፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ክርክሩም የተካሄደው በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የሚባሉት የመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ አይደሉም። የስም መመሳሰል ነው!) የተወከሉ ተዋሕዶዎች እና በሥነ ጊዮርጊስ የተወከሉ ጸጎች ነበሩ። እነዚህም ለየራሳቸው ባለቀረኝ (ረዳት) ነበራቸው። ባለቀረኝም ማለት «ይህ ቀረኝ» እያለ ተጨማሪ ጥያቄ የሚጠይቅ ማለት ነው። ባለቀረኞችም (ረዳቶችም) አለቃ ተክለ ሥላሴና መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ለተዋሕዶ፤ አለቃ ሀብተ ወልድ፣ አለቃ ውቤና አለቃ ቤተ ሌዊ ለጸጋ ወገን ነበሩ። በዚህ መሠረት ክርክሩ ተካሂዷል።
መጀመሪያ አፈጉባዔው አለቃ ኪዳነ ወልድ መጠየቅ ጀመሩ፡-
ጥያቄ፡-ሥላሴ በአካል ሦስት ናቸው?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎን ሥላሴ በአካል ሦስት ናቸው።
ጥያቄ፡- ሥላሴ በክብር ዕሩያን ናቸው አይበላለጡም?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎን አይበላለጡም።
ጥያቄ፡- ሥላሴ በከዊነ ህልውና ከመገናዘብ በቀር አንዱ አካል በአንዱ አካል አያድርም?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎ በከዊነ ህልውና ከመገናዘብ በቀር አንዱ አካል በአንዱ አካል አያድርም።
ጥያቄ፡- አንተ በራስህ አንቅተህ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ቃል ሥጋ በኾነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረበት መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የጸጋ ልጅ ኾነ እያልህ ታስተምራለን?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- ዝምምምም!
መልስ በዙር አምቤ እንግዳ እና በዋልድቤ እንግዳ፡- አዎን ወልደ ሥላሴ እንላለን። ዙር አምቤ እንግዳ እና ዋልድቤ እንግዳ ከጸጋዎች ጋር አብረው የመጡ የቅብዐት እምነት ተከታይ የኾኑ መነኮሳት ናቸው። አዎ ወልደ ሥላሴ እንላለን ብለው በድፍረት በጉባዔው መካከል በመናገራቸው ንጉሡ ዐፄ ዮሐንስን አስቈጣቸውና እንዲህ ካላችሁማ አራት አምላክ ማለታችሁ ነዋ ብለው ተቆጡባቸው። ዕጨጌ ቴዎፍሎስ ግን ጃንሆይ ዳኝነት መስማት ነው እንጂ መቈጣት አይደለምና አይቆጡ አሏቸው።
ከዚህ በኋላ ባለቀረኙ አለቃ ተክለ ሥላሴ «ቀረኝ» ብለው ተነሡ።
ጥያቄ፡- ሃይማኖት በብሉይ በሐዲስ ተነግሯል ተጽፏል?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎ ተነግሯል ተጽፏል።
ጥያቄ፡- በብሉይ ወልድየ አንተ ተብሎ ቀዳማዊ ልደቱ ወአነ ዮም ወለድኩከ ተብሎ ደኃራዊ ልደቱ ተነግሯል?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎ ተነግሯል።
ጥያቄ፡- በሐዲስም ፈነዎ ወልዶ ተብሎ ቀዳማዊ ልደቱ ወተወልደ እምብእሲት ተብሎ ደኃራዊ ልደቱ ተነግሯል?
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- አዎን ተነግሯል።
ጥያቄ፡- ቅድመ ዓለም ከአብ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን መወለዱን ካመንህ ኹለት ልደት ማለት ይህ ነዋ!
መልስ በሥነ ጊዮርጊስ፡- ዝምምምም!
ከዚህ በኋላ ኹለተኛው የተዋሕዶ ባለቀረኝ መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ «ቀረኝ» ብለው ተነሡ።
ጥያቄ፡- የንጉሥ ገንዘብ ተሰፍሮ ተቈጥሮ በመዝገብ ይጻፋል?
መልስ፡- አዎ ተቈጥሮ ተሰፍሮ በመዝገብ ይጻፋል።
ጥያቄ፡- በመዝገብ ከተጻፈው ያተረፈም ያጎደለም ይቀጣል?
መልስ፡- አዎን ያተረፈም ያጎደለም ይቀጣል።
ጥያቄ፡- የሥላሴ ገንዘባቸው ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቈጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል?
መልስ፡- አዎን የሥላሴ ገንዘብ ሃይማኖት ተሰፍሮ ተቈጥሮ በመጽሐፍ ተጽፏል።
ጥያቄ፡- ከመጻሕፍት ቃል ያተረፈም ያጎደለም ይቀጣል?
መልስ፡- አዎን ያተረፈም ያጎደለም ይቀጣል።
ጥያቄ፡- መጽሐፍ ነአምን ክልዔተ ልደታተ ብሎ በአኀዝ ወስኖ ነግሮናል?
መልስ፡- አዎን መጽሐፍ ነአምን ክልዔተ ልደታተ ይላል።
በዚህ ጊዜ ጠያቂው የተዋሕዶ ባለቀረኝ ከመጻሕፍት ቃል ያተረፈም ያጎደለም የሚቀጣ ከኾነ መጽሐፍ ጠንቅቆ ነአምን ክልዔተ ልደታተ ብሎ ወስኖ ከተናገረ አንተ ከዚህ አልፈህ ተርፈህ ሦስት ልደት እያልክ ስታስተምር ከተገኘህ ትቀጣልኛለህ ብለው ውርድ ነዙ።
ጸጋዎች ደግሞ በተራቸው በአለቃ ሥነ ጊዮርጊስ አማካኝነት ተጠየቅ አሉ። ዐፄ ዮሐንስ ግን ተጠየቁ ቀርቶ እርሱ (መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ማለታቸው ነው) ነአምን ክልዔተ ልደታተ ብሎ ቈጥሮ እንዳስረዳ አንተም ሦስት ልደት የሚል ገጸ ንባብ አምጣ አሉት። በዚህ ጊዜ ራስ መኮንን አባት ደጃች ወልደ ሚካኤል ተነሥተው ጃንሆይ ተዋሕዶዎች እየተፈራረቁ ሲጠይቁ እንደቆዩ ኹሉ ጸጋዎችም እየተፈራረቁ ሊጠይቁ ይገባል። ይህን ካላደረግን ንጉሡ አዳልተዋል ይባላል አሉ። ዐፄውም በዚህ መሠረት ጠይቅ ብለው አለቃ ሥነ ጊዮርጊስን ፈቀዱለት። አለቃ ሥነ ጊዮርጊስም ተጠየቅ ብለው ጥያቄያቸውን ጀመሩ።
ጥያቄ፡- እናትና ልጁን ልደት እንጂ ያገናኛቸዋል?
መልስ (መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ)፡- አባዬ አባዬ ያራዳ መምህር የርሷ ልደት በዘር በሩካቤ የርሱ እንበለ ዘር ምን አገናኛቸው።
በዚህ ጊዜ ጉባኤተኛው ኹሉ በጸጋዎች ላይ ሳቀባቸው። ነገሩ እንዳላማረ ሲያዩት ዐፄ ዮሐንስ ወልደ ዮሐንስ ኹለት ልደት ብሎ ከመጽሐፍ ምስክር እንዳመጣ ኹሉ አንተም ሦስት ልደት የሚል ገጸ ንባብ አምጣ አሉት። አለቃ ሥነ ጊዮርጊስም በደብረ ብርሃን ተአምረ ማርያም ተጽፎ ይገኛል አለ። ንጉሡም ከምታስተምረው ከአራቱ ጉባኤ ምስክር አጣህና ስለሃይማኖት ተአምረ ማርያም ትጠቅሳለህ? አሏቸው። እርሱም ከጉባኤ መጻሕፍትስ የለም አለ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ምኒልክ ነገሩ ይደርና እንመካከርበት አሉ። ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ዮሐንስም በዚሁ ሐሳብ ተስማሙ።
የሸዋው ንጉሥ ዐፄ ምኒልክ ለሚሲዮናውያኑ የነበራቸው አመለካከከት ለዘብተኛ ነበር። እርሳቸው ለሀገራችን ሥልጣኔን የማምጣት ሐሳብ እንጂ ለተዋሕዶ ሃይማኖት የዐፄ ዮሐንስን ያህል አይጨነቁም ነበር። ዐፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት የሚለው የታሪክ ጸሐፊው የተክለጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ የሚነግረን ይህንኑ ነው። የቦሩ ሜዳውን ክርክርም ከገጽ ፻፺፯ ጀምሮ ጽፎት ይገኛል። ከሠሩት ሥራ አንጻር ሲታይ ግን ለተዋሕዶ እምነት ያላቸው አመለካከት ለዘብተኝነት ያለበት አይመስልም። በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም በተካሄደው ከኢጣሊያ ጋር በተደረገው የአድዋ ጦርነት ላይ ሕዝቡን የቀሰቀሱበት መንገድ ያወጁት አዋጅ ለዘብተኛ የሚያስብላቸው አይመስለኝም። ያወጁት አዋጅ እንዲህ ይላል፡- «እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የኹሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ፣ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል። እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም ዓይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልምርህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝ:: ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ»(ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በተክለ ጻዲቅ መኩሪያ ገጽ ፪፻፳፮)
ኾኖም ግን መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ነገሩ አላምር ቢላቸው ንጉሠ ነገሥቱን በቆስጠንጢኖስ ዳኝነት ይዠወታለሁ ካህኑ አሐዱ አብ ቅዱስ ብሎ ከባረከው በኋላ መስዋዕት እንደማያድር ኹሉ ንጉሥም ካከራከረና ካመሳከረ በኋላ ፍርድ ሳይሰጥ አይበተንም ብለው ንጉሠ ነገሥቱን ጠየቁ። ዐፄ ዮሐንስም በጀ ብለው ይፈረድ አሉ። ኹሉም በአንድ ቃል ከመጽሐፍ ያላገኛችሁትን በማስመሰል ሰውን ኹሉ ስታስክዱ ኑራችኋልና ትቀጣላችሁ እያሉ በጸጋዎች ላይ ፈረዱባቸው።
ዐፄ ዮሐንስ ግን በአምላክ ላይ ያልተገባ ነገር ተናግረዋልና የአካል ቅጣትም ይገባቸዋል አሉ። ኾኖም ግን የተዋሕዶዎች አፈ ጉባኤ አለቃ ኪዳነ ወልድ ጃንሆይ ይህማ አይኾንም ከነዚህ የባሰ አርዮስ ክዶ ነበር ነገር ግን ተጋዘ ተሰደደ እንጂ አልተቀጣም እነዚህም የሚመለሱት አምነው ተገዝተው ይመለሱ አንመለስም ያሉት ግን ይጋዙ ይሰደዱ እንጂ አካል ቅጣት አይገባም አሉ። ዐፄ ዮሐንስ ግን የቅብዐት ተወካይ የነበሩትን ዙርአምቤ እንግዳንና ዋልድቤ እንግዳን አልምራቸውም እነዚህ ወልደ ሥላሴ ብለው በአምላኬ ላይ በድፍረት ተናግረዋልና ብለው እጅ እግራቸውን ምላሳቸውን አስቆረጧቸው። ዋልድቤ ወዲያው ሞተ ዙርአንቤ ግን ቆይቶ ንስሐ ገብቶ ሞቷል። ጸጋዎቹ እነአለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ግን ከዚህ በኋላ ኹለት ልደት እንላለን ብለው ምለው ተገዝተው ወደመጡበት ተመልሰዋል። አልፎንሱ ሜንዴዝ በሀገራችን የተከላቸው የቅብዐት እና የጸጋ እምነቶች በዚህ መልኩ ነው በተዋሕዶ ሊቃውንት መቃብር ተምሶ የተቀበሩት።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፮/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment