የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፲፩፡- እነርሱ «በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ» እኛ ደግሞ «በተዋሕዶ የባሕርይ ልጅ ኾነ» እንላለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የዛሬው ጦማር ረዘም ስለሚል ቀስ ብላችሁ ቅዳሜና እሁድን ጨምራችሁ ከፋፍላችሁ አንብቡት። ለንባብ
እንዲመቻችሁ አድርጌ ለሦስት ከፋፍየላችኋለሁ። እግዚአብሔር ከፈቀደ ሰኞ አዲስ ክፍል ይዤላችሁ እቀርባለሁ ማለት ነው። እናንተን
ላለማሰልቸትም በሚቀጥለው ሳምንት ልንቋጨው እንችላለን ፈቃዳችሁ ከኾነ ይቀጥል የምትሉ ከኾነ ግን ያው እንቀጥላለን ማለት ነው።
#ወልደ_አብ ገጽ ፪፻፲፪ ላይ «በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን
ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው፡፡ ምነው ይህስ
ቢኾን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ
በማይመስለው አይወልድም፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም
ነፍስ ሕያው የኾነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው በደመ ነፍስ ሕያው ያልኾነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ
ሕያው ያልኾነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልኾነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ
ተወለደ» ይላል፡፡ እስኪ ቃል በቃል እንመልከተው፡፡
v “በቅብዐት
የባሕርይ ልጅ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ
ልደት ተወለደ ማለት ነው”
ኹላችን እንደምናውቀው በከዊን አብን «ልብ» ወልድን «ቃል» መንፈስ ቅዱስን «እስትንፋስ» እንላለን፡፡
የአብ «ልብነት» ከወልድ «ቃልነት» ከመንፈስ ቅዱስም «ሕይወትነት (እስትንፋስነት)» አይቀድምም አይከተልምም፡፡ በተመሳሳይ የወልድ
«ቃልነት» ከአብ «ልብነት» እና ከመንፈስ ቅዱስ «እስትንፋስነት» አይይቀድምም አይከተልምም፡፡ የመንፈስ ቅዱስም «ሕይወትነት
(እስትንፋስነት)» ከአብ «ልብነት» ከወልድ «ቃልነት» አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ እስትንፋሳቸው
ነው ማለት የባሕርይ ሕይወታቸው ነው ማለት ነው፡፡ በቅብዐት እምነት ውስጥ ግን «ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን
በመላ ተቀብሎ» ይላሉ፡፡ እንግዲህ
«ወልድ» ማለት ልጅ ማለት እንደኾነ እናውቃለን፡፡ ልጅነቱም ከአብ የባሕርይ ልጅነት ነው፡፡ ይህ «ወልድ» የሚለው ስም አብ «አብ»
ከተባለበት መንፈስ ቅዱስም «መንፈስ ቅዱስ» ከተባለበት ጥንት ከሌለው ዘመን ስሙ አይቀድምም አይከተልምም፡፡ ስለዚህ «ወልድ» የሚለው
ስም የተገባው የኾነ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ አይደለም፡፡ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜስ «አማኑኤል» «ኢየሱስ» «ክርስቶስ»
ተባለ እንጅ ወልድ የተባለውስ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ «ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል» ከአብ በተወለደ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ
ይህ «ወልድ» የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ያገኘው (ገንዘቡ ያደረገው) ዛሬ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሳይኾን ጥንት ከአብ
ተወልዶ «ወልድ» ተብሎ በተጠራበት ጥንት በሌለው ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ «ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን
በመላ ተቀብሎ» ቢባል ክህደት ነው አንጅ እምነት አይባልም፡፡ ምክንያቱም «አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ ወልድም በአብና
በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነውና፤ መንፈስ ቅዱስም በአብና በወልድ ህልው ነውና» እንዳሉ የቀደሙ አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ፻፩ ÷፲ ላይ፡፡ ስለዚህ ይህ ህልውና
ቀድሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ያለ በመሆኑ እና ወልድ ከዚህ ህልውናው የተለየበት ጊዜ ስለሌለ «ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ» ቢባል ክህደት ነው፡፡ «በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን ነው
ቢሉ ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው» ማለትን ከማን
እንደተማሩት አይታወቅም፡፡ አብ በመለኮቱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ወለደው እንጅ ድኅረ ዓለምም ዳግመኛ በሰውነቱ ከእናት አልወለደውም፡፡
በሰውነቱስ ከአብ ዳግመኛ ተወልዶ ቢኾን ኖሮ «ወልደ አብ» መባል «ወልደ ማርያም» ከመባል በበለጠበት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅድመ
ዓለም «ወልደ አብ» የተባለው ድኅረ ዓለም «ወልደ ማርያም» ቢባል እኩል ነው አንጅ አይበላለጥም፡፡ እንዲያውም ሊቃውንቱ ሲያመሰጥሩ
«ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ» ይላሉ፡፡ ይህ ማለት «ወልደ አብ» መባሉ «ወልደ ማርያም» በመባሉ ታወቀ ተገለጠ ማለት
ነው፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ፶፫÷፲፫ ላይ «ወልድ ዋሕድ ከአብ መወለዱ እንዴት እንደኾነ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ
እንዴት እንደኾነ አትጠይቀኝ፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአብ ተወልዷልና ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው
ሰውም ነው» ይላል፡፡ ሊቁ «ለራሱ በአደረገው ተዋሕዶም ከድንግል ማርያም ተወልዷልና አምላክ ነው ሰውም ነው» አለ እንጂ «ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው» አላለም፡፡ ሊቃውንቱ
«ትስብእት የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ገንዘቡ አደረገ» ይላሉ። ይህ ማለት ለአካላዊ ቃል ሕይወቱ የነበረውን መንፈስ ቅዱስን በተዋሕዶ
ገንዘቡ አደረገ ሲሉን ነው። ዳግመኛ የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት ተቀበለ ማለት ግን መጀመሪያውኑ አካላዊ ቃል ሕይወት የለውም ነበር
ማለት ነውና የተሳሳተ ትምህርት ነው።
«ምነው ይህስ ቢኾን ወልድ በአብ ያልተወለደ በራሱ ያልተወለደ ስለምን በመንፈስ
ቅዱስ ተወለደ ቢሉ ይህስ ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው አይወልድም»
ይኼኛው ከመጀመሪያ ሐሳባቸው ጋር ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም ቅድም «ወልድ
በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው» ብለው ነበር አሁን ግን «ምነው ይህስ ቢኾን ወልድ በአብ ያልተወለደ»
በማለት ሐሳባቸውን ራሳቸው ያጣሉታል፡፡ በእርግጥ መጽሐፋቸው ሙሉውን እንደዚህ እርስ በእርሱ
የተጣረሰ ሐሳብ የሰፈረበት ነውና አይገርምም፡፡ እሽ ይኹን ብለን ብንቀበለው እንኳ «ወላዲ በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል እንጅ በማይመስለው
አይወልድም» ስላሉ መንፈስ ቅዱስን «ወላዲ» ያሰኛልና አንቀበለውም፡፡ አብን
«ወላዲ» «አሥራጺ» ፣ ወልድን «ተወላዲ»፣ መንፈስ ቅዱስን «ሠራጺ» ብንል እንጅ መንፈስ ቅዱስን «ወላዲ» እንዳንል እነሆ የታወቀ
የተረዳ ነው፡፡ «ወላዲ
በሚመስለው ሕይወት ይወልዳል» አልን እንጅ መቼ «ወላዲ»
ነው አልን ቢሉም ወላጅ የሚመስል ሕይወት የለም ብለን እንመልሳለን፡፡
v
«ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል እነሆ ዛሬ በደመ ነፍስ
ሕያዋን የሆኑ እንስሳ ከእንስሳ ይወለዳሉ በነባቢትም ነፍስ ሕያው የኾነ ሰው ከሰው ይወለዳል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብ ሕይወቱ ነው
በደመ ነፍስ ሕያው ያልኾነ ከእንስሳ በነባቢት ነፍስ ሕያው ያልኾነ ከሰው እንዳይወለድ፡፡ እንደዚህም ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው
ያልኾነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ»
በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን
ረቂቅ ልደት በእንስሳት እና በሰው ልጅ ልደት ልንመስለው እንዴት እንችላለን? ሰው ቢወለድ ከእናት እና ከአባቱ ዘር ነው እንጅ
በድንግልና አይደለም፡፡ እንስሳትም ከእንስሳት ቢወለዱ እንዲሁ በተራክቦ ነው እንጅ በድንግልና አይደለም፡፡ የወልድስ ከድንግል ማርያም
መወለድ በማክሰኞ ቀን ኅቱም ምድር ለታብቁል ባለው ቃል አብቅላ አፍርታ እንደተገኘች ያለ ነው፡፡ ሰው ከሰው የተለየ እንስሳን፤
እንስሳም ከእንስሳ የተለየ ሰውን ይወልዱ ዘንድ ፈጣሪ ተአምሩን ከገለጸ ይወልዳሉ፡፡ ይህንንም በተለያዩ ዜናዎች እየሰማን እና እየተመለከትን
ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ምሳሌ «ወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን በመላ
ተቀብሎ ከአብ የባሕርይ ልደት ተወለደ ማለት ነው» ለሚለው ማስረጃ
ሊኾን አይችልም፡፡ «እንደዚህም
ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልኾነ ከአብ አይወለድምና ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወለደ» ብለው ክህደታቸውን በአራት ነጥብ ይቆልፉታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሕያው ያልኾነ ከአብ ካልተወለደ
በቀዳማዊ ልደቱ አብ ወልድን የወለደው የባሕርይ ሕይወቱ ከኾነው መንፈስ ቅዱስ ሕያው ከኾነ በኋላ ነውን ቢሏቸው መልስ የላቸውም፡፡
በነገራችን ላይ «በግብረ መንፈስ ቅዱስ» የሚለውን የሊቃውንቱን ትምህርት በማጣመም ነው ለራሳቸው እየተጠቀሙበት ያሉ።
======================================================
#ወልደ_አብ ገጽ ፪፻፲፱ ላይ «ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም
የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ ልጅነት አገኘ፡፡
ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ኾነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ
ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱን በመላ ተቀብሎ
ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ
እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ
ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን
ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ
እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪» ይላሉ። እስኪ
አሁንም ቃል በቃል እንመልከት፡፡
«ይህ የጸጋ
ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደ አብ ቃለ
አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ ልጅነት አገኘ» ሥጋ ከፈጣሪው የጸጋ ልጅነትም
የለውም ነበር ማለታቸው አዳም ስለበደለ እና ጸጋ እግዚአብሔር ስለተገፈፈበት ነው፡፡ ኾኖም ግን እምቅድመዓለም የባሕርይ ልጅነት
ያለው መለኮት ሲዋሐደው የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ እና ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ ልጅነትንም አገኘ ብለው
ይደመድማሉ፡፡ በጣም ጥሩ ነው አሁን ላይ መለኮት ሲዋሐደው ሥጋ አምላክ ኾነ ክቡር ኾነ የቃል ገንዘብ ገንዘቡ ኾነ እና ወልደ አብ
ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ ማለት ነው፡፡ ይህ ነው በተዋሕዶ ከበረ ማለት። ነገር ግን ቀጥለው ይህንን ያፈርሱትና «ይህ ልጅነት
ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ኾነ» ከላይ «የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ
ልጅነት አገኘ» ብለው ነበር አሁን ደግሞ እንደገና ተመልሰው «በሥጋ ርስት
ልጅነትን የሚሻ ኾነ» ብለው የሚጋጭ ሐሳብ አስፍረዋል፡፡ ለዚህ ሐሳባቸውም የሚደግፍ
ማስረጃ ብለው ሰውን ለማደናገር ግዕዙን ብቻ ጠቅሰው አማርኛውን ሳያስቀምጡት አለፉ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግእዝን እንደማይችል ስለሚያውቁ
እንዲህ ይላልሳ እያሉ ያወናብዳሉ «እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱» ፍችውም «ሃብታም ሲኾን እናንተ በርሱ ድህነት ባለጠጋዎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ደሃ ኾነ»
የሚል ነው፡፡ እነርሱ ግን ሙሉውን ሳይጠቅሱ ቆርጠውታል፡፡ ሆኖም ይህ ጥቅስ «ቃል በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ» ለመሆኑ ምንም
ማረጋገጫ የለውም፡፡ ስለዚህም ማስረጃነቱን ለማወናበድ ካልተጠቀሙበት በቀር ምንም ማስረጃነት የለውም፡፡ ማስረጃ ሊኾን የማይችለውም
ነድየ የሚለው የሚስማማው ለሥጋ ነው እንጅ ለመለኮት አይደለምና ቃል ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት ተወግዷል፡፡
ስለዚህ የዚህ ማስረጃነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ቀጥለውም «ስለዚህ ከእምቅድመ
ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም» ይላሉ፡፡ በመቀጠልም «ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ
ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር» ብለው ወልድን ከአብ ያሳንሳሉ፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመግዛት አንድ ናቸው፡፡ ይህ
ምስጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ይህ የመግዛት አንድነት ወልድ ሥጋን በለበሰ ጊዜ አልተቋረጠም፡፡ ስለዚህ ወልድ የመግዛት አንድነቱን ይዞ
ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሥጋን ቢዋሐድ ሥጋ የመግዛት ሥልጣንን ከወልድ ያገኛል (ገንዘቡ ያደርጋል) እንጅ ከአብ አያገኝም፡፡
አስቀድመን እንደተናገርነው ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስ አሉና አብ ለወልድ የመግዛት ስልጣንን የሚሰጠው ወልድም የመግዛት
ስልጣንን የሚቀበል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመግዛት አንድነቱ የተለየበት ጊዜ ስለሌለ፡፡
አሁንም በግእዝ ጠቅሰው ለማወናበድ «ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ
እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰» ይላሉ ትርጉሙን እንመልከት፡- «እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፡- ክብሬን
ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም» የሚል ነው ቆርጠው ስላስቀሩት ነው እንጅ፡፡ እስኪ አስተውሉ ወገኖቼ! «ወልድስ በሰውነቱ
መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ
ባልሰጠውም ነበር» ለሚለው «ክብሬን ለሌላ ምስጋናየንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም”
ማስረጃ ሊኾን የሚችለው በምን ሂሳብ ነው፡፡ ወይስ ደግሞ ግእዝ ስለኾነ የተጠቀሰው ኹሉ ማስረጃ ይኾናል ማለት ነው፡፡
በመቀጠልም «መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡
አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው» ይላሉ፡፡ አብን ሰጭ ወልድን
ተቀባይ ልናደርገው እንዴት እንደፍራለን? ወልድስ ለመግዛት አብን እያስፈቀደ ነው ልንል እንዴት እንደፍራለን? ወልድ መንፈስ ቅዱስን
ዳግመኛ መቀበል ያስፈለገውስ እምቅድመዓለም የባሕርይ ሕይወቱ የኾነው መንፈስ ቅዱስ አልቆበት ነው ልንል ነውን? ወይስ ዳግመኛ መንፈስ
ቅዱስን ሊያድስ ነው ልንል ይኾን? ለዚህም ማስረጃቸው ያው የተለመደው ነው፡፡ «አኮ ዘይሁብ
እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮም ፫ ቁ ፴፬፡፡»
ትርጉሙም «እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ
አይሰጥምና አባት ልጁን ይወዳል ኹሉንም በእጁ ሰጥቶታል» የሚል ነው፡፡ አንድምታውን ስትመለከቱ «ከእግዚአብሔር አካል ዘእምአካል
ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ የመጣ እሱን እግዚአብሔርነቱን ያስተምራል፡፡ ሀብተ መንፈስን በልክ የሚሰጥ አይደለምና» ይላል ተመልከቱት
ኹላችሁም፡፡ ሌላው የጠቀሱት «ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪» የሚል ነው ትርሙም «ኹሉን ወራሽ ባደረገው» ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ኹለቱም ቦታዎች
ላይ ያስቀመጧቸው ጥቅሶች «ወልድ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ
አገዛዙን ክብሩን ሰጠው» የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማስረጃ ተብለው የተቀመጡት ኹሉ ማስረጃነት
የሌላቸው የመጽሐፉን ገጽ ብቻ ለመጨመር የተጻፉ እንደሆኑ ልብ ይሏል፡፡
======================================================
#ወልደ_አብ ገጽ ፻፹፪ ላይ «መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን ነው
ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ
አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ኾነው ማለት ነው፡፡ በእንተዝ ይትበሃል
ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል
እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን
ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯» ይላል ሙሉ ንባቡ፡፡ እንግዲህ እንደተለመደው ቃል በቃል ለማየት እንሞክር፡፡
«መንፈስ ቅዱስ
ቅብዕ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ
ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት
ኾነው ማለት ነው» በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ «መንፈስ ቅዱስ
ቅብዕ ኾነ» የሚል ትምህርት የለም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ካሉት ምስጢራት መካከል አንዱ «ሜሮን» ነው፡፡
በዚህ ሜሮን በሚባል ቅዱስ ቅብዐት ላይ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል መንፈስ ቅዱስ ያከብረዋል እንላለን እንጅ «መንፈስ ቅዱስ ቅብዐ
ሜሮን ነው» ብለን አልተማርንም፡፡ በሐዋ ሥራ ፪ ላይ እንደምንመለከተው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ አደረባቸው እንላለን እንጅ
«ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ሆኑ» አንልም ምክንያቱም የሚያድርባቸው በጸጋ ነውና፡፡ ስለዚህ ይህ አስተምህሮ የእኛ አይደለምና በአንዲት
ገዳማችን ስም እንዲህ ዓይነቱን ኑፋቄ ማውጣት ድፍረት ካልኾነ በቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ለዚህም የጠቀሱት ማስረጃ ያው እንደተለመደው
አንዱን ካንዱ ጋር በማቀላቀል የሚያስቀምጡት የተቆረጠ የመጽሐፍ ክፍልን ነው፡፡ “በእንተዝ ይትበሃል
ከመ ነሥአ መንፈሰ ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ቀብዓኒ በእንተዝ ሰበከ እንዘ ይብል
እስመ መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኃደረ ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ እንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ እን
ሳዊሮስ ዘአንጾ ሃ አ ክ ፱ ቁ፲፯” ይላሉ፡፡ የጠቀሱት የሃይማኖተ አበው ክፍል ምን እንደሚል በግእዝም በአማርኛም እንመልከተው እስኪ፡፡
በመጀመሪያ እነርሱ እዚህ ላይ ቁጥር ፲፯ ያሉት የቁጥር ፲፮ን የተወሰነ ክፍል እና የቁጥር ፲፯ን የተወሰነ ክፍል ቆራርጠው ነው፡፡
እንዲህ ይላል ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ ክፍል ፱ ቁጥር ፲፮ ግእዝ «ወሃሎ መንፈስ ቅዱስ ይጼልል መልዕልተ ማይ እምቅድመ ዝንቱ
ግብር ዘተፈጸመ በእንቲአነ በጥበብ ወሥርዓት ዘከመ ወጠነ ዳግመ ልሂኮተነ ወበእንተ ዝንቱ ይደሉ ይትበሃል ከመ ውእቱ ነሥአ መንፈሰ
ዚአሁ ዘተነግረ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ በእንተ ዝንቱ ቀብዓኒ» አማርኛ ትርጉም «እኛን ማደስን
እንደጀመረ በጥበብ በሥርዓት ስለእኛ ከተፈጸመው ከዚህ ሥራ (ከጥምቀት)
አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ ይሰፍ ነበረ ስለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ሕልው ነው ስለዚህ ነገር አዋሐደኝ
ሲል በኢሳይያስ የተነገረለትን የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስን እርሱ ገንዘቡ እንደአደረገ ሊነገር ይገባዋል» የሚል ነው፡፡ በወልድ
ህልው ሆኖ የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስ ሥጋ ገንዘቡ አደረገ ሲል እንዲህ አለ እንጅ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ አብ ከድንግል ማርያም በሥጋ ወለደው አላለንም፡፡ ቁጥር ፲፯ ግእዝ «በእንተዝ
ሰበከ እንዘ ይብል እስመ መንፈስ ዘዚአየ ዘህላዌየ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ወለምንትኑ ተሰመይኩ መሢሐ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ኮንኩ ሰብአ
ዝንቱ ውእቱ መድኃኒትነ ዝንቱ ውእቱ ፈውሰነ ዝንቱ ውእቱ ሐዋጺነ» ይላል አማርኛ ትርጉሙም «ስለዚህ በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚኾን መንፈስ
ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ ሰው ብኾን ነው እንጅ ያለዚያ ለምን ክርስቶስ ተባልኩ? የምንድንበት ይህ ነው፡፡ የሚፈውሰን
ይህ ነው የጎበኘን ይህ ነው» ይላል፡፡ እንግዲህ ኹላችሁ እንደምታዩት ቆራርጠው በጠቀሱት ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የባሕርይ
ሕይወት ኾነው የሚል ትርጉም አንድም ቦታ ተጽፎ አላገኘንም፡፡ «በባሕሬዬ ገንዘቤ የሚኾን መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ብሎ አስተማረ»
ይላል እንጅ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ተቀበልሁ አላለንም፡፡ ሰው ስለኾነ ይህንን ተናገረ ክርስቶስ የተባለው ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ
በኋላ ነው እና፡፡ ከተዋሕዶ በፊት ክርስቶስ አልተባለም ነበርና አሁን ግን ሲዋሐድ ክርስቶስ ተባለ፡፡ ስለዚህም ሰው በመሆኑ «በእኔ
ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በህልውናየ ጸና ለሥጋየ ገንዘቡ ኾነ» አለን እንጅ እነርሱ እንደሚሉት ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን
ተቀበልሁ አላለንም፡፡ «ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ» የሚሉት በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ወዴት ሄዶ ነው?
እዚህ ላይ ማስተዋል ያስፈልገናል ዋናው የክህደታቸው ምንጭ ይህ ስለኾነ፡፡ እኛ የምንለው መንፈስ ቅዱስ ለአብ እና ለወልድ የባሕርይ
ሕይወታቸው ነው ይህም ጥንት ከሌለው ዘመን ጀምሮ በሰው ህሊና በማይመረመር አምላካዊ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወልድ ከሥጋ ጋር
ሲዋሐድ ይህ የወልድ የባሕርይ ሕይወቱ የኾነው የመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ለሥጋ ገንዘቡ ኾነ ነው፡፡ እነርሱ የሚሉት ደግሞ ወልድ
ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ዳግመኛ መንፈስ ቅዱስን ሕይወቱ አደረገ ነው፡፡ እኛ የምንጠይቀው ያ በቃል ህልው ሆኖ ይኖር የነበረው
መንፈስ ቅዱስ የት ሄዶ ነው ዳግመኛ አከበረው የሚባለው? ወይስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ያልቃል ልትሉን ነው? ወይስ ደግሞ መንፈስ
ቅዱስ አርጅቶበት ማደስ ያስፈልገዋል ልትሉን ነው? እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን እንመራለን፡፡ ኢሳ ፷፩÷፩ ላይ ያለውን ቃል
ሉቃ ፬÷፲፯ ላይ ይተረጉሙታል፡፡ ሳዊሮስም ሃይማኖተ አበው ላይ እሱን ይተረጉማል ሳዊሮስ ክ ፱ ቁ ፲፰ እንዲህ ይላል «ስለዚህ
ነገር ከዚህ በኋላ ለድኆች የምሥራች እነግራቸው ዘንድ ያዘኑትን አረጋጋቸው ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ ዕውሮች
ያዩ ዘንድ ስለዚህ ላከኝ አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ ኾነ መባሉ ቃል ሰው ስለኾነ ነው ሰውማ ባይኾን ኖሮ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር
ህልው እንደኾነ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ገንዘቡ ነውና እንደምን ገንዘቡ ኾነ ይባላል አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው መሆኑን እንደተናገረ» ሳዊሮስ እዚህ ክፍል ላይ የተረጎመው ኢሳ ፷፩÷፩
ላይ ያለውን ቃል ነው፡፡ እንግዲህ ሳዊሮስ በግልጽ እንዳስቀመጠልን መንፈስ ቅዱስ በወልድ ህልው ሆኖ ይኖራል ያ ህልው ሆኖ የሚኖረው
መንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ለሥጋ ገንዘቡ ኾነ ማለት ነው እንጅ ዳግመኛ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚል ትምህርት
አላስተማረም እንዲያውም እዚሁ ክፍል ቁጥር ፲፱ ላይ ሊቁ ሳዊሮስ እንዲህ ይላል «በዚህም ግብር ተዋሕዶ ጠፍቶ ከነቢያት እንደ አንዱ
አልኾነም መንፈስ ቅዱስ ያደረበት አይደለም» ይላል፡፡ ስለዚህ የት ቦታ ላይ ነው ወልድ መንፈስ ቅዱስን ዳግመኛ ተቀብሎ አብ ከማኅጸነ
ማርያም ወለደው የሚለው ትምህርት ያለው? ሉቃ ፬÷፲፯ ላይም ወንጌላዊው ሉቃስ ‹‹ኢሳ ፷፩÷፩›› ያለውን ወስዶ አስቀምጦታል፡፡
ትርጓሜ ወንጌሉ እንዲህ ይላል፡፡ «ዘይብል መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ» መጽሐፉን ገልጾ ሳለ ማስተማር በእኔ
ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሐደኝ እግዚአብሔር አንድም ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተርጉሞታል መንፈስ ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ
ብሎ የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ በእኔ ህልው ነው ወዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ነዳያንን አስተምራቸው
ዘንድ ላከኝ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ እነሱ ለጻፉት ኑፋቄ ይህ ማስረጃ ተብሎ ሊጻፍ አይገባውም ነበር ነገር ግን ሰውን ወደ
ጥርጥር ለመክተት ተጠቅመውበታል፡፡ «ቀባ» የሚለው ቃል በርካታ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ተመልክተናል እዚህ ላይ ቀብዓኒ ያለውን
ያዋሐደኝ ብለው ነው የተረጎሙት፡፡ ስለዚህ ምናልባት ቅብዐቶች የራሳቸው ሃይማኖተ አበው የራሳቸው የትርጓሜ መጻሕፍት ሊኖሯቸው ይችል
ይኾናል እንጅ የእኛ መጻሕፍት ግን «መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ኾነ ማለት ምስጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ
ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት ማለት ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ
መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ኾነው ማለት ነው» ብለው አናገኛቸውም፡፡
ምክንያቱም ኑፋቄ ነውና! አባቶቻችንስ የማይመረመረውን መለኮት መርምሮ በማይደርሰው ኅሊናችን እንመረምር ዘንድ እንደማይገባ አስተማሩን
እንጅ በድፍረት የመሰለንን ነገር ለመለኮት እንቀጽል ዘንድ አላስተማሩንም፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ፶፫÷፭ ላይ «ተመርምሮ
የማይታወቅ ከኾነስ አለመመርመርን ማወቅ ይገባናል፡፡ ድንቅ ምንድን ነው? የባሕርዩ ሥራ ነው እንጅ ድንቅ እርሱ ከኾነ ድንቅ የኾነ
እርሱም ኹልጊዜ ድንቅ በመባል የሚኖር ከኾነ እውቀትን ድንቅ ድንቅ ሥራ በሚሠራ ለፍጥረቱ ኹሉ ገዥ ለእርሱ ተዉ» ይላል፡፡ ስለዚህ
የማይመረመረውን መለኮት እንመረምራለን እያሉ ክህደታቸውን ለሚተፉ የቅብዐት ምንፍቅና አራማጆች መልእክታችን ቆም ብላችሁ አስቡ የሚል
ይኾናል!
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፩/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment