© መልካሙ በየነ
መስከረም ፲/ ፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
ጅበላ ኦሆ በሀሊት ማርያም ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጎዛምን
ወረዳ ቤተ ክህነት ውስጥ የምትገኝ ጥንታዊና ተአምረኛ ቦታ ናት። የሚያሳዝነው ነገር እንደ ጥንታዊነቷና ተአምረኛ እንደመኾኗ መጠን
ታዋቂነቷ ያን ያህል መኾኑ ነው። እኔ በሕይወቴ ከማዝንባቸው ነገሮች መካከል ትልቁን ቦታ የሚይዘው እንደነዚህ ያሉ ቦታዎች ማወቅ
እና ማሳወቅ አለመቻላችን ነው። በተለይ ጎጃም ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የተረሱ ናቸው። የጥንታዊነታቸውን
እና ተአምረኛ የመኾናቸውን ያህል በአግባቡ ተንከባክበን ታሪካቸውን ደጉሰን ለትውልድ ለማስተላለፍ ብሎም የቀድሞ ይዘታቸውንና ገጽታቸውን
ሳይለቁ በቅርስነት የማቆየት ችግር አለብን። ከእነዚህ ገዳማት እና አድባራት በኋላ የተሠሩ ቦታዎች ኹሉ ታዋቂነታቸው እየጨመረ መጥቶ
በወርኃዊና በዓመታዊ በዓላቸውም የብዙ ቀን ጉዞ በብዙ ብር ክፍያ ተጉዘን ከቦታው በረከትን እንቀበላለን። «በቅርብ የሚገኝ ፀበል
የልጥ መንከሪያ ይኾናል» እንደሚባለው በቅርብ ለሚገኙ ተአምራዊ፣ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ቦታዎች ትኩረታችን ያን ያህል ነው። እንደነዚህ
ያሉ ቦታዎችን ጥቅማቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ተአምራቸውንና በረከታቸውን ከሚያውቁት ጥቂቶች በቀር ብዙዎቻችን ማየት እንኳ ይከብደናል።
የኦሪት መስዋእት ይሠዋባቸው ከነበሩ አምስት ቦታዎች መካከል አንዷ የኾነችው
ጥንታዊቷ ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም በቅርባችን ናት ግን ብዙዎቻችን ለማየት ብለን በዓላማ ሄደን አልጎበኘናትም። መርጡለ
ማርያምን ካነሣን ላይቀር ከኹለት ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ የምናገኘው ደምበዛ ከሚባል ስፍራ አምባላይ ከሚባለው ተራራ ላይ የጥንት
ገዳም አለ። ይህ ገዳም ከዛፍ በቀር ገዳምነቱ አይታወቅም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ገዳሙ ፈርሶ አጽመ ቅዱሳንን እያፈለሱ የእርሻ
ቦታ አድርገውት ስንዴ እና ባቄላ እየዘሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ይጠቀሙበታል። የተረሳ ቦታ በቅዱሳን አጽም ላይ ስንዴ እየተዘራ
የሚበላበት ቦታ ነው። ከዚህ ቦታ ዝቅ ስንል ደግሞ በሣር ክዳን የተሠራ በዓመት ኹለት ጊዜ ብቻ የሚቀደስበት (መጋቢት ፳፱ እና
ነሐሴ ፲፫) ደምበዛ በዓለ እግዚአብሔር ገዳም አለ። ይህ ገዳም ተአምረኛ ፈዋሽ ፀበል ያለው ሲኾን በጣም የሚደንቅ ዋሻም አለው።
እኔ በዚያ ቦታ በነበርኹበት ጊዜ እንኳ ቦታው አጠገቡ በሚገኘው ወንዝ እየተሸረሸረ በጣም አደጋ ላይ ነበር። ይህን ቦታ ስንቶቻችን
እናውቀዋለን?
በዚያው አቅራቢያ የምትገኘው ሌላዋ የተዋሕዶ መዲናዋ ድቦ ኪዳነ ምሕረትም
አቡነ ተክለ ሃይማኖት የባረኳት ቦታ እንደኾነች ይነገርላታል። ጥንታዊና ተአምረኛ ቦታ ናት። ግን ስንቶቻችን እናውቀዋለን?
ሌላው በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገደመ የሚነገርለት የጣቤት ቅዱስ
ጊዮርጊስ ገዳም ነው። ይህ ቦታ የት ነው? የሚል ብዙ ሰው ይኖራል። እኔ ራሱ ቦታውን አላየሁትም ማየት ብቻ ሳይኾን እንዲህ ያለ
ቦታ ምሥራቅ ጎጃም ውስጥ ይኖራል ብየ እንኳ አስቤም አልሜም አላውቅም። ቦታው በደጀን ወረዳ ቤተክህነት ሥር የትኖራ ውስጥ የሚገኝ
ትልቅ ገዳም። የማስታወቂያ ታፔላው የተለጠፈውም ከደጀኖ ወደ ደብረ ማርቆስ በሚወስደው መንገድ ላይ ከየትኖራ ከተማ ወጣ ብሎ እንዳይላሉ
እርሻ መሬት ማለቂያ አካባቢ ነው። ይህን ቦታ ስንቶቻችን አይተነዋል? እኔ አላየሁትም አላውቀውምም።
ከዚህ በተጨማሪ ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ የሚገኙት እንደ ገዳመ አስቄጥስና
እንደ ግምጃ ቤት ኪዳነ ምሕረት ያሉት ገዳማትስ ምን ያህል ጥንታውያን እንደኾኑ ታውቃላችሁ?
እንደ አንቀጸ ብጹአን ዳግማዊ ላሊበላ እና አዲሱ መድኃኔ ዓለም ያሉ የሚያስደንቁ
ቦታዎችም እዚሁ ከደብረ ማርቆስ ከተማ ብዙ ርቀት ሳንጓዝ የምናገኛቸው ተአምረኛ ቦታዎች ናቸው። የኹለተኛው ፓትርያርክ የቅዱስ ሰማእት
አቡነ ቴዎፍሎስ ተወልደው ተምረው አገልግለው የኖሩበት ቦታ ደብረ ኤልያስ እዚሁ ጎጃም ውስጥ የሚገኝ ልዩ ቦታ ነው። ግን ስንቶቻችን
አይተናቸዋል።
ብዙዎቻችን ጉዞ እያዘጋጀን አክሱም ጽዮንን አይተናል መልካም ነው። ደብረ
ሊባኖስን አቡነ ሐብተ ማርያምን አይተናል ጥሩ ነው። ግሸን ደብረ ከርቤን ጎብኝተናል። ላሊበላን አይተናል። በጣም ብዙ ቦታዎችን
በእግርም በመኪናም ተጉዘን ጎብኝተናል እንዲያውም ኹለት እና ሦስት ጊዜ ደጋግመን ያየናቸው ቦታዎችም ይኖራሉ። ነገር ግን ጎጃም
ውስጥ የሚገኙ ተአምረኛ ታሪካዊ ድንቅ ቦታዎችን ስንቶቻችን አይተን ይኾን? በተለይ በዚሁ አካባቢ የምንገኝ ክርስቲያኖች ርቀን ሄደን
ስንት ቦታዎችን ጎብኝተናል? ግን በቅርብ የሚገኙትንስ ማየት የለብንም ወይ? እስኪ እናስብበት። እንዲያውም ከተቻለ ጠንካራ የጉዞ
ማኅበራትም መመሥረት የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ታሪካዊ እና ተአምረኛ ቦታዎችን የማስተዋወቅ አቅምም ችሎታውም ስለሌለኝ ወደ ምስካበ
ቅዱሳን ጅበላ ኦሆ በሀሊት ማርያም ልውሰዳችሁና እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ሄጄ ካየሁት ተአምር እና በረከት ላካፍላችሁ።
ምስካበ ቅዱሳን ጅበላ ኦሆ በሀሊት ማርያም ገዳም
=================================
መቼ ተገደመች? ለሚለው ጥያቄ እንደነገርኋችሁ ታሪክ እና መረጃ ከትቦ የማስቀመጥ
ችግር ስላለብን እኔ ማግኘት አልቻልሁም። በርግጥ የነበረው ኹኔታ ቁጭ ብዬ ታሪክ ለመጠየቅ አላስቻለኝም ነበር። ይህን ለማድረግ
ያላስቻለኝ የመጀመሪያው ጉዳይ አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እየተሠራ ስለኾነ እደንደደረስን ወደዚያ የበረከት ሥራ ስላመራን ነው።
በዚያ ቦታ ኹሉ በረከትን የሚሻማበት ስለነበር ቁጭ ብሎ ታሪክ የመጠየቅ አቅሙ አልነበረኝም። ኹለተኛው ነገር በዚያ ቦታ የሚኖር
አንድም ገዳማዊ አለመኖሩ እንደፈለጉ መጠየቅ የሚቻልበት እድል አላገኘሁም። ሦስተኛው ነገር ደግሞ የቦታውን ታሪክ የያዘ ምንም ዓይነት
የኅትመት ውጤት በቦታው አይገኝም። በዚህ በሰፊው አዝናለሁ። ስንት በስሟ ጽዋእ የሚጠጣ ማኅበርተኛ እያለ ታሪኳን ዘግቦ በመጽሐፍ
መልኩ አዘጋጅቶ የሚያከፋፍል ሰው ግን የለም።
የስሟ ትርጓሜ፡- ኦሆ በሀሊት የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲኾን ትርጉሙም እሽ ባዪት ማርያም ማለት
ነው። እመ ብርሃን በዚህ ቦታ ቆሞ ለሚለምናት ሰው እምቢ ትለው ብላችሁ ነው? እሽ ይኹንልህ ኃጢአትህ ግዱፍ ጸሎትህ ውኩፍ ነው
ወደ ተድላ ደስታ ቦታ ግባ የምትልበት ልዩ ቦታ ነው።
ምስካበ ቅዱሳን ጅበላ ኦሆ በሀሊት ማርያም ገዳም የሥውራን ቅዱሳን አበው መኖሪያ ቦታ ናት፡፡ እመ ብርሃን በራዕይም ተገልጣም የምትነጋገራቸው እኛ የማናያቸው የበቁ የተሠወሩ ቅዱሳን አሉባት፡፡ ይህን የምለው ከምድር ተነሥቼ አይደለም፡፡ ዓይኔ ያንን ድንቅ ተአምር በማየቱ “ወዮልኝ በኃጢአቴ ጠፍቻለሁ” ብየ እንባዬን እንዳፈስ ያደረገኝ ነገር ዝም ብሎ እንደ ውኃ ፈሳሽ ተራ ነገር ስላልኾነ ነው፡፡ አስቸጋሪውና ውጣ ውረድ የበዛበትን መንገድ ተጉዞ እሽ ባዪት ማርያም ላይ የደረሰው የበረከቷ ተካፋይ የኾነው የተዋሕዶ ልጅ ድካሙን ከምንም ሳይጥፍ አዲስ እየተሠራ ላለው ሕንጻ ድንጋይ ሲያቀብል አርማታ ሲሞላ ፌሮ ሲያነጥፍ ግባታውን ውኃ ሲያጠጣ ውሏል፡፡ ሰዓቱ መሸት እያለ ሲመጣ አባቶች ትምህርት እና ቡራኬ ሊሰጡ አዲስ እየተሠራ ካለው ሕንጻ ላይ ቆመው መርኃ ግብር ጀመሩ፡፡ መልእክቶች ተላለፉ ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ማሠሪያ ገንዘብ ተሰበሰበ፡፡ ገንዘብ ለመሰብሰብ ታቦቱ የሚከብርበትን ጥላ መዘቅዘቅ በኦሆ በሀሊት ማርያም ገዳም ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ እናም ሰዓቱ 12፡25 አካባ ሲኾን ርእሰ ርኡሳን አባ ገብረ ማርያም የዕለቱን ትምህርት ሊሰጡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብለው እንደጀመሩ እልልታ እና ጭብጨባ በዛ፡፡ አባ ማስተማራቸውን አቆሙ፡፡ ነገሩን የተረዳነው ወደ ትልቁ የሾላ ዛፍ ዓይናችንን ባነሣን ጊዜ ነበር፡፡ በአራት የተከፈለ የዕጣን ጢስ ከዛፉ ጫፍ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ ከግራ ወደ ቀኝ እየተመላለሰ ሲያጥን ተመለከትን፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ያርጋል፡፡ ይህን የተመለከተው በቦታው የተሰበሰበው ኹሉ በዓይኑ ስለተመለከተው ድንቅ ተአምር ፈጣሪውን በእልልታ እና በጭንጨባ አመሰገነ፡፡
የዕጣኑ ጢስ ከትልቁ የሾላ ዛፍ በላይ ከፍ ብሎ ለኹሉ ይታያል፡፡ ይህ የዕጣን
ጢስ ከየት መጣ? ከሾላው ዛፍ ሥር ካህናት ማዕጠንታቸውን ይዘው አላየናቸውም፡፡ ከሾላው ዛፍ ሥር እሳት የሚያነድ ጭስ የሚያጨስ
ሰው አልተመለከትንም፡፡ ታዲያ ይህን ዕጣን ማን አጨሰው?
የበቁ ሥውራን ቅዱሳን አበው ናቸውን? ሊቃነ መላእክት ናቸውን? ጸወርተ መንበር
አርባዕቱ እንስሳ ኪሩቤል ናቸውን? መንበሩን የሚያጥኑ ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ናቸውን? ካህኑ አሮን ነውን ወይስ ካህኑ
ዘካርያስ ነው? በውኑ ይህን ዕጣን ማን አጠነው? ከእርሱ ከእግዚአብሔር በቀር በውኑ ማን ሊያውቅ ይችላል? ከኦሆ በሀሊት እመብርሃን
ወላዲተ አምላክ በቀር በእውነት ይህን ማ ሊናገረው ማንስ ሊያውቀው ይችላል? ከሠላሳ ደቂቃ ላላነሰ ያህል ከዛፉ በላይ የዕጣን ጢስ
ተመልክተናል፡፡ በቦታው የነበሩ ሰዎች ኹሉ ለዚህ ምስክሮች ናቸው፡፡ ነፋስ ጢሱን ሲያንቀሳቅሰው አይተናል፡፡ ይህ በእውነት ድንቅ
ተአምር አይደለምን? እኛ ወደ ሰማይ አንጋጠን ወደ ላይ ወደ አርያም የሚያርገውን ዕጣን እየተመለከትን አቡነ ዘበሰማያትንና ጸሎተ
ማርያም ከመጸለይ ያለፈ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይህን የተመለከቱ ዓይኖቻችን አነሆ ብጹአን እና የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ብዙዎች
ይህን ሊመለከቱ ወደው ተመኝተው ሳይመለከቱ ቀርተዋልና፡፡
ከዋዜማው በፊት ማለትም መስከረም ስምንት ቦታዋ በቀስተ ደመና ተከባ እንደነበርም
በቦታው የነበሩ አባቶች ነግረውናል፡፡ ከየአቅጣጫው ቀስተ ደመና እየመጣ ወደ ኦሆ በሀሊት ማርያም ሲገባ አይተናል ብለውናል፡፡ እግዚአብሔር
ከፈቀደ ይህንንም ለመመልከት ያድለን፡፡ በዋዜማው ምሽት ላይ ዕጣኑን ሲያርግ ተመልክተናል፡፡ ለዚህ ምሥክሮ እኛ ራሳችን ነን፡፡
እኔም ራሴ ተመልክቸዋለሁና፡፡ ይህንን በመመልከቴም ይህንን ባለመሠወሯም እመብርሃንን አመሰግናታለሁ፡፡ በዋናው በዓል በዐሥር ደግሞ
ታቦቷ ሲወጣ ከወደ ደቡብ አቅጣጫ ጉም መጥቶ መሸፈኑን ዓይቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር እስካሁን ድረስ በበረከት የጎበኛት በረድኤት ያልተለያት
ድንቅ ተአምረኛ ቦታ ናት ኦሆ በሀሊት ገዳም፡፡
ሌላው ወደ ቦታዋ ለመድረስ እንኳን ለሕጻናትና ለአረጋውያን ለወጣቶችም ፈታኝ
ነው፡፡ ውጣ ውረድ የበዛበት የበረሃው ጉዞ ብቻ ከአንድ ሰዓት ያላነሰ ይፈጃል፡፡ ነገር ግን መንገዱ በአንድ ጊዜ ከአንድ ሰው በላይ
ማሳለፍ ስለማያስችል በበዓሏ ቀን ከሦስት ሰዓት ያላነሰ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ መንገዱ በእግር ብቻ ሳይኾን በእጅም ጭምር የሚያስሄድ
ነው፡፡ ትንሽ ውፍረትና ስብ ያጠራቀሙ ግን አንድ እርምጃም ይራመዳሉ ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ተሸክሞ መሄድ ቀርቶ ራስን ይዞ
መንቀሳቀስ ብቻውንም ፈታኝ ነው፡፡ እንደ ሰው ሰውኛው ስንመለከተው ማንም ቦታዋን ለመርገጥ ይችላል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ ግን
የእመ ብርሃን ድንቅ ጥበቃ ስላለ ወድቆ የተጎዳ ድንጋይ ተንዶ የመታው አንድም የለም፡፡ ከተማ ላይ የዐሥር ደቂቃ ጉዞ መጓዝ ከብዷቸው
የሠላሳ ደቂቃ የታክሲ ሰልፍ የሚሰለፉ ሰዎችም ሳይቀር ቦታዋ ላይ ያለምንም ድካም ደርሰዋል፡፡ ሕጻናት እንኳ ብርታት አግኝተው በቦታው
ደርሰው ተመልክቻለሁ፡፡ የስድሳ እና የሰባ ዓመት አረጋውያን አባቶችንና እናቶችንም ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ ኹሉ በተአምር የተደረገ
ነው፡፡ ከተማ የዐሥር ደቂቃ ጉዞ ለመጓዝ እግራቸው ስብር ስብር የሚልባቸው ሰዎች እንዴት አድርገው ያንን ተራራ ወጡት ያንን ቁልቁለትስ
ወረዱት? ከድንግል ማርያም አጋዥነት በቀር በውኑ ለደካማዎች ለእኛ እንዴት ይቻላል? ታክሲ ላይ የኹለት ሰዎችን ቦታ የሚይዙ የራሳቸው
ሰውነት ሸክም የኾነባቸው ሰዎች ሳይቀሩ ያለምንም ድካም ቦታው ላይ ደርሰው ተመልክቻለሁ፡፡
አንድ እናት ኦሆ በሀሊት ያደረገችላትን ተአምር ስትናገር እንዲህ አለች፡፡
እኔ እግሬ አብጦ ከአልጋዬ ተነሥቼ እንኳ ወጥቼ ለመግባት እቸገር ነበር ዛሬ ግን እመ ብርሃን ረድታኝ እቅፍ ድግፍ አድርጋኝ ይኸው
ዛሬ ቦታዋ ላይ ቆሜ እገኛለሁ አለች፡፡ ምነገዱን የምታውቁት ሰዎች መንገዱ እንኳን ለታመመ ሰው ለጤነኛ ሰውም ከባድ ነው፡፡ ግን
እመ ብርሃን በልዩ ተአምሯ ቦታዋን ሊመለከት የወጣውን ኹሉ ከቦታዋ አድርሳ በሰላም ትመልሰዋለች እንጅ ደክሞ ወድቆ ተሰብሮ የሚቀር
ሰው የለም፡፡
ሌላው ጸበሏ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ቦታዎች ጸበሉ በሰፊው የሚፈስ ባይኾንም
እንደ እንባ ያህል ጠብ ጠብ የሚለው ተአምረኛ ጸበል ፈዋሽ ነው፡፡ አምናችሁ ባላችሁበት ቦታ ኹሉ ኾናችሁ ለምኗት ኦሆ በሀሊት ማርያም
ትሰማችኋለች ተአምሯን ታሳያችኋለች፡፡ እስኪ ቦታዋ ላይ ሄዳችሁ ጸበሉን ተጠመቁ አፈሩን ተቀቡ፡፡ እስኪ ሱባኤ ግቡ፡፡ ቦታዋ ልዩ
የቃል ኪዳን ቦታ ናት፡፡ እኔ ያየሁትን ስላየሁ ነው፡፡
ሌላው ተአምር የአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ነው፡፡ የግንባታውን ፍጥነት
ለተመለከተ ሰው ተአምረ ማርያምን በደንብ ይረዳል፡፡ መንገዱ አንድ ራስን ይዞ ለመንቀሳቀስ ከባድ በኾነበት ኹኔታ ሲሚንቶ፣ ፌሮ፣
አሸዋ፣ ጠጠር፣ ውኃ እንደልብ ሳይገኝ በኹለት ወር ውስጥ ያንን ያህል ሥራ መሥራት ተአምር ካልኾነ በቀር ምን ሊኾን ይችላል?
ቦታዋ ላይ ደርሼ ተአምሯን እንደ ኃጢአቴ ብዛት እንደ ሰውነቴ ክፋት ሳትመለከት
ስታሳየኝ የመንገዱን አድካሚነት ከምንም አልጣፍሁትም፡፡ ለዚያች ተአምረኛ ቦታ እንኳን በእግር እና በእጅ ቀርቶ ለምን እየተንከባለልኩስ
አልሄድ? እመቤታችን እኮ የተጓዘችበት ያረፈችበት ቦታ ነው እኛ የምንጓዝበት፡፡ እመብርሃን የተወደደ ልጇን አዝላ የረገጠችውን እኔም
ከረገጥሁት እመ ብርሃን ቁጭ ብላ ያረፈችበትን ቦታ እኔም ካረፍሁበት ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን በረከት አለ?
ቦታዋ ጥንታዊ ናት የምትባለው እንዲሁ አይደለም፡፡ ድንቆችና ተአምሮች እስካሁን
ድረስ ያልተቋረጠባት፡፡ በዚህ ኃጢአታችን ከፍ ከፍ በሎ ሰማየ ሰማያት በደረሰበት ክፉ ዘመን እኛ የምንመለከተው ተአምር በቦታዋ
መኖሩ ቦታዋ የቃል ኪዳን ቦታ መኾኗን ከማስረዳቱም በላይ ጥንታዊነቷንም ይመሰክራል፡፡ እመ ብርሃን ወደ ግብጽ በተሰደደችበት ጊዜ
በዚች ቦታ ለዘጠና ቀናት ያህል አርፋባታለች፡፡ በመንገዳችን መካከልም ይህ የእመ ብርሃን የእግሯ ዱካ ነው ይህ ደግሞ ያረፈችበት
ቦታ ነው እየተባልን ነው ወደ ቦታዋ የደረስን፡፡ ይህ ኹሉ ሲባል ግን ቦታዋን ከማየቴ በፊት እንዴት ይኾናል? የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ቦታዎችን ጥንታዊ እና ተአምረኛ ናቸው ለማስባል የማይኾንና የማይመስል ታሪክ የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ ያ ታሪክ የፈጠራ
እና ውሸት መኾኑን ማረጋገጥ የሚቻልበት ብዙ መንገድ አለ፡፡ ይች ቦታ ግን የውሸት እና የፈጠራ ታሪክ የላትም እውነተኛ ዛሬም ሄደን
የምናረጋግጠው እውነት ያለባት ቦታ ናት፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የእመ ብርሃን ድንግል ማርያም ሥዕል በዚች ቦታ ይገኛል፡፡ ጊዜውና
ኹኔታው የተመቸ ስላልነበረ ሥዕለ ማርያምን የማየት ዕድሉን አላገኘሁም፡፡ ሥዕሏ ግን በዚች ቦታ እንደሚገኝ አልጠራጠርም፡፡ ሕንጻ
ቤተክርስቲያኑ ሲያልቅ ለቅርሶች ደህንነትም አመቺ ኹኔታ ሲፈጠር የማየት ዕድሉን እናገኛለን ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የዚች ሥዕለ
ማርያም በቦታዋ መገኘት ደግሞ ጥንታዊነቷን ይመሰክራል፡፡ ሌላው የጎጃም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በዚች ቦታ ይፈርዱ እንደነበር ይነገራል፡፡
ይች ቦታ ከእነብሴ ሣር ምድሩ አምባላይ ተራራ ጋር ተመሳሳይነት አላት፡፡ ሰፊ ቦታ አላት፡፡ ነገር ግን ወደ ቦታዋ እንስሳትን ለማስገባት
እጅግ ፈታኝ ስለኾነ ያንን ሰፊ መሬት ለግብርና አገልግሎት መጠቀም አልተቻለም፡፡ ቦታዋ ብዙ ገዳማውያንን ማኖር የምትችል ሰፊ የእርሻ
ቦታ ያላት ሰፊ የሱባዐየ ቦታ ያለት ናት፡፡ ውኃ በቀላሉ ማግኘት ግን ያዳግታል፡፡ ለእንስሳት ምቹ የኾነ ሣር ቢኖርም በሬ ለማድለብ
በግና ፍየል ለማርባትና ገዳማውያንን ራሳቸውን ለማስቻል የተደረገ ሙከራ ግን አላየሁም፡፡ በሬ፣ ላም፣ በግ፣ ፍየል ወዘተ ወደ ቦታዋ
ለማድረስ ምንም ዓይነት መንገድ መንገድ የለም፡፡ መጎተቻ ቦታ የላትም፡፡ ራሳቸው እንዳይሄዱ ለሰውም አመቺ አይደለም እንኳን ለእንስሳት፡፡
ወደ ቦታዋ መሄድ ለሚፈልግ ኹሉ ከደብረ ማርቆስ ተነሥቶ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ
በየቦ በኩል አድርጎ ወደ ሊባኖስ ከዚያም ወደ ጭምት ከዚያም ወደ ገተም አድርጎ አንድ መንገድ ብቻ ያገኛል ያችን ተከትሎ ከርቀት
ቦታዋን እየተመለከተ መድረስ ይችላል፡፡ በመኪና ለሚሄድ ሰው ቀጥታ በሊባኖሱ መኪና ገብቶ መሄድም ይችላል፡፡ መኪናው ጭምት ድረስ
መድረስ ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ገተም ማርያሞችን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ ስንሄድ በሰላም ያድርችሁ ስንመለስ እንኳን ደህና መጣችሁ
እያሉ ተቀብለውናልና ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በተለይ ስንመለስ መንገዱም ከባድ እና አድካሚ ስለኾነ ጥሬያቸውን ቀቅለው እንጀራቸውን
ወጥ ቀብተው ጠላቸውን ጠምቀው ማያቸውን ቀድተው ገተም ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ የሚያደርጉት ግብዣ አይ ሲያስቀና፡፡ ሰው ኹሉ
እንዲህ ቢረዳዳ ቢተባበር የት እንደርስ ነበር? እግዚአብሔር ከዚህ መልካም አገልግሎታችሁ አይለያችሁ፡፡ መባረክ እንዲህ ነው፡፡
ቦታዋን ተሳልሞ የመጣውን ኹሉ ተቀብላችሁ ትልቁን በረከት ወስዳችኋል፡፡ በጎደለ ይሙላበት በወጣ ይተካበት እጃችሁ ከቁርጥማት ደረታችሁን
ከውጋት ይጠብቃችሁ፡፡ እመ ብርሃን ፍቅሯን አትለያችሁ፡፡
ወደ ፊት ብናስተካክል መልካም ነው የምለው ነገር!
=================================
እንደ አንድ ክርስቲያን ቢኾን መልካም ነው የምለው ነገር እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
፩ኛ. በኦሆ በሀሊት ማርያም ስም የጽዋዕ ማኅበር ያላችሁ ክርስቲያኖች ኹሉ
የተደበቀ የተረሳ ታሪኳን ጽፋችሁ በመጽሐፍ መልኩ ታትሞ ገባ ለገዳሟ መርጃ እንዲውል ብታደርጉ፡፡ ብዙ ሰዎች ይችን ቦታ ለማየት
ይጓጓሉ፡፡ አንዱ ለአንዱ እንዲያስረዳ የተሰፈረ የተመጠነ እውነተኛ ታሪክ የያዘ መጽሐፈ ኦሆ በሀሊት ማርያም ገዳም መታተም ይኖርበታል፡፡
በቃል ያለ ይረሳል ሲባል ሰምታችኋል መቸም፡፡ በነገራችን ላይ የታሪክ ጉዳይ ከተነሣ ላይቀር የዚች ቦታ ሳይኾን የሌሎች ቦታዎችም
በተለይ ጎጃም ውስጥ ያሉ ቦታዎች ታሪክ አልተጻፈላቸውም፡፡ ታሪካቸውን ጠይቆ የመረዳትና የመጻፍ ሥራ ደግሞ የኹላችን ኃላፊነት ነው፡፡
፪ኛ. ገዳሟ እያስገነባች ያለውን አዲሱን ሕንጻ ኹላችንም በየአቅማችን እንደየችሎታችን
ብንደግፈው፡፡ በዚያ ሕንጻውን እየሠሩ ያሉት ወንድሞቻችን እንደልብ የሚጠጡት ውኃ እንደልብ የሚመገቡት ምግብ አያገኙም፡፡ ውኃው
በክረምት የተገደበ ውኃ ነው፡፡ ለመጠጥም ለግንባታም የሚጠቀሙት ያንን ነው፡፡ ለግንባታ የሚጠቀሙበትና ለመጠጥ የሚጠቀሙበት ኹለት
ኩሬዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ቦታዋ ስንሄድ ለእነዚህ ወንድሞቻችንም አንዳንድ ነገሮችን ብንተባበራቸው መልካም ነው፡፡
፫ኛ. ከበረከቷ ሊካፈል የሚሄድ ሰው ሥጋዊ ነገርን ባያደርግባት፡፡ ለአንድ
ቀን አዳር ቤት ለመሥራት በሚል ስም ዛፎች ሲጨፈጨፉ አስተውያለሁ፡፡ የታሸገ ውኃ፣ ማርማላት፣ የታሸገ ቆሎ፣ ኩኪስ፣ ምግብ በየዓይነቱ
ተሸክሞ የሄደውም በጣም ብዙ ነው፡፡ መብላት መጠጣታችን የግድ ቢኾንም የገዳማውያንን ኑሮ ልንመለከት ነውና የሄድነው በልክ በመጠን
ቢኾን መልካም ነው፡፡ ለመኝታ ፍራሽ፣ ሸራ ወዘተ የያዘውንም ቤት ይቁጠረው፡፡ ይህ ኹሉ ወንጀልና ኃጢአት ባይኾንም በዝናቡ በብርዱ በሙቀቱ ለአንድ ቀን ተፈትነን የጋዳማውያን ኑሮ ብንቀምሰው
መልካም ነው፡፡ ሌላው ሱሱ ተነሥቶበት በዚያ ድንቅ ተአምር በሚታይበት ቦታ ሲጋራ ቋጥሮ የሄደ መኖሩ ደግሞ ያሳዝናል፡፡ እየተሰበሰቡ
ዘፈን መዝፈን መጨፈር መጮኽም አይፈቀድም፡፡ የሥውራን ቅዱሳን መኖሪያ ቦታ ነውና በእኛ መታወክ መረበሽ የለበትም፡፡ ይህንን ጉዳይ
በተለይ አስተባባሪዎች ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡
፬ኛ. ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ አለማቻልንም አስተውያለሁ፡፡ አንድ ሰው ብቻ
በሚያስሄድበት ጠባብ መንገድ ላይ ተንጠላጥሎ አልፎ ለመሄድ የሚሞክር ሰው አለ፡፡ ሌላው ተሰልፎ ሰልፉን ጥሶ ቶሎ ለመሄድ የሚቸኩል
አለ፡፡ በረከታችን በከንቱ እንዳይቀር በትዕግሥትና በዕርጋታ ብናደርገው መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ቀስ ብሎ የሚሄድን ሰው አልፎ
ሮጦ ቀድሞ መሄድ ቀላል ነው ነገር ግን እነዚያን ተስፋ ማስቆረጥም የለብንም፡፡ ሰውም በእኛ እደርስ አደርስ ፊኛው መፈንዳት የለበትም፡፡
መንገዱንም ማማረር የለበትም፡፡
እግዚአብሔር ፈቅዶ ያየሁትን እንድናገር ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ ኦሆ በሀሊት ማርያም እሽ ትበለን በረድኤቷ አትለየን፡፡
ታሪኳን በመጽሐፍ መልኩ ለማውጣት ግን በተለይ ማኅበርተኞች ብታስቡበት መልካም ነው እላለሁ፡፡
እመብርሃን በረድኤቷ አትለየን አሜን፡፡
※※※※※※※※³ ※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB
No comments:
Post a Comment