Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፲፮



የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት- እነርሱ «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ» እኛ ደግሞ «ለሊሁ ቀባዒ ወለሊሁ ተቀባዒ ወለሊሁ ቅብዕ » እንላለን
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ቅብዐቶች «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚል የአካላት የግብር ስም አላቸው፡፡ ይህም የአካላት የግብር ስም አንዱ ለአንዱ መኾን ይችላል፡፡ መፋለስ እና መቀላቀል አለበት፡፡ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ የሥላሴ የግብር ስም ተፋልሶ አለበት፡፡ አብን ቀባዒ ወልድን ተቀባዒን መንፈስ ቅዱስን ቅብዕ ናቸው ማለት በክብር አንድ እንዳልኾኑ የሚያሳይ ነው። ቀባዒ ማለት አክባሪ ተቀባዒ ማለት ከባሪ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ማለት ክብር ማለት ነውና። አብ አካላዊ ቃልን በመንፈስ ቅዱስ ክብርነት አከበረው የሚል ጠማማ ትምህርት የያዘ ነው። አንዱን አካል አክባሪ አንዱን አካል ከባሪ አንዱን አካል ደግሞ ክብር በማድረግ አንዲትን የሥላሴ ክብር ሲከፋፍሏት ይታያሉ።
እኛ አብ ወላዲ አሥራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ የሚለውን የሥላሴ አካላዊ ግብር ነው የተማርነው። ይህ አካላዊ ግብር አይፋለስም አይቀዳደምም። አይፋለስም ማለት የአብ ግብር ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶ አይነገርም፣ የወልድ ግብርም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶ አይነገርም፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብርም ለአብና ለወልድ ተሰጥቶ አይነገርም ማለት ነው። አይቀዳደምም ማለትም የአብ መውለድ ማሥረጽ፤ የወልድ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ መሥራጽ አይቀድምም አይከተልም ማለት ነው።
በቅብዐቶች ዘንድ ይህ የሥላሴ አካላዊ ግብር በአፍ ደረጃ የታመነ ቢኾንም ምስጢሩ ላይ ግን ችግር አለ። ይህን የሥላሴ አካላዊ ግብር ከመናገር ይልቅ «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ»  የሚል የአካል ይኹን የሥልጣን ይኹን የኩነት ይኹን የምን ይኹን የምን የማይታወቅ ግብር ለሥላሴ ቀጽለው በአምላክ ላይ ያላቸውን ተሳልቆ ያሳያሉ። የሚገርመው ነገር «በመለኮት ኹሉም ቀባዒ ናቸው በሥጋ ግን አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ናቸው» የሚለው ትምህርታቸው ነው። በመለኮት ኹሉም ቀባዒ ማለትም አክባሪ ናቸው ብለው ካመኑ ታዲያ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ሥጋውን ቀባው ወይም አከበረው ማለት ለምን ተሳናቸው? እኛ ግን ወልድ ቀባዒ ነው ራሱም ተቀባዒ ነው ራሱም ቅብዕ ነው እንላለን። ይህም ማለት ወልድ በራሱ ክብር የተዋሐደውን ሥጋ አከበረው ማለታችን ነው። ለዚህም ነው በተዋሕዶ ከበረ ማለታችን።
ለዚህም ማስረጃ አለን። ሊቁ ቄርሎስ ስምዐት ፻፳፬÷፴፬ ላይ «ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ …ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ..» ይላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እነርሱ የማይቀበሏቸው ነገር ግን ምእመናንን ለማታለል ሲሉ ያላሉትን «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ፤ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ» የሚሉ ደገኛ መጻሕፍት ናቸው በማለት ከሚጠቅሷቸው መድሎተ አሚን እና ከዋዜማ ያገኘሁትንም ማስረጃ እዚህ ላይ ባቀርብ ደስ ይለኛል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ዋዜማ፣ ገጽ ፻፴፩ ላይ «አባ ቄርሎስም ወደ ጎንደር በገባ ጊዜ የጎንደር ሊቃውንት ክርስቶስን በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የጸጋ ልጅ በማለትና የባሕርይ ልጅ በማለት እንደ ተለያዩ ሰምቶ ኹለቱም ወገኖች ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ እንዳይሉ አወገዛቸው። ወዲያውም እርሱ ራሱ ወልድ ቅብዕ ነው። ቀቢና ተቀቢም ራሱ ነው ብሎ ለጎንደር ሊቃውንት የማይስማማ ትምህርት አስተማረ»
ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ዋዜማ፣ ገጽ ፻፴፬ ላይ «አባ ሰላማም ጎንደር እንደ ደረሱ ከእርሳቸው አስቀድሞ እንደ ነበረው እንደ አባ ቄርሎስ ወልድ ቅብዕ ብለው አስተማሩ። መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ የሚሉትን የጸጋ ልጆችንና ቅብዐቶችን ግን ገዘቱ»
መድሎተ አሚን ገጽ ፻፸፱-፻፹ ላይ «የኢትዮጵያ ሃይማኖት በሕግ ተወስኖ ጳጳሳቱ ክህነት የሚሰጡበት ንጉሡ ተቀብቶ የሚነግሥበት ሕዝቡ ተስማምቶ የሚኖርበት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኹለት ልደት በተዋሕዶ ከበረ ማለት እንደነ በሕገ መንግሥት ተጽፎ አንዱን ክፍል አንቀጽ ይዞ ይገኛል»
መድሎተ አሚን ገጽ ፻፺ ላይ «ወልድ ቅብዕ ማለትና መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ማለት በተዋሕዶ የባሕርይ አምላክ ነ ማለትና በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ነ ማለት መገናኘት የማይቻላቸው ልዩ ልዩ ነገሮች መናቸውን ሊረዱ አልቻሉም»
መድሎተ አሚን ገጽ ፻፺፩ ላይ «እንዲያውም በጠቅላላው ዛሬ በኢትዮጵያ ኹሉም ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኹለት ልደት በተዋሕዶ ከበረ የሚል ነው እንጂ ከዚህ ወጥቶ አንድ አካል ኹለት ባሕርይ በቅብዐት የጸጋ ልጅ በቅብዐት የባሕርይ ልጅ የሚል አይገኝም»
በአጠቃላይ «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ብሎ ማመን የሚከተሉትን ስህተቶች ያመጣል።
፩ኛ. የአካላት ግብር ስም ኹለት ጊዜ እንደተሰጣቸው ያሳያል፡፡ ዘመን ሳይቆጠር ቀድሞ «አብ ቀባዒ ወልድ ቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቀባዒ» ድኅረ ዓለም ወልድ በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ደግሞ «አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ» ሆኑ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የግብር መቀዳደምን እና መለዋወጥን ያሳያል፤
፪ኛ. ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ምእራፍ ፪ ቁጥር ፻፶፬ ላይ «ለአጽንዖተ ክልዔሆሙ፤ አብን መንፈስ ቅዱስን በጥንተ ስማቸው ለማስጠራት በጥንተ ግብራቸው ለማጽናት» የሚለው ትምህርት ተቀባይነትን አላገኘም ማለት ነው፡፡
፫ኛ. አብ ከቀባዒነት ወደ ቀባዒነት፤ ወልድ ከቀባዒነት ወደ ተቀባዒነት፤ መንፈስ ቅዱስ ከቀባዒነት ወደ ቅብዕነት እንደተለወጡ የሚያሳይ መሆኑ፡፡ ይህ ደግሞ ወልድን ክብር አልባ ነው ያሰኛል። ምክንያቱም ክብር አለው ካሉ በራሱ ክብር የተዋሐደውን ሥጋ አከበረው ባሉ ነበርና።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፯/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment