Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፲፪



የዶግማ ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፭፡- ቅብዐቶች ለቅዱሳን እና ለመስቀል ስግደት አይገባም ይላሉ እኛ ግን ይገባል እንላለን።
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ይህን መልእክት ለኹሉ እንዲደርስ ሸር ማድረግ ግድ ይላል።
ቅብዐቶች ለቅዱሳን ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። ይህ አመለካከት ምናልባትም ለፕሮቴስታንት መናፍቃን ያላቸውን አጋርነት እያረጋገጡ መኾኑ ለማንም የማይካድ እውነታ ነው። ብዙ የቅብዐት እምነት ተከታዮች የእናት የአባቴን እምነት አልተውም ከማለት የዘለለ መከራከሪያ ነጥብ አያቀርቡም። የቅብዐትን ምስጢር በሚገባ ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ የሄኖክ ደቀ መዛሙርትም እንዲህ ያለውን የዶግማ ልዩነት ደብቀው በበዓላት እና በአጽዋማት ላይ ሲከራከሩ ነው የሚታዩት። እውነታው ይገለጥ ከተባለ ግን ልዩነታችን የዶግማ ነው። የቀኖና ልዩነትማ እኮ ምንም ማለት አይደለም ምክንያቱም አስታራቂ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ስላለን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ እንመራለን። የጌታ ልደትን በዚህ ቀን አክብሩ ጾም በዚህ ቀን ይገባል በዚህ ቀን ይፈሰካል ብለው በሠሩልን ሥርዓት እንመራለን። ዶግማውን ግን ማንም አይሽረውም ማንም አይለውጠውም ማንም አያስተካክለውም። ከዶግማ ልዩነቶቻችን መካከል የመጀመሪያውን በክፍል ፲፩ ተመልክተናል። ባለፈው ክፍል እንዳየነው ቅብዐቶች ወልድን ፍጡር ነው ይላሉ እኛ ግን ፈጣሪ ነው እንላለን ብለናል። ዛሬ ደግሞ ቅዱሳን ላይ ያላቸውን የተጣመመ ትምህርት አሳያችኋለሁ። ለዚህም ከታች በፎቶ የተያያዘውን «ወልደ አብ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ያለውን ማስረጃ ተመልከቱ። ፎቶው ለማይከፍትላችሁ ግን ከታች ጽፌላችኋለሁ። ብዙ የቅብዐት እምነት ተከታዮች ይህን ተመልክታችሁ ዛሬውኑ ከዚህ ምንፍቅና ካልወጣችሁ በእውነት በራሳችሁ ፈቃድ ሞትን እንደመረጣችሁ እውቁት። ይህን የሚያነብ ሰው ኹሉ ለሌሎች መልእክቱን ማድረስ ስለሚኖርበት ሸር ማድረጉን አትዘንጉት እናንተ ለአንድ ነፍስ መዳን ምክንያት ብትኾኑስ ማን ያውቃል።
ወልደ አብ ገጽ ፪፻፶፩ ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
«የጻድቃን እናቶች ይሰገድላቸዋልን ስንኳንስ ለእናቶቻቸው ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም። እርሷ ግን የባሕርይ ልጅ የኾነውን ብትወልድ እሰግድ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ንጽሕተ ሥጋ ወነፍስ ተብሎ ይሰግድላታል። ሰጊድ ወክብር ይደልዋ ለእግዝእትነ ማርያም ወለደማቴዎስ ፍስሐ እንዳለ ጊጋር በነገረ ማርያም፤ ለመስቀልም መሰገዱ የእርሱን የባሕርይ ልጅነቱን ያጠይቃል እንዴት ቢሉ እንግዲያው የቅዱስ ጴጥሮስ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ይሰገድለታልን፤ ስንኳንስ ለመስቀሉ ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም። መስቀል ግን የባሕርይ ልጅ የኾነው ሥጋው ቢቆረስበት ደሙ ቢፈስበት እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር ተብሎ ይሰገድለታል» ይላል።
ይህ ምንም ማብራሪያ የማያስፈልገው ቁልጭ ያለ ክህደት ነው። ለቅዱሳን እናቶች መስገድ ይቅርና ለቅዱሳን ልጆቻቸውም ስግደት አይገባም እያለ ነው የሚናገረው። ከዚህ በተጨማሪም እንኳን ለቅዱስ ጴጥሮስና ለቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል መስገድ ይቅርና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለቅዱስ ጴጥሮስም መስገድ አይገባም እያለ ነው ኑፋቄውን የሚዘራ። ይህንን ኑፋቄ ተቀብላችሁ እውነት ነው ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ትሉኝ እንደኾነ እንጅ ተመልሳችሁ ቀኖና ላይ ልትገቡ አትችሉም። ይህንን ኑፋቄ በውኑ ከወዴት አመነጫችሁት?
በርግጥ ወልድን ፍጡር ነው ብሎ ለሚያምን ሰው ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ማለት ቀላሉ ስለኾነ ምንም ላይመስላቸው ይችላል። ለእኛ ግን ይህ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ለቅዱሳን ስግደት እንደሚገባ ማስረዳት ካስፈለገ ጥቂት ጥቅሶችን ብጠቁም ደስ ይለኛል። በርግጥ ቅብዐቶች ለእመቤታችን ስግደት ይገባል ለቅዱሳን ግን ስግደት አይገባም ነው እያሉ ያሉት። ቢኾንም ግን ያው ከፕሮቴስታንቱ የቀዱት ኑፋቄ ነውና ነገ ደግሞ ለመላእክትም ለእመቤታችንም ስግደት አይገባም ስለሚሉ የተወሰኑ ነገሮች ልበላችሁ።
·        ለእመቤታችን ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- እመቤታችን መልእልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ናት፡፡ እመቤታችን አምላክን በድንግልና ጸንሶ በድንግልና የመውለድ ለማንም ያልተደረገ ልዩ ጸጋ የተሰጣት ናትና የጸጋ ስግደት እንሰግድላታለን፡፡ የምንሰግድላት ግን አምላካችን ናት ብለን ሳይኾን የአምላክ እናት እናታችን ብለን ነው፡፡ መዝ ፻፴፩÷ ላይ ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን ይላል ዳዊት፡፡ እመቤታችን ደግሞ እግሮቹ ከቆሙበት ሥፍራ በላይ በማኅጸኗ ተሸክማዋለችና እንሰግድላታለን፡፡
·        ለመላእክት ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- ለቅዱሳን መላእክት የሚሰገደው ስግደት የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ዘፍ ፲፱÷ ላይ ኹለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር፡፡ ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ ይላል።
·        ለቅዱሳን ስግደት አይገባም ለሚሉ፡- ለቅዱሳን የሚሰገደው ስግደት የጸጋ ስግደት ነው፡፡ ዳን ÷፵፮ ላይ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነጾር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት ይላል፡፡ ታዲያ ለቅዱሳን ስግደት ባይገባ ኖሮ ያውም ትዕቢተኛ የነበረው ንጉሥ ናቡከደነጾር ለነቢዩ ዳንኤል እንዴት ሊሰግድለት ቻለ?
ለቅዱሳን ስግደት እንደሚገባ የሚጠቁሙ ጥቅሶች => ዘጸ ፲፰÷፯፣ ፩ኛ ነገ ፲፰÷፯፣ ፪ኛ ነገ ÷፲፭፣ ፪ኛ ነገ ÷፴፯፣ ዳን ÷፵፮፣ ፪ኛ ሳሙ ÷፪፣ ሐዋ. ሥራ ÷፳፭።
ሌላው ቅብዐቶች መስቀል ላይ ያላቸው ትምህርትም የተዛባ መኾኑን በመጽሐፋቸው ላይ አይተናል። «የቅዱስ ጴጥሮስ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ይሰገድለታልን፤ ስንኳንስ ለመስቀሉ ለእርሳቸውም አይሰገድላቸውም» የሚለው ትምህርታቸው እንኳንስ ለመስቀላቸው ይቅርና ለቅዱሳኑ ለእነ ቅዱስ ጊዮርጊስም ለእነ ቅዱስ ጴጥሮስም ስግደት አይገባቸውም የሚል ነው። ይህ ማለት ለመስቀልም ስግደት አይገባም ማለት ነው። በእውነት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ስግደት አይገባምን? ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት መዝ ፻፴፩÷ ላይ ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን ማለቱን እናስተውል፡፡ እግሮቹ የቆሙበት ስፍራ በእውነት ከመስቀሉ በላይ ምናለ? እግሮቹ ብቻ ያይደለ መላ አካሉን ምቹ ዙፋኑ አድርጎ ያሳረፈበት ቦታ በእውነት መስቀሉ አይደለምን? እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን «እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር - ዓለምን ኹሉ ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት [በክቡር ደሙ ለቀደሰው] መስቀልም እሰግዳለሁ» እያልን በዘወትር ጸሎታችን እናነሣዋለን እንሰግድለታለንም።
ጠቅለል ስናደርገው ቅብዐቶች ለቅዱሳን እና ለመስቀል አይሰገድላቸውም ይላሉ፤ እኛ የተዋሕዶ ልጆች ደግሞ የጸጋ (የአክብሮት) ስግደት ይገባቸዋልና እንሰግድላቸዋለን እንላለን።
የቅብዐት እምነት ተከታዮች ሆይ! የውስጡን ምስጢር ደብቀው በጾም እና በበዓላት እንድትነታረኩ ያደረጓችሁን ሐሰተኛ መምህራን አትስሟቸው። ከቅዱሳን አንድነት ሊለይዋችሁ ነው የተነሡት። ለመስቀል አይሰገድም እያሏችሁ ነው ያሉት። ከመስቀል ከለይዋችሁ ከቅዱሳን ከለይዋችሁ ታዲያ ምን ሕይወት አላችሁ? ቅዱስ ጊዮርጊስ አያስፈልጋችሁም አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይጠቅሟችሁም እያሏችሁ መኾኑን ልብ ብላችሁ ወደ እውነተኛዪቱ ሃይማኖት ተመለሱ እንላለን።
በጾም እና በበዓላት ላይ እንድትከራከሩ ያደረጓችሁ አውቀው ነው። ዋናውን ምንፍቅናቸውን በአንድ ጊዜ ወደእናንተ ለማድረስ ስለተቸገሩ ነው እንጂ ነገ ከነገወዲያ የምን ቅዱሳን ነው የምን መስቀል ነው የምን ስግደት ነው የምን ጾም ነው ማለታቸው አይቀርም። በመጽሐፍ ጽፈውላችኋል እኮ ነገ ደግሞ በተቀደሰው ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ይህንኑ ማስተማራቸው አይቀርምና አትከተሏቸው።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፫/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment