Tuesday, October 9, 2018

መካነ ቅዱሳን ጣቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳም

 

※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፲፬/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
መካነ ቅዱሳን ጣቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በአዋበል ወረዳ እነቢ ቀበሌ የሚገኝ በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተ የአንድነት ገዳም ነው። ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ፲፰፻፷፰ ገዳማት መካከል በቀደምትነቱ ፮ተኛ ላይ የሚገኝ እንደኾነ የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ሊባኖስ አስታጥቄ አስረድተውናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በርጒም ሔሮድስ አማካኝነት ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ በዚች ቦታ ማረፏም ይነገራል። እመቤታችን አርፋበታለች የሚባለው ዋሻም ዛሬ የእመቤታችንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸበል ከሚገኝበት ቦታ በላይ ካለው ገደል ውስጥ የሚገኝ ነው። እመቤታችን በዚህ ዋሻ ባረፈችበት ጊዜ እጅግ ራባት። መልአከ መበሥር መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤልም አእዋፋትን የዓለም ጌታ እመቤታችን ድንግል ማርያም ርቧት ከዚዚያ ዋሻ ትገኛለችና የምትመገበውን ውሰዱላት ብሎ አዘዛቸው። አእዋፋትም የሚበላውን ፍራፍሬ እየወሰዱ በዋሻው ሞሉላት። እመ ብርሃንም ያንን ተመግባለች። ይህ ዋሻ እስከ ጣና ቂርቆስ ድረስ የሚዘልቅ እንደኾነ ይነገራል። አንድ በቦታው ሱባዔ የገቡ አባት ወደ ውስጥ ለስምንት ሰዓታት ያህል መሄዳቸውንና ሊጨርሱት አለመቻላቸውን መናገራቸውን የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ሊባኖስ ነግረውናል።
እመቤታችንም በዚህ ዋሻ የነበራትን ቆይታ ጨርሳ ስትሄድ ቦታዋን ባርካታለች። ለምለም ሁኚ፣ ደረቅ ነገር አይኑርብሽ፣ ለንስሐ የማይበቃ ሰው አይርገጥሽ፣ ቋንጃ ቆራጭ ሽፍታ ወንጀለኛ አይሸሸግብሽ ብላታለች። ቦታው ክረምት ከበጋ ለምለም ነው ደረቅ አይታይበትም። እመቤታችን እንዲህ ባለች ጊዜ ሦስት ምንጮች ፈልቀው ቦታውን የሚያጠጡ ኾነዋል። ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የሚታይ የሚገኝ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ምስክር ነው። አጠቃላይ በአረንጓዴ ዛፎች የተሞላው ይህ ቦታ ፲፪ ነጥብ ፭ ሄክታር ስፋት አለው።
ይህ ቦታ እመቤታችን ከባረከችው ወዲህ በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከግብጽ መልአኩ በራዕይ እየመራ በዚህ ቦታ ያሳረፋቸው አባ ዮሐንስ ገዳሙን መሥርተውታል። መልአኩም ለአባ ዮሐንስ ቦታህ ይህ ነው በዚህ ቦታ ብዙ የመንፈስ ልጆችን ትወልድበታለህ ቦታው የተባረከ የተቀደሰ ነውና አለው። አባ ዮሐንስም ዋሻ ፈልፍለው ቤተክርስቲያኑን ከዚያ ላይ አደረጉ። ገዳሙንም የወንዶችና የሴቶች ብለው ለኹለት ከፍለው መሥርተውታል። ዛሬ ድረስ ከወንዙ ባሻጋሪ የሴቶች ገዳም ይታያል። ዛሬ ግን ከወንዝ ወዲያ ማዶ ያለው የሴቶች ገዳም በደጀን ወረዳ በየትኖራ ቀበሌ ያለ ሲኾን የወንዶች ገዳም ደግሞ በአዋበል ወረዳ በእነቢ ቀበሌ ይገኛል። አባ ዮሐንስም ከብቃታቸው የተነሣ ወደ ሴቶች ገዳም ሲሄዱ ከምድር ለቀው ምድርን ሳይነኩ እንደነበር ይነገራል። በወንዶችና በሴቶች ገዳም መካከል ያለውንም ወንዝ ውኃ ሳይነካቸው ይሻገሩት ነበር። በወቅቱ እስከ ፳፻ የሚደርሱ መነኮሳት ይኖሩበት የነበረ ሲኾን ዛሬ ግን የሴቶች ገዳም የጸበል ቦታ ኾኗል የወንዶች ገዳም ደግሞ አንድ አባት አባ ሊባኖስን ብቻ የያዘ ነው። በገዳሙ የሚገኙት የጸሎት የትሕትና የአርምሞ የሥራ አባት አባ ሊባኖስ አስታጥቄ ብቻ ናቸው። ከዝንጀሮ ጋር እየታገሉ ገዳሙን እየጠበቁ የሚገኙት የበረኃው መናኝ አባ ሊባኖስ ብቻ ናቸው።
በግራኝ ወረራ ጊዜ የአቡነ ዜና ማርቆስ ደቀ መዛሙርት ከሰማይ የወረደ ጽላትና መስቀል ይዘው ከግራኝ የጥፋት ወረራ ሸሽተው ወደዚህ ገዳም መጥተው ተጠግተዋል። ግራኝም መነኮሳትን እየተከተለ መጥቶ ለንስሐ የማይበቃ ሰው ሊረግጣት አይችልምና ከላይ ከተራራው ላይ ኾኖ ድንጋይ እየፈነቀለ መጣል ጀመረ። እግዚአብሔርም ተርብ አስነሥቶ ግራኝን በተርብ አባረረው። የአቡነ ዜና ማርቆስ ደቀመዛሙርትም ለ፳፯ ዓመታት ያህል በዚች ቦታ ተቀምጠዋል። ከ፳፯ ዓመታት ቆይታ በኋላ ሀገሩ ሰላም መኾኑን ዓይተው ሊመለሱ ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመለሱ። በዚያም ሀገሩ ሰላም ኾኖ አገኙት። ቦታቸውን ሲያገኟትም ይህ ቤተእግዚአብሔር ነው። ያቦካነው ሊጥ በዚህ ነበር ብለው ሲጠጉ የተቦካው ሊጥ ከ፳፯ ዓመታት በኋላ እንደነበረ ኾኖ አግኝተውታል። ያንንም ጋግረው ተመግበዋል። ገድለ ዜና ማርቆስ ላይ እንደሚገኘው።
ሀገር ሰላም መኾኑን ካረጋገጡ በኋላ ከሰማይ የወረደውን መስቀል እና ጽላት ሊወስዱ ተመ
ለሱ። ኾኖም ግን እግዚአብሔር አልፈቀደላቸውም ነበርና ሊወስዱት አልቻሉም። ያደረጉት ነገር ቢኖር ጽላቱን መስቀሉን እና ይዘውት መጥተው የነበረውን አጽመ ቅዱሳን ከዋሻ ላይ ዘግተውት አትመውት መሄድ ነበርና ዘግተውት ሄዱ። ይህ የታተመው ቦታ እስካሁን ድረስ በቦታው የሚገኝ ምስክር ነው። ይህ የታተመው ዋሻም የሚጠበቀው በዘንዶ ነው።
ገዳሙ የተነገረለት ትንቢት የተሰጠው ቃል ኪዳን እየተፈጸመለት እንደኾነም አስረድተውናል። አንድ አባት ከዋልድባ መጥተው ፍልሰታ ማርያምን በዚህ ገዳም ሱባዔ አሳልፈው ነሐሴ ፲፮ መጥተው ከኪዳን በኋላ፡-
ይህ ቦታ ትንቢቱ እየተፈጸመለት ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ልኮኝ ነው ከዋልድባ ወደዚህ ቦታ የመጣሁ። ቦታው ለኹሉ ይታወቃል። ቤተክርስቲያኑ ይሠራል። ዋሻውም ይሠራል። ከሰማይ የወረደው መስቀልና ታቦትም ወጥቶ ይከብራል። መንገዱም ይሠራል። ብለው ነገሩኝ። እኔ ግን አላመንኋቸውም ነበር። ብዙ ባሕታውያን ነን ባዮች እንደዚህ ዓይነት ነገር ሊናገሩ ይችላሉና። ነገር ግን ይህን እንደተጠራጠርኩ አውቀው አባ አልተቀበሉኝም ተጠራጥረውኛል አይደል? ይህ የእግዚአብሔር መኾኑን እንዲረዱ እስከ መስከረም ፲፯ በአራቱም አቅጣጫዎች ፰ ጸበሎች ይፈልቃሉ። ይህ ምልክት ይኹንዎ አሉኝ እንዳሉትም በኹለቱ አቅጣጫ ዐራት ጸበሎች ፈልቀዋል የቀሩትም እንደሚፈልቁ ተስፋ አደርጋለሁ። መንገዱንም የሚሠሩ ሰዎች በኅዳር እንደሚጀምሩት አነጋግረውኛል። ቦታውንም ብዙ ሰዎች እያወቁት ነው። ብዙ ሰዎችም በጸበሉ እየተፈወሱበት ነው። ጸበሉ ተአምረኛ ጸበል ነው። ሲሉ አባ ሊባኖስ ይናገራሉ።
ቦታው ለንስሐ የማይበቃ ሰው አይረግጠውም። ከየትኖራ (ከደጀን ወደ ማርቆስ በሚወስደው መንገድ) በኩል ወደ ደቡብ ምእራብ አቅጣጫ ፳ ደቂቃ ብቻ ጉዞ የሚወስደው ገዳሙ ጥንታዊ የመኾኑን እና መንገዱ አስቸጋሪ ያለመኾኑን ያህል ብዙዎች አያውቁትም። በቦታው ድኅነት እያገኙበት ያሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር ላልፈቀደለት ለንስሐ ለማይበቃ ሰው ይህን ቦታ ሊረግጥ አይችልም ሲሉ አባ ሊባኖስ ያዩትን ተአምር ጨምረው ነግረውናል። አውቶቡስ ተኮራትረው ፷ ሰዎች ይህን ቦታ ሊያዩ ሕዳር ፳፩ አብማ ማርያምን አክብረው ሕዳር ፳፪ ወደዚህ ቦታ መጡ። ከአስፋልቱ ጀምረው እስከ መውረጃው ተራራ ድረስ ፷ ሰዎች ከመጡ በኋላ ቦታውን የረገጡ ፳፰ ሰዎች ብቻ ናቸው። ወደ ቦታው ይደርሳሉ የተባሉት ሲቀሩ፤ ወደ ቦታው አይደርሱም የተባሉት ደግሞ ወደ ቦታው ደርሰዋል። መንፈስ ርኩስ ያለበት ሰው በተለይ እንዲህ ኾኘ እንዲህ ተደርጌ ጨነቀኝ ጠበበኝ ወዘተ እያለ ለዚሁ ጉዳይ ከመጣ በኋላ ቦታውን ሳይረግጥ ይመለሳል ብለዋል አባ ሊባኖስ።
በዚህ ገዳም በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸበል በርካታ ሕሙማን ተፈውሰዋል። የስኳር በሽተኞች የኤድስ ሕሙማን መተት ጥንቆላ ዛር ወዘተ ፈውስ አግኝተውበታል። አባ ሊባኖስ እንደነገሩን በ፯ ቀን ጸበል ከኹሉ ደዌ እየዳኑ ይሄዳሉ። አንዲት ብቻ ናት ፲፬ ቀን የቆየችው ከHIV ለመፈወስ። ወደ ፵ የሚደርሱ የHIV ሕሙማን ድኅነት አግኝተዋል። የደብተራ መተት በ፫ ቀን ይወገዳል ያሉት አባ ሊባኖስ ከዚህ ቦታ ዛፍ መቁረጥ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። አንድ ሰው እኔ ለሥራ ጉዳይ ከገዳሙ ስወጣ አይቶ በሌላ መንገድ ገብቶ ምሳሩን ይዞ ለቀንበር የሚኾን ዛፍ ሊቆርጥ ሲል እረፍ አትቁረጥ የሚል ድምጽ ይሰማል ሲዞር ሰው የለም አሁንም ሊቆርጥ ሲል እንደዚያው ይለዋል። ሲዞር አሁንም ሰው የለም በመጨረሻ ልቁረጥ ብሎ በኃይል ሲያነዝር እግሩን ቆረጠው። ያ ሰውም ጮኸ እኔ ስመለስ ምንድን ነው ብየ ስጠጋ በምሳር ተቆርጦ አገኘሁት። እኔም ብዙ መከርኩትና ለሚያውቃቸው ሰዎች ስልክ ደውየ አስወሰድኩት። ኾኖም ግን ሊድን አልቻለም እንዲያውም እግሩ ኹሉ መስተት መትላት ጀመረ። በመጨረሻም ከጸበሉ ወስጄ እምነት ቀብቼ መልክአ ጊዮርጊስን ስደግም በሰማእቱ እርዳታ ቁስሉ እንደሌለ ኾነ ይላሉ አባ ሊባኖስ፡፡ አንድ ሰውም እንዲሁ ተደብቆ ከዚህ ገዳም እንጨት ቆርጦ ቤት ይሠራል፡፡ ከዚህ ገዳም የወሰደውን እንጨት አልፎ አልፎ በማድረግ ግድግዳውን ይገደግዳል፡፡ ቀኑ ሲመሽ ይህ ግድግዳ በእሳት ነበልባል ይታጠራል፡፡ ከዚህ ገዳም የተወሰዱት እንጨቶች በሙሉ በእሳት ነበልባል ተያያዙ፡፡ ሰው ኹሉ ይህን ተአምር ሲመለከት እጅግ ተደነቀ፡፡ አንተ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ያ ሰውም ከጣቤት ገዳም እንጨት ቆርጨ ነበር ያ ነው አለ፡፡ ከዚያም ቄስ መልካም የሚባሉ የእነቢ ካህን ያንን ነበልባል ያለበትን እንጨት ብቻ መርጠው እሳቱ ሳያቃጥላቸው ፍህም ሳይነካቸው አንድ ላይ ሰብስበው ለገዳሙ አስረክበዋል ብለውናል፡፡
በዚህ ገዳም እንስሳትንም መግደል አይፈቀድም፡፡ አንድ ሰው ከዚህ ገዳም ድኩላ አግኝቶ ገድሎ ሥጋዋን ለመብላት ተሸክሞ ከቤቱ ወሰዳት፡፡ ኾኖም ግን ያ ድኩላዋን የገደላት ሰው በድንገት ታሞ ወዲያኑ ሞተ ድኩላዋና ገዳዩ ሰው አብረው ተቀበሩ ሲሉም አክለውልናል፡፡ በዚህ ቦታ ሽፍታና ቀማኛ መሸሸግ እንደማይችል እመ ብርሃን ተናግራላታለች፡፡ አንድ ነፍሰ ገዳይ ሽፍታ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከሩቅ ሀገር ዐሥራ ኹለት ሰዎችን ገድሎ ወደ እነቢ ይመጣል፡፡ ከዚያም አንድ ቤት ያንኳኳና እኔ እገሌ ነኝ ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ምን ኾነህ መጣህ ይሉታል፡፡ የኾነውን ኹሉ ይነግራቸዋል፡፡ ሽፍታውም መሸሸግ ይፈልግና ወደ ጣቤት እደሚሄድ ይነግራቸዋል፡፡ እኒህ ሽማግሌ ግን ጣቤት የቅዱሳን ቦታ እንጅ የሽፍታ የወንበዴ የገዳይ ቦታ አይደለምና ወደዚያ መሄድ የለብህም ይሉታል፡፡ እርሱ ግን አሸፈረኝ ብሎዳ ጣቤት ይሄዳል፡፡ አንድ ቀን እንዳደረ ከተሸሸገበት ተይዞ ተሰቅሎ ተገደለ በማለትም ነግረውናል፡፡  እነቢ ለሚገኙ አንድ አባት በዚህ ጣቤት ወደሚባለው ገዳም ሄጀ ልሸሸግ ነው ይላቸዋል፡፡
ይህን ቦታ ማየት በጸበሉ መጠመቅ ትልቅ በረከት ትልቅም ፈውስ አለው፡፡ በተለይ ደግሞ ብቻቸውን ከላይ ታች ከታች ላይ በዚህ ሙዙን በዚያ ፓፓያውን በዚህ ሽንኩርቱን በዚያ ማንጎውን በዚህ በሬዎችን በዚያ ፍየሎችን በዚህ ላሞችን በዚያ ዝንጀሮዎችን አረ ስንቱን ነገር እንደሚሠሩት እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እርሳቸውን አንድ መደብ ሽንኩርት በማጠጣት አንድ ዝንጀሮ በማባረር ብናግዛቸው ዋጋችን በእውነት እጅግ ትልቅ አይደለምን፡፡ እርሳቸው ለወሬ ጊዜ የላቸውም ኹሌ ሥራ ላይ ጸሎት ላይ ናቸው፡፡ ቦታውን በሙዝ በፓፓያ በማንጎ በብርቱካን በሸንኮራ አገዳ ወዘተ በመሸፈን ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ለሚተካው መናኝ የተመቸ ቦታ ማስረከብን ዓላማቸው አድርገው ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ምንኩስና ምነና ብሕትውና እግዚአብሔር ገልጦላቸው በድብ ገብቷቸው በሕይወት የሚኖሩ አባት ናቸው፡፡ ገዳሙ እንዲለማ አባቶች በብዛት እንዲኖሩበት ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ደብረ ሊባኖስ ድረስ ሄደው የትራንስፖርት ወጭ ሸፍነው ወደ ዐሥራ ኹለት የሚደርሱ መነኮሳትን አምጥተው ገዳሙን ለማልማት ጥረት አድርገዋል፡፡ ኾኖም ግን ሥራው እና ጸሎቱ እየከበዳቸው አንድ አንድ እያሉ ኹሉም ገዳሙ ለቀው ሄደዋል ብለው አጫውተውናል፡፡ በዚህ ቦታ ትልቅ በረከት አለ፡፡ ትልቅ ቃል ኪዳንም አለ፡፡ በሕይወቴ እቆጭ የነበረው እዚሁ አፍንጫየ ሥር ያሉ ገዳማትን ባለማየቴ እና ባለማስተዋወቄ ነበር፡፡ እነሆ አምላክ ፈቅዶ ቦታውን ለማየት ሦስት ቀናትን በቦታው ለማሳለፍ የተፈላውን የሽንኩርት ፍል ውኃ ለማጠጣት በተአምረኛውና በፈዋሹ ጸበል ለመጠመቅ እናንተም ቦታውን እንድትመለከቱት ለማስተዋወቅ በቃሁ፡፡ ይህን ላደረገልኝ አምላክ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡
***ቦታውን ለመጎብኘት አቅጣጫ ለመጠየቅ ካስፈለገ የገዳሙን አስተዳዳሪ ብቸኛውን የገዳሙን አገልጋይ አባ ሊባኖስን በ+251931892213 ደውላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡
※※※※※※※※š³ ※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB

No comments:

Post a Comment