የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፯፡- ሥጋ ወደሙ ላይ ያላቸው የተጣመመ ትምህርት።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
«ወልደ
አብ» የተባለውን የክህደት እና የኑፋቄ መጽሐፍ ይዘው ሲከራከሩ የነበሩት አንዳንድ ቅብዐቶች ዛሬ መጽሐፋቸውን ፎቶ እያነሣሁ አብሬ
እያያያዝኩላቸው እያዩት ሌላ ነገር የምጽፍ ሲመስላቸው ሳይ ጊዜ ገረመኝ። «መጽሐፉ እኛን የቅብዐት አማኞችን አይወክልም» ካላችሁ
መልካም ነው አውግዛችሁ ለዩት። «የእኛ ነው» ካላችሁ ደግሞ መጽሐፋችሁ ላይ የተጻፈውን ነገር አምናችሁ መቀበል አለባችሁ ማለት
ነው። አምናችሁ ከተቀበላችሁ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እየሰጣችሁ መከራከር እንጅ «እኛ በፍጹም የማናምነውን ነገር አትጻፍብን»
ልትሉኝ አትችሉም። እኔ ገጽ ጠቅሼ የምጽፍላችሁ እኮ ከመጽሐፉ ላይ በቀላሉ እንድታዩትና እኔ የምጽፈው እናንተ ከያዛችሁት መጽሐፍ
ጋር አመሳክራችሁ የተለየ ከኾነ እኔ እንድወቀስበት እንድከሰስበት ነው።
በነገራችን
ላይ ቅብዐት አለ በሚባልባቸው አካባቢዎች ያሉ ምእመናን ይጾማሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይሰግዳሉ፣ ይመጸውታሉ። ይህን በሚገባ አውቃለሁ በሚገባም
አይቻለሁ። ለመስቀልም ለቅዱሳንም ስግደት እንደሚገባ ያምናሉ በተግባርም ይፈጽማሉ። ምክንያቱም «እምነቴ የእናቴ ነው የአባቴ ነው»
ከማለት ውጭ ጠለቅ ያለውን ምስጢር ስለማያውቁት ነው። ዛሬ የቅብዐት መምህራን ነን የሚሉ ገዳማውያኑን ጨምሮ ግን የቅብዐት መሠረተ
እምነቱ ምን እንደኾነ ጠንቅቀው ያውቁታል። ይህንን ትምህርት ለመስቀል ሲሰግድ ለቅዱሳን ሲሰግድ ለኖረ ምእመን እንዴት አድርገው
በአንድ ጀንበር ለቅዱሳን እና ለመስቀል አይሰገድም ይበሏቸው? ዘንድሮ በጥቅምት ወር ጒንደ ወይን ላይ ወጣቶችን ሰብስበው ስለቅብዐት
ሲያስተምሩ የነበሩት መምህራን «ወልደ አብ ማለት ግጸዌ ማለት ነው፤ ማውጫ ነው» ሲሉ ሰምቻለሁ። ግጸዌው ወይም ማውጫው «ወልደ
አብ» ለቅዱሳን አይሰገድም፣ ለመስቀልም አይሰገድም፣ ወልድ ፍጡር ነው፣ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ካለ ዋናው መጽሐፍ ምን ሊኾን
እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለኝም።
አሁን
እኔ የምጽፈውን እያነበቡ በውስጥ መስመር «እኔ ቅብዐት ነኝ ግን ለቅዱሳን ስግደት አይገባም፣ ለመስቀል ስግደት አይገባም፣ ወንጌል
በአሚን ብቻ ታድናለች፣ ወልድ ፍጡር ነው የሚል ትምህርት አልተማርኩም አላውቅምም» የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በእውነት አግዚአብሔር
በሚያውቀው ለእነዚህ ሰዎች በጣም አዝንላቸዋለሁ። ምክንያቱም «ቅብዐት ናችሁ» እያሉ በእልህ እና በትዕቢት እንዲነዱ እያደረጓቸው
ያሉት ቀሳጢ እና መናጢ «መምህራን» ናቸውና። ይህን ከ«ወልደ አብ» አግኝቼ የጻፍኹላችሁን ኑፋቄ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ቢሰብኩት
አንድ የቅብዐት ምእመን አያገኙም በዚህ እተማመናለሁ። ለዚህ ነው ውስጥ ውስጡን እንደ ሰደድ እሳት በኑፋቄ እየለበለቡ በእልህ የሚነዳ
ደጋፊ ለመሰብሰብ እንቅልፍ አጥተው በመሥራት ላይ የሚገኙት። እስኪ ዋናውን ምስጢር ጠይቁ። እስኪ የቅብዐት ሊቃውንትን ጠይቁ። በተለይ
ደግሞ መጽሐፉን ያሳተመችውን ገዳም ቆጋ ኪዳነ ምሕረትን ሄዳችሁ በትሕትና ጠይቁ። ወልደ አብ ገጽ እዚህ ላይ ለቅዱሳን ስግደት አይገባም
ይላል፣ እዚህ ገጽ ላይ ደግሞ ወልድ ፍጡር ነው ይላል፣ እዚህ ገጽ ላይ ደግሞ ወንጌል በአሚን ብቻ ታድናለች ብሏል፣ እዚህ ገጽ
ላይ ደግሞ ለመስቀል ስግደት አይገባም ብሏል ወዘተ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው አብራሩልን በሏቸው። በርግጥ አሁንም ቢኾን እውነታውን
ደብቀው በጾም እና በበዓልላት ልዩነታችን (በቀኖና) ሊደልሏችሁ እንደሚነሡ የታወቀ ነው።
ያም ኾነ
ይህ ግን ቅብዐት ነኝ ብሎ ስለቅብዐት እምነት አውቃለሁ ያለ ሰው የጻፈው መጽሐፍ «ወልደ አብ» እንደ እኔ አመለካከት የቅብዐቶችን
ሙሉ ትምህርት የያዘ ነውና ለእነርሱ ትክክል ነው። ትክክል ነው ብለው ከተቀበሉት ደግሞ በዚያ የተጻፈውን ኹሉ እምነቴ ነው ሊሉ
ይገባል ማለት ነው። ቀስ በቀስ ምእመኑን ካስለመዱ በኋላ መጽሐፉ ወደያዘው መሠረታዊ ክህደት ማምራታቸው አይቀርምና ከወዲሁ በስመ
ቅብዐት በእልህ የምትንቀሳቀሱ ወገኖቼ ቆም ብላችሁ በሰከነ እና በተማረ አስተሳሰብ ራሳችሁን ቃኙት።
ዛሬ የምንመለከተው
ቅብዐቶች ሥጋ ወደሙ ላይ ስላላቸው የተጣመመ ትምህርት ነው። ቅብዐቶች ወልደ አብ ገጽ ፪፻፴፬ ላይ «ሥጋውስ በሰውነቱ ተበልቶ በአምላክነቱ
ያድናል፣ ደሙም በሰውነቱ ተጠጥቶ በአምላክነቱ ያስተሠርያል» በማለት ሥጋ ወደሙ ላይ ያላቸውን ብዥታ ያለበት የደበዘዘ ትምህርት
ጽፈዋል።
ነገር
ላለማብዛት ስለሥጋ ወደሙ ወይም ስለቅዱስ ቊርባኑ ብዙ አልጽፍም ግን ሥጋ ወደሙ የሚያድነን የዘላለም ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምንወርስበት
እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዲመልሱልን መጠየቅ እፈልጋለሁ። በርግጥ እንደነርሱ አስተምህሮ ከኾነ ሥጋ ወደሙ በአምላክነቱ የሚያድነው
በሰውነቱ ተበልቶ እና ተጠጥቶ ነው። ይህ ሥጋ ወደሙ ላይ የመጣው የተጣመመ ትምህርት ሥግው ቃል ላይ ያለ ስህተታቸው ነው። ሥግው
ቃልን አንድ ነው በማለት ፈንታ በቃል ርስት ፈጣሪ በሥጋ ርስት ፍጡር እያሉ በተዋሕዶ አንድ የኾነውን ወደ ኹለት በመለያየት የጀመሩት
ስህተት ሥጋ ወደሙ ላይም መጣባቸው። ሥጋ ወደሙ መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው አማናዊ (እውነተኛ) መብልና መጠጥ ነው።
የቅብዐቶች አስተምህሮ ግን ሥጋ ወደሙ ለመታሰቢያነት ይደረጋል እንጅ
አማናዊ አይደለም ከሚሉት ከፕሮቴስታንቶች ትምህርት የሚርቅ አይደለም።
ቅብዐቶች
«ሥጋውስ በሰውነቱ ተበልቶ በአምላክነቱ ያድናል፣ ደሙም በሰውነቱ ተጠጥቶ በአምላክነቱ ያስተሠርያል» ሲሉ ሥጋ ወደሙ ሰውነቱ ለብቻው
አምላክነቱ ደግሞ ለብቻው የተከፈሉ ናቸው ማለታቸው ነው። ምክንያቱም «በሰውነቱ እንበላዋለን እንጅ በሰውነቱ አያድነንም፤ በሰውነቱ
እንጠጣዋለን እንጅ በሰውነቱ አያስተሠርይልንም» ማለታቸው ነውና። በሌላ አነጋገር ደግሞ «በአምላክነቱ አንበላውም አንጠጣውም ግን
በአምላክነቱ ያድነናል ያስተሠርይልንማል» ማለታቸው ነው። ታዲያ እንዲህ ከኾነ የተዋሕዶ (አንድ የመኾን) ምስጢር ወዴት አለ?
«በሰውነቱ ይበላል ይጠጣል በአምላክነቱ ግን አይበላም አይጠጣም» ብሎ መናገር የዕሩቅ ብእሲ ሥጋ እና ደም እንበላለን እንጠጣለን
ወደ ማለት አያደርስም ብላችሁ ነው? መለኮት የተዋሐደውን ነፍስ የተለየውን ሥጋ እና ደም እንበላለን እንጠጣለን ካላሉ በጣም ከባድ
ኑፋቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ፳፰÷፳፪ ላይ
«ዳግመኛም የሚያድን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ እና ደም እንደኾነ በከበረ ቊርባን እናምናለን። ቄሱ ሳያከብረው ኅብስት ወይን የነበረ
፤ ቄሱ ባከበረው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በላዩ ይወርዳል። ኅብስት ከመኾን የወልደ እግዚአብሔር ቃል አማናዊ ሥጋ ወደ መኾን ይለወጣል።
ወይኑም እንዲሁ ወይን ከመኾን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ አምላካዊ ደም ወደ መኾን ይለወጣል። ከሥጋው ጋር አንድ ኾኖ» ይላል።
ሊቁ አማናዊ
ሥጋ እና ደም ወደ መኾን ይለወጣል ካለን ታዲያ የክርስቶስ እውነተኛ ሥጋ እና ደሙ ሰውነት እና አምላክ ተብሎ የተከፈለ ነውን?
አይደለም በፍጹም ሎቱ ስብሐት! ታዲያ ክርስቶስን ከኹለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ፤ ከኹለት አካላት አንድ አካል ነው ካልን በሰውነቱ
የሚበላ በአምላክነቱ የሚያድን ነው ልንለው እንዴት እንደፍራለን? በሰውነቱ ይጠጣል በአምላክነቱም ያስተሠርያል ልንለውስ እንዴት
በሐሰት እንነሣሣለን? ሥጋው ሰውነቱ እና አምላክነቱ ተለያይተው የሚገኙበት አይደለም። ደሙም ሰውነቱ እና አምላክነቱ የተለያዩበት
አይደለም። ሥጋውም ደሙም ሰውነቱ እና አምላክነቱ ተዋሕደው አንድ የኾኑበት ነው። ስለዚህ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ እና ደም እንበላለን
እንጠጣለን እንላለን እንጅ ሰውነቱን ከመለኮቱ ለይተን በሰውነቱ ይበላል ይጠጣል በአምላክነቱ ያድናል ያስተሠርያል አንልም።
«ወልደ
አብ» እና «መሠረተ ሃይማኖት» የተሰኙት የቅብዐቶች መጻሕፍት በውስጣቸው ስለያዙት የነገረ ሥጋዌ ጠማማ አስተምህሮ በቀጣይ ክፍሎች
የምንመለከት ይኾናል። ከዚህ በኋላ በምንመለከታቸው ክፍሎች ውስጥ ነገረ ሥጋዌ ላይ ስላላቸው የተንሸዋረረ አስተምህሮ አልፈን አልፈን
ግን በጥልቀት የምንመለከት ስለኾነ እስካሁን የጻፍኹላችሁን ልዩነታችንን እንደ መግቢያ እንድትቆጥሩልኝ አሳስባለሁ።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፭/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment