Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፮



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የቅብዐት አስተምህሮ በየዘመናቱ
==================================
የቅብዐት እምነት መሠረቱ ካቶሊክ ቢኾንም ወደ ሀገራችን ሲገባ ግን እንደ ሀገራችን ወግና ባህል ተቀዶ የተሰፋ ነው። ይህንንም ከቦሩ ሜዳ ክርክር በፊትና ከቦሩ ሜዳ ክርክር በኋላ ብለን ብንመለከተው መልካም ይኾናል።
============================
ቅብዐትና ጸጋ በአልፎንሱ ሜንዴዝ ከተተከሉ በኋላ ወንድምን ከወንድሙ ወላጅን ከልጁ ሲያለያዩ ደም ሲያፋስሱ እንደቆዩ ቀደም ባሉ ክፍሎች ተመልክተናል። ሀገራችን ከተተከሉ ወዲህ ስላላቸው እንቅስቃሴ እና ባህል በጥቂቱ እንበል። ከቦሩ ሜዳው ክርክር በፊት ሦስት ዓይነት የቅብዐት ባህሎች ጎልተው ወጥተዋል። ይህንንም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ ፯፻፹ ላይ እንዲህ ይጽፉታል።
መጀመሪያ በፋሲል ዘመን የተነሡት እነዘኢየሱስ መጽሐፍ «አንደየ ርእሶ» ይላልና «ቃል በተዋሕዶ ዜገ ከሥጋ ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን አጣ ለቀቀ ሲቀባ ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሶ በሰውነቱም በአምላክነቱም አንድ ወገን በቅብዐት የባሕርይ ልጅ ኾነ ብለዋል» ይላሉ። በፋሲል ዘመን የነበሩት የመዠመሪያዎቹ የዚህ የክሕደት አስተምህሮ ጠንሳሾች ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን ከዐይን ጥቅሻ በምታንስ ጊዜ ስለዜገ ማለትም ስለደሐየ፣ ስለ አጣ፣ ስለተቸገረ ወደ ቀደመ ባሕርይ ክብሩ (ወደ አምላክነቱ) ለመመለስ ቅብዐት ያስፈልገዋል ባዮች ናቸው ሎቱ ስብሐት። የዛሬዎችም በመጽሐፋቸው «ወልደ አብ ገጽ ፪፻፲፱» አጣ፣ ደሐየ፣ ተቸገረ (ዜገ) ሲሉ «ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ኾነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ኾነ» ብለዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን ሲገልጹ ወልደ አብ ገጽ ፻፷፮ ላይ  « መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ ኾነ» በማለት ጽፈዋል። በተጨማሪም ወልደ አብ ገጽ ፪፻፲፱ ላይ «ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር» በማለት አብን ሰጭ ወልድን ደግሞ ተቀባይ መንፈስ ቅዱስን ስጦታ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡
ስለዚህ ነው እንግዲህ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን ጠቀመው ረባው ማለታቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ባይወለድ ኖሮ ወልድ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ መግዛት ማዘዝ አይችልም ነበር ማለታቸው ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገዋል ማለታቸው ነውና ከመጀመሪያዎቹ የቅባት ክፍል ጋር አንድነት አላቸው፡፡
ወልደ አብ ገጽ ፪፻፴ ላይ ደግሞ ለመለኮት የማይቀፀል ቃል እንዲህ ብለው ቀፀሉ «በዚህም በባሕርይ ልጅነቱ እኛ ብቻ ተጠቅመንበት አልቀረንም እርሱም ተጠቀመበት እንጂ» ይላሉ። ወልድ ምን ተጎድቶ ምን ጎድሎበት ነው በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው፡፡ ይባስ ብለው ገጽ ፪፻፴፫ ላይ «ቅብዐቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ እንደአስተካከለው...» ብለው ወልድን ከባሕርይ ክብሩ ዝቅ ሲያደርጉት ይስተዋላሉ፡፡
በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው በእውነት ምን ጎድሎበት ይኾን? ሃይማኖተ አበው ዘኤፍሬም ፵፯ ግን እንዲህ ይላል «የድንግልን ሥጋ መረጠ ሰው መሆኑን ሊያስረዳ ፍጹም አካሉን በማኅጸኗ ፈጠረ ከእርሷ ሥጋን የተዋሐደ እጠቀምበታለሁ ብሎ አይደለም» ይላል፡፡
=============================================
ኹለተኛው ባህላቸው በአንደኛው ዮሐንስ ዘመን የተነሡት እነ አካለ ክርስቶስ ያመጡት ነው። እነዚህ ደግሞ «ዜገ» የሚለውን የእነ ዘኢየሱስን ትምህርት ነቅፈው አጸይፈው መጽሐፍ «እስመ ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ ይላልና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል ኾነ እንጂ የአምላክነት ክብር አላገኘም። ሲቀባ ግን ክብር ተላልፎለት ተፈጥሮ ተገብሮ ጠፍቶለት በቅብዐት የባሕርይ ልጅ የባሕርይ አምላክ ኾነ» ብለዋል። እነዚህ ከመዠመሪያዎቹ የሚለዩት መቀባትንና መለወጥን ለሥጋ ብቻ መስጠታቸው ነው እንጂ በሌላው ኹሉ አንድ ናቸው።
የዛሬዎቹም ወልደ አብ ገጽ ፪፻፴፪ ላይ «ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብዐት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ኹለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጂ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም» ይላሉ፡፡ ተዋሕዶ ለእነርሱ ኹለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ብቻ ያጸና ነው እንጂ የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት እንዳልተወገደ ነው የሚያምኑት፡፡
እኛ ደግሞ ኹለትነት ጠፍቶ አንድነት ሲጸና የሥጋ ንድየት በቃል ባዕልነት ተወግዶ ቅድምና የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ኾነ እንላለን፡፡ ሰው አምላክ ኾነ አምላክ ሰው ኾነ ማለት ስለዚህ ነው፡፡ የሥጋ ገንዘብ (ከኃጢአት በቀር) ለመለኮት የመለኮትም ገንዘብ ለሥጋ ገንዘቡ ኾነ የምንለው በተዋሕዶተ መለኮት ነው እንጂ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፡፡
================================================
ሦስተኛው ባህላቸው በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን የተነሡት እነአለቃ ጎሹ በቅብዐት ብቻ ማለትን ነቅፈው «መጽሐፍ በኹለቱም ኹሉ በተዋሕዶ ከበረ በቅብዐት ከበረ ይላልና ቅብዐት ያለተዋሕዶ ተዋሕዶም ያለቅብዐት ብቻ ብቻውን አያከብርም በተዋሕዶና በቅብዐት በአንድነት የአምላክነት ክብር ከብሮ የባሕርይ ልጅ ኾነ» ብለዋል።
በዚህ ዘመን ያሉት የቅብዓት እምነት አራማጆችም ይህንን ደግፈው ይታያሉ፡፡ ወልደ አብ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ ፻፳፮ ላይ « ተዋሕዶ ተፈጠረ ሳይዋሐድ አልተፈጠረም፡፡ ተዋሕዶ ሳይፈጠር አልቆየም፡፡ ሲዋሐድ ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ተዋሕዶ ቀደመ ባሉ ጊዜ ከቅብዓትም ተዋሕዶ ቀደመ ማለት ይኾናል» በማለት በተዋሕዶ እና በቅብዐት እንደከበረ ይናገራሉ፡፡
==================================================
እነዚህ ሦስቱም ባህሎች ኑፋቄዎች ናቸው። እነዚህን ሦስቱንም የቅብዐት ባህሎች ወንድማቸው ከኾነ ጸጋ ጋር በአለቃ ኪዳነ ወልድመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ» ከተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ የተለዩ ናቸው) በተወከሉ የተዋሕዶ ሊቃውንት ቦሩሜዳ ላይ በነበረው ጉባኤ በ፲፰፻፸፰ . አርቀው ቀብረዋቸዋል። ኾኖም ግን ከብዙ ዓመታት በኋላ አካል አግኝተው ነፍስ ዘርተው ተነሥተዋል።
=============================
ከዚህ በኋላ በድብቅ ውስጥ ውስጡን በግል ደረጃ ካልኾነ በቀር ራሳቸውን ይፋ አድርገው ጎልተው አልወጡም። በክርክሩ ወቅት በመሸነፋቸው ዳግመኛ ሦስት ልደት ላይሉ ምለው ተገዝተው ስለነበር የተለቀቁት በፍርሐት ውስጥ ስለነበሩ በአደባባይ መውጣት አልቻሉም ነበር። ኾኖም ግን አጋጣሚውን ተጠቅመው በ፲፱፻፹፰ . በተሐድሶ መናፍቃን ቀስቃሽነት አካል ነሥተው ነፍስ ዘርተው ከተቀበሩበት መቃብራቸው ብቅ ለማለት በቅተዋል።
መነሻው ገና ታህሳስ ፳፰ ይከበር ሰለነበር ነው። ለምን ታህሳስ ፳፰ ገና ይከበራል ማክበር ያለብን ታህሳስ ፳፱ ብቻ ነው በሚል ክርክር ተነሣ ግጭት ተፈጠረ። ይህንን ክፍተት ተጠቅመው የተሐድሶ መናፍቃን ጉዳዩን ጉዳያቸው አድርገው ያዙት። መምህር ወልደ አብርሃም በምስጢረ ተዋሕዶ መጽሐፋቸው ገጽ ፵፮ ላይ እንደገለጡት ጥላሁን መኮንን የተባለ የተሐድሶ መናፍቅ «ከተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውጡ ጳጳስ እኔ ከእስክንድርያ አመጣላችኋለሁ» እንዳላቸውና በወቅቱ የቅኔ መምህር የነበሩት አሁን ግን በአንድ ገዳም ውስጥ የሚኖሩት (እንደ እኔ ገዳሙ ቆጋ ኪዳነ ምሕረት መሪጌታውም የኔታ ሄኖክ እንደኾኑ አስባለሁ) ቅብዐትን ከተቀበረበት ቆፍረው እንዲያወጡት እና ነፍስ እንዲዘሩበት ለሦስት ወራት ያህል የተሐድሶ ሥልጠና በመናፍቃኑ ሰልጥነዋል። በዚህም መሠረት በቅብዐት ስም ወረዳ ቤተክህነት እስከመክፈት የዘለቀ ሥራ ለመሥራት ቻሉ። ኾኖም ግን በመንግሥት ዘንድ እንዲህ የሚባል እምነት እውቅና ስላልነበረው ወዲያውኑ እንዲዘጋ ተደርጓል።
ከዚህ በኋላ ፲፱፻፺፬ . «ቅብዐት» እንደ አንድ ሃይማኖት ተቈጥሮ በመንግሥት ዘንድ ዕውቅና እንዲሰጠው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር «ጥንታዊት ኦርቶዶክስ ቅብዐት» በሚል ስም እውቅና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ይኸው ጥያቄያቸውም ግንቦት ፲፱፣፳ እና ፳፩ ቀን ፲፱፻፺፬ . በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተቃዋሚ ካለ እንዲቀርብ ተብሎ ታትሞ ወጣላቸው። ይህንን የተመለከተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስም ተቃዋሚ ኾኖ ስለቀረበ (በዚህ በኩል በወቅቱ የነበሩት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከፍተኛ ሥራ እንደሰሩ ይነገርላቸዋል) ሐምሌ ቀን ፲፱፻፺፬ . ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት እንደማይችሉ ፍትሕ ሚኒስቴር እንቅጩን ነገራቸው።
እንግዲህ ከዚህ ወዲህ ነው ደግሞ ሌላ ምዕራፍ መክፈት የጀመሩት። መንግሥት እውቅና አልሰጥም ካለን እኛ ራሳችን ለራሳችን እውቅና ሰጥተን እንንቀሳቀሳለን እውቅና የሌለው ሃይማኖት ነው ተብለን በመንግሥት ዘንድም እንዳንጠየቅ ከቤተክህነቱም እንዳንባረር «ቅብዐት ምስጢር ነው» አንዳንዴም «ባህለ ትምህርት ነው» እያልን እንቀመጥ ብለው ወሰኑ። በዚህ ውሳኔያቸውም መሠረት ከባለ ሃብቶች በሚደረግላቸው ሰፊ ድጋፍ ከቤተክህነቱ ሳይለዩ ራሳቸውን ሳይገነጥሉ በመንግሥት ዘንድም እውቅና ሳይሰጡ በቤተክርስቲያናችን ስም መጻሕፍትን ማሳተምና በአደባባይ መሸጥ ጀመሩ።
በዚህም መሠረት ሐምሌ /፳፻፩ . ላይ ካሳሁን ምናሉ በተባለ ሰው «መሰረተ ሐይማኖት» የተሰኘው መጽሐፍ ታትሞ መሰራጨት ጀመረ። ይህ መጽሐፍም ለቅብዐቶች የመዠመሪያቸው እንደኾነ በዚሁ መጽሐፍ መቅድም ገጽ ላይ ተጽፎ ይገኛል።
ከ፳፻፩ . በኋላ መኾኑን እንጂ መቼ እንደታተመ የማይታወቀው ኹለተኛው መጽሐፍም «ወልደ አብ» ይባላል። በብዛት መሠራጨት የጀመረው በ፳፻፮ . ነው። ስለዚህም መጽሐፉ የታተመው በዚህ አካባቢ ሊኾን እንደሚችል ይገመታል። ይህ መጽሐፍም የጸጋንና የቅብዐትን ባህል የሚያራምድ በሀገራችን ሑከት ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብሎ ጥቅምት ፲፪ የጀመረው የ፳፻፲ . የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞታል። ይህ መጽሐፍ እንዲወገዝ በ፳፻፱ . የምእመናንን ፊርማ በማሰባሰብ ከወረዳ ቤተክህነት ጀምረን ደረጃውን ጠብቀን እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ድረስ የጠየቅን ቢኾንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊወገዝ አልቻለም ነበር። ኾኖም ግን ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ (በ፳፻፲ . የርክበ ካህናት ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የምዕራብ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ኾነው የተመደቡት) ጉዳዩን ይዘው ለሊቃውንት ጉባኤ አስመርተው ለምልአተ ጉባኤው አስቀርበው መጽሐፉ ከማንኛውም አገልግሎት እንዲለይ ተደርጓል። በዚህም ብፁዕነታቸውን ማመስገን ይገባናል። የዚህ መጽሐፍ አሳታሚ ደግሞ በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተክህነት ሥር ያለች አንዲት ገዳም ናት። ምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት አጸደ ኤዎስጣቴዎስ አንድነት ገዳም ናት። ቅብዐትን ከአልፎንሱ ሜንዴዝ የተማረው ኤዎስጣቴዎስ ዘጎጃም እስከዚች ገዳም ድረስ እንዳስተማረ ይነገርለታል። አጸደ ኤዎስጣቴዎስ መባሏም ለዚህ ይመስላል። ክፉ መናፍቅ ተጣብቷት ስሟን በየምንፍቅና መጻሕፍት ላይ እየለጠፉ ጥንታዊቱን ገዳም ስሟን ያጎድፉታል።
ሦስተኛ መጽሐፋቸውን ደግሞ በ፳፻፱ . «ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ» በሚል ከስሙ ጀምሮ የተበላሸ መጽሐፍ በእኛ ሊቃውንት ስም አሳትመዋል። የዚህ መጽሐፍም አሳታሚ ከላይ የገለጥናት ገዳም ናት።
ይህ ኹሉ ሲኾን ግን እኛ የተዋሕዶ ልጆች ተኝተናል። ከ፳፻፬ . ጀምረው አሁን በሊቀጳጳስነት ደረጃ ሀገረ ስብከቱን እያስተዳደሩት የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ማርቆስም እንዲህ እንደሚደረግ እያወቁ ዝም ማለታቸው ያሳዝናል። እንዲያውም ይህ አልበቃ ብሏቸው የእነዚህን መጽሐፈ ምንፍቅና አሳታሚ ገዳም ባገኙት አጋጣሚ ኹሉ ሲያወድሱ መሰማታቸው እርሳቸውም ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው የሚያሳብቅ ነው። ቅብዐቶችም ጊዜ ዓይተው ነፍስ ለመዝራት አካል ለምንሣት የበቁት የሊቀ ጳጳሱን ድጋፍ በማግኘታቸው ይመስላል።
አሁን በየዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የቅብዐት አማኝ ወጣቶች እውቅና የሌለው ማኅበር አቋቁመው እስከ መንቀሳቀስ ደርሰዋል። በየገዳማቱና በየአድባራቱም በመሄድ ስልጠና እንዲሰጡ በጀት ተመድቦላቸው በመሥራት ላይ ናቸው። በደብረ ማርቆስ ወረዳ ቤተክህነት ሥር የሚተዳደረው አባ ዐሥራት ገዳም ይህን መጽሐፈ ኑፋቄ በማሰራጨትና ሥልጠናውን በመከታተል ላይ የሚገኝ ገዳማችን ነው። ይህ ኹሉ ሲደረግ ይህ ኹሉ ሲፈጸም ይህ ኹሉ ሲከወን እያየን ዝም ማለት የሞት ሞት ነው።
ዛሬ ጦር አንመዝም ቤተክርስቲያናችንን ግን እንደ አባቶቻችን በደማችን ልንጠብቃት ይገባል። በዚህ ሃይማኖት ወደ ሀገራችን መግባት የተነሣ እኮ ብዙዎች ተገድለዋል ብዙዎች አካላቸውን አጥተዋል ብዙዎች ሀብት ንብረታቸውን ተነጥቀዋል። አባቶቻችን እስካሁን ድረስ አቆይተውናል። ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ለእኛ አስረክበውናል። በዚህ ዘመን ጉባኤ የሚያዘጋጅ የግራ የቀኙን ሰምቶ የሚፈርድ ንጉሥ የለም። ቢኖር ኖሮ ግን በጉባዔ ተከራክሮ ወደ እውነቱ መድረስ በተቻለ ነበር። አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ይህን ጉዳይ ትኩረት የሰጡት አይመስልም።
ታዲያ ከእኛ ምን ይጠበቃል?
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፯/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment