የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፰፡- እነርሱ «በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» እኛ ደግሞ «በተዋሕዶ ከበረ» እንላለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
መጀመሪያ
ስለተዋሕዶ እና በተዋሕዶ ከበረ ስለሚለው የእኛ ትምህርት እንነጋገር። ተዋሕዶ ስንል ከኹለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ ከኹለት አካላት
አንድ አካል መኾኑን መናገራችን ነው። ይኸውም መለኮታዊ ባሕርይ እና ሰብአዊ ባሕርይ፣ መለኮታዊ አካል እና ሰብአዊ አካል ናቸው።
እነዚህ ባሕርያት እና አካላት ሊነጣጠሉ የማይችሉ አንድ ኾነዋል። በተዋሕዶ ከበረ ማለትም አካላዊ ቃል ከትስብእት ጋር ሲዋሐድ ትስብእት
አምላክነትን ገንዘቡ አድርጓል ማለታችን ነው። ትስብእት ክቡር አምላክ የኾነው በተዋሕዶ ነው ማለታችን ነው። ይህንንም በፍሕም መስሎ
ማየት ይቻላል። ከሰል ፍሕም የሚኾነው ከእሳት ጋር ስለተዋሐደ ብቻ ነው። ትስብእትም አምላክ የኾነው የከበረው በተዋሕዶ ነው ማለት
ነው። ይህን የምንለውም አካላዊ ቃል ክቡር አምላክ ስለኾነ ነው። አምላክ ደግሞ የተዋሐደውን ሥጋ ማክበር የራሱ ነው አክብሩኝ ብሎ
የሚጠይቅ አይደለም።
ቅብዐቶች ግን ተዋሕዶው ክብር አላሳለፈለትም ይላሉ። ትስብእት
አምላክ የኾነው በተዋሕዶ ሳይኾን ከተዋሕዶ በኋላ በተፈጸመለት ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ። ይህንን ትምህርታቸውንውም ወልደ
አብ ገጽ ፪፻፴፪ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን። «ተዋሕዶ ክብር
የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብዓት
አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ኹለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን
አላሳለፈም» ይላሉ። ልዩነታችን በግልጽ ይታያችሁ። እኛ የምንለው የመለኮት ክብር ለትስብእት ገንዘብ የኾነው በተዋሕዶ ብቻ ነው።
ተዋሕዶ ኹለትንትን አጥፍቶ አንድነትን ያመጣ ብቻ ሳይኾን ትስብእትን አምላክ ያደረገ፤ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብም
ለመለኮት ገንዘብ የኾነው በተዋሕዶ ብቻ ነው ባይ ነን። ቅብዐቶች ግን ተዋሕዶ አንድነትን ብቻ አመጣ እንጅ ክብርን አላሳለፈም ክብር
ያሳለፈ ቅብዐቱ ነው ይላሉ።
እኛ የተዋሕዶ ልጆች በተዋሕዶተ ቃል ሥጋ ክቡር አምላክ ሆኗልና
በተዋሕዶ ከበረ እንላለን፡፡ ይህንንም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ድርሳን ፪ ቁጥር ፻፶፭ ላይ እንዲህ ይላል «…አብን በልብነት
መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስነት ገንዘብ ለማድረግ ሥጋ ቃልን ተዋሐደ» ስለዚህ ሥጋ የአብን ልብነት የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስነት
ገንዘቡ ያደረገው ቃል ስለተዋሐደው እንጅ መንፈስ ቅዱስ በቅብዐትነት ስላከበረው አይደለም ማለት ስለዚህ ነው፡፡
ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ ላይ «ወካዕበ
ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ
እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ
ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት
አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ
ነዳይ ስለኾነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከኹሉ በላይ የኾነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የኾነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ
እንደኾነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ» ይላል። ስለዚህ ራሱ ሥጋን የተዋሐደው አካላዊ ቃል አክባሪ ነው ማለት ነው።
ይህም ማለት ሥጋ በተዋሕዶተ መለኮት አምላክ ኾነ ለሥጋ አምላክ ከመኾን የበለጠ ምን ክብር ይመጣለታል ታዲያ?
ተዋሕዶ ኹለትነትን ብቻ ያጠፋ ክብርን ያላሳለፈ ነው የሚሉት
ቅብዐቶች ክብርን ያገኘ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ወልድም በባሕርይ ክብሩ ሥጋን አልተዋሐደም ያሰኝባቸዋልና
ክብርን ለማግኘት የጸጋ አምላክ ኾነ ያሰኛል፡፡
è«በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» የቅብዐቶች ከባድ ኑፋቄç
=======================================
ከላይ
የተመለከትናቸው ጥቂት ማስረጃዎች እንደሚያስረዱን ሥጋ ክቡር አምላክ የኾነው በተዋሕዶ ነው ማለት ነው። ስለዚህም «ወልድ ዋሕድ
በተዋሕዶ ከበረ» ማለት እውነተኛ እና የቀደመች መንገድ የቀናችም
ሃይማኖት ናት።
ከዚህ
እውነት ወጥተን «በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» ማለት በርካታ ኑፋቄዎች አሉበት። በዚያውስ ላይ «በመንፈስ ቅዱስ ከበረ» የሚለው
ትምህርት ቀድሞ በሊቃውንት የተወገዘ አይደለም እንዴ? ታዲያ የተወገዘ ኑፋቄ እንዴት አሚን ሊኾን ይችላል። ቅዱስ ቄርሎስ ሃይማኖተ
አበው ፸፫÷፵፱ ላይ፡-
«ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት
ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤
የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይኹን» ይላል።
«በቅብዐተ
መንፈስ ቅዱስ ከበረ» ብሎ ማመን የተወገዘው ምስጢር ስለሚያፋልስ ነው። ምስጢር የሚያፋልስበትን ነገር ደግሞ አስከትለን እንመለከታለን።
èመለኮታዊ ግብርን ይከፍላልç
===================
ምስጢረ
ሥላሴ ላይ አስቀድመን እንደተመለከትነው አካላዊ ግብር ሦስት ሲኾን መለኮታዊ (አምላካዊ) ግብር ግን አንድ ነው። በሥላሴ ዘንድ
የአካላዊ ግብር ሦስት መኾን የመለኮታዊ ግብራቸውን ለሦስት አይከፍለውም። የመለኮታዊ ግብራቸው አንድ መኾንም የአካላዊ ግብራቸውን
አይጠቀልለውም። መለኮታዊ ግብር ከምንላቸው መካከል አንዱ «ማክበር» ነው። በማክበር ደግሞ ሦስቱም አካላት አንድ ናቸው። «አብ
እና ወልድ ሥጋን አላከበሩትም ያከበረው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው» ብሎ መናገር መለኮታዊ ግብራቸውን ካለመረዳት የሚመጣ ስሕተት ነው።
እኛ «ቃል ሥጋን አከበረው የባሕርይ አምላክም አደረገው» ስንል እኮ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ቃል ብቻውን አክባሪ ነው
ብለን አይደለም። ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከክብር አንድነት ሳይለይ ሥጋን ተዋሐደው የባሕርይ አምላክም
አደረገው ማለታችን ነው። ወልድ አከበረ ስንል አብ እና መንፈስ ቅዱስም አከበሩ ማለታችን ነው። «በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ»
የሚለው አነጋገር ግን ከዚህ የተለየ ነው። «ወልድ ሥጋን በመዋሐዱ ለሥጋ ክብር አልተላለፈለትም» ይላሉ። እንደ እነርሱ አነጋገር
«ሥጋ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ የኾነው በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ (በመንፈስ ቅዱስ ክብርነት) ነው» ማለት ነው። በእነርሱ
አነጋገር መሠረት ይህ መንፈስ ቅዱስ ሥጋን የባሕርይ አምላክ ያደረገበት ክብር በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ካለው ክብር የተለየ
ነው። እኛ «ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ» የምንል የተዋሕዶ ልጆች ግን በክብር መለያየት የለባቸውምና ቃል ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ
ጋር አንድ በኾነ በራሱ ክብር የተዋሐደውን ሥጋ አከበረው እንላለን።
è«መንፈስ ቅዱስም ሥጋ ለበሰ» ያሰኝባቸዋል።ç
===============================
መንፈስ
ቅዱስ ሥግው ቃልን (ኢየሱስ ክርስቶስን) አከበረው ካሉ መንፈስ ቅዱስም ሥጋ ለበሰ ያሰኝባቸዋል። «ሲዋሐድ ሲቀባ» አንድ ጊዜ ነው
የሚለውን የመተርጒማነ ወንጌል ትምህርት ቅብዐቶችም ይስማሙበታል። አተረጓጎማቸው አፈታታቸው ግን ለራሳቸው እንዲስማማ አድርገው ስለኾነ
በኃይለ ቃሉ ላይ መስማማታቸው ብቻውን ወደ መልካሚቱ መንገድ አላደርሳቸውም ወደ ኑፋቄ አዘቅት ጣላቸው እንጂ።
ሊቃውንት
ወንጌልን ሲተረጉሙ ማቴዎስ ወንጌል ፩÷፲፮ ላይ «ሲቀባም ሲዋሐድም አንድ ጊዜ ነው» ይላሉ። «ቀባ» ማለት አከበረ ማለት ነው በዚህም
መሠረት «ሲዋሐድም ሲቀባም አንድ ጊዜ ነው» ማለት ሲዋሐድም ሲከብርም አንድ ጊዜ ነው ማለት ነው። በተዋሕዶ ከበረ ማለትም እኮ ይኸው ነው። «ሲቀባ ሲዋሐድ አንድ ጊዜ
ነው» አካላዊ ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ቀባው (አከበረው) ማለት ነው። ስለዚህ ነው «ሲቀባም ሲዋሐድም አንድ ጊዜ ነው» ማለት።
ቅብዐቶች
«ሲቀባም ሲዋሐድም አንድ ጊዜ ነው» በሚለው የሊቃውንቱ ትምህርት የሚያምኑ ከኾነ በተዋሕዶ ከበረ ብለው ወደ ቀናችው ሃይማኖት ወደ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በመጡ ነበር ነገር ግን ቃሉን ለራሳቸው ከመተርጐም ባለፈ ምስጢር ሲመረምሩ አይታዩም።
«በቅብዐተ
መንፈስ ቅዱስ ከበረ» ማለት መንፈስ ቅዱስም ሥጋ ለበሰ ያሰኛል ማለታችንም መክበሩ በኅድረት ነው ወይስ በተዋሕዶ ነው የሚለውን
ጥያቄ የሚያስነሣ ስለኾነ ነው። በኅድረት ቢሉ መንፈስ ቅዱስ ያከበረው በኅድረት ከኾነ በቅዱሳን ላይ አድሮ እንደሚኖረው ያለ ነውና
የጸጋ ልጅ ቢያስብለው እንጂ የባሕርይ ልጅ አያስብለውም። በተዋሕዶ ነው ቢሉ መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ጋር ተዋሕዶ ሥጋን ያከበረው
ከኾነ መንፈስ ቅዱስም ሥጋን ለበሰ ያሰኝባቸዋል።
èወልድን ከአምላክነት ክብሩ ዝቅ ያደርጋል።ç
=============================
ከሦስቱ
አካላት አንዱ አካላዊ ቃል ፈጥሮ የተዋሐደውን ሥጋ ክቡር አምላክ ማድረግ አይችልም የሚል ኑፋቄ ያለበት ነው። አካላዊ ቃል ፈጥሮ
የተዋሐደውን ሥጋ ማክበር የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ይላሉ። መንፈስ ቅዱስ ማክበር የቻለውን ሥጋ ወልድ ማክበር አይችልምን?
ሲባሉ በድፍረት አዎ ይላሉ። ወልድ የተዋሐደውን ሥጋ ማክበር አይችልም ካሉ ደግሞ ወልድን ከአምላክነት ክብሩ ማሳነሳቸው ነውና እጅግ
የከፋ የአርዮስ ክሕደት ይከተላቸዋል ማለት ነው። ስለዚህ ወልድን አምላካችን ነው በአምላክነቱም የተዋሐደውን ሥጋ ክቡር አምላክ
ዘለዓለማዊ ገዥ አደረገው ብሎ ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ በማለት ማመን ይገባል ማለት ነው።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፮/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment