ ተዋሕዶ ማለት ግን አንድ መኾን ማለት አይደለም እንዴ? ታዲያ አንድ ነው ካልን ማን ነው ተፈጠረ የሚባለው? ሥጋ ነው እንዳትሉን ሥጋማ መጀመሪያውንም ፍጡር ነው፤ ቃል ነው እንዳትሉን አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐድ ሥጋ አምላክ ይኾናል እንጅ ፈጣሪ ወደ ፍጡርነት ሊቀየር እንዴት ይችላል? ሥግው ቃል ነው የተፈጠረ ካላችሁ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ነው ማለታችሁ ነውና ከአርዮስ በምን ተለያችሁ? አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ስላለው እንጅ በሥጋው ፍጡር ቢለው ባልተሳሳተም ነበር የምትሉትም ሸውራራ ትምህርታችሁ ተዋሕዶን እንደማታውቁት ማሳያ ነው። ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ሥጋ ነው ይህ ደግሞ መለኮት ነው ሊባል እንዴት ይቻላል? አንዱ ለስንት ይከፈላል? ለስንትስ ይሰነጠቃል?
ሌላው ወልደ አብ ላይም ፍኖተ ሕይወት ላይም የምናገነው «እመንፈስ ቅዱስ» የሚለውን ግብረ መንፈስ ቅዱስ መተርጎም ላይ ያለ ጠማማ ትምህርት ነው። ፍኖተ ሕይወት ገጽ ፪፻፲፭ ላይ «መናፍቃን ግን ተሰብአ እመንፈስ ቅዱስ ያለውን ይዘው ከመንፈስ ቅዱስ ዘርእ ከማርያም ደም ተከፍሎ ወልደ ተፈጠረ ብለዋል» ይላል። መናፍቃን ሊላቸው የቻለ መንፈስ ቅዱስን እንደ ዘርአ ብእሲ አድርገው የሚቆጥሩትን ሰዎች እንጅ ወልድ ተፈጠረ የሚሉትን አለመኾኑን ግልጽ ነው። ከማርያም ደም ተከፍሎ ወልድ ተፈጠረ ቢሉ ኖሮ ግን መናፍቅ አይባሉም ነበር በዚህ መጽሐፍ ትምህርት መሠረት።
ገጽ ፪፻፲፮ ላይም «ከመንፈስ ቅዱስ ዘር ተከፍሎ ወልድ ተፈጠረ ሲል አይደለም ብሏል» በማለት «እመንፈስ ቅዱስ» ያለውን ሲተረጉሙ ይታያሉ። «ከመንፈስ ቅዱስ ዘር ተከፍሎ» የሚለው ቢወጣ ግን እውነት ይኾን ነበር ማለታቸው ነው። በእውነት «እመንፈስ ቅዱስ» ሲሉ ሊቃውንት ምን ማለታቸው ነው። ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ያለውን ብቻ ትርጓሜ በአጭሩ ላቅርብላችሁ። «ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ፡፡ ወተሰብአ እመንፈስ ቅዱስ ይላል አብነት እም፡ በ፡ ነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ሐተታ የከፈለ ያነፃ ያዋሐደ መንፈስ ቅዱስ ነውና ወእማርያም እምቅድስት ድንግል፡፡ እም እና እም አንድ ወገን ነው እመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው የሆነ፡፡ አንድም መንፈስ ቅዱስ ከመክፈሉ የተነሣ እመቤታችን ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ ከማለቷ የተነሣ ሰው የሆነ» በማለት ሊቃውንቱ ይተረጒማሉ።
ፍኖተ ሕይወት ገጽ ፪፻፲፰ ላይ «ይከፈል ብለው ቢያዙ ከእመቤታችን ደመ ድንግልና ተከፈለ። ይፈጠር ብለው ቢያዙ ወልድ ከደመ ድንግልና ተዋህዶ ተፈጠረ። ወልድንም በሰውነቱ አርእስት ፍጡር ማለት ይገባል? እንደ አርዮስ ክህደት አይኾንም? ቢሉ አርዮስስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ኾነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለውስ ክህደት ባልኾነበትም በመለኮቱ ግን ፍጡር ቢለው ክህደት ኾኖበታል» ይላሉ። ይኸው አገላለጽ ወልደ አብ ገጽ ገጽ ፻፴-፻፴፩ «ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደ አርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት» ይላል፡፡ እዚህ ላይ የምጠቁማችሁ የኹለቱን መጻሕፍት ተመሳሳይነት እንጅ ወልደ አብን ስንመለከት መልስ የሰጠንባቸው ክህደቶች ናቸው ድጋሜ እያየናቸው ያሉትና ዳግም መልስ መስጠት አልፈልግም።
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ «ፍኖተ ሕይወት» የተባለውን መጽሐፍ ሊቃውንቱ እንዲመረምሩት መነሻ ሃሳብ ማቅረብ እና ይህ መጽሐፍ ትክክል ነው ብለው ባለማወቅ የሚያከፋፍሉ ሰዎች ራሳቸውን ቆም ብለው እንዲፈትሹት ማስደረግ ነው።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፳፭/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment