የቀኖና ልዩነቶቻችን
የጌታን ልደት በዓል ታኅሳስ ፳፰ ቀን ለምን እናከብራለን?
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ቅብዐቶች በመሠረታዊነት ለመከራከሪያ የሚያነሡት ሐሳብ X«ጳጉሜን ስድስት ስትኾን በዓለ ልደት ወደ ፳፰ ቀን የሚወርድ ከኾነ ግዝረትም ጥምቀትም አንዳንድ ቀን ወደ ኋላ መውረድ አለባቸው ማትለት ነው። አመቱም ወራቱም ቀኑም በሙሉ በዓላት ኹሉ ወደ ዋዜማ መውረድ አለበት ማለት ነው»X የሚለውን ነው።
ልዩነታችን ቅብዐቶች የጌታ ልደት በዓል ኹል ጊዜ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን መከበር አለበት ይላሉ። እኛ ግን በዘመነ ዮሐንስ ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን እናከብራለን። ታኅሳስ ፳፰ ቀን ልደትን ማክበራችን ራሱን የቻለ ምክንያት ስላለው እርሱን እንመለከታለን። ልደት ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ከተከበረ ጥምቀት፣ ግዝረት፣ ሌሎችም በዓላት ለምን አንድ ቀን ወደፊት አይከበሩም የሚል ጥያቄም ስለሚያስነሣ ይህንንም እንመለከታለን።
ታኅሳስ ፳፰ ቀን የጌታን ልደት የምናከብረው ስለሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡-
W ፩ኛ. የዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ከሌሎች ዓመታት በተለየ ፮ ቀን ትኾናለች። ይህች ጳጉሜን ስድስት በመኾኗ ምክንያት ታኅሳስ ፳፱ ይከበር የነበረውን የጌታ ልደት በዓል አንድ ቀን ወደፊት ታመጣዋለች። የዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ወደ ዘመነ ዮሐንስ መሸጋገር አትችልም የምትፈጸመው የምታልቀው በዚያው ዘመን ነው የሚሉ ሊቃውንትም አሉ። እነዚህ ሊቃውንት ሌሎችን ወደፊት የምንመለከታቸውን ማስረጃዎች ያቀርባሉ።
W ፪ኛ. ወንድ ልጅ የተጸነሰ እንደኾነ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀን ይቆያል። የጌታ ጽንሰት መጋቢት ፳፱ ቀን ነው። ልደቱም ታኅሳስ ፳፱ ቀን ነው ይህን ስንቈጥር ፱ ወር ከ፭ ይኾናል። በዘመነ ዮሐንስ ልደትን መቼ እናክብረው ብለን ስንነሣ ጌታ ከተፀነሰበት መጋቢት ፳፱ ጀምረን ፱ ወር ከ፭ ቀን ስንቈጥር ታኅሳስ ፳፰ ቀን ላይ ያርፋል። ስለዚህም በዘመነ ዮሐንስ የልደት በዓሉን ታኅሳስ ፳፰ እናከብረዋለን ማለት ነው። በዘመነ ሉቃስ የምትፈጸመዋ ስድስቷ ጳጉሜን ልደቱን ታኅሳስ ፳፰ እንድናከብር ታስገድደናለች ማለት ነው። በዘመነ ዮሐንስ ታኅሳስ ፳፱ እናክብር ካልን ግን ጌታ በማኅፀነ ማርያም የቆየው ፱ ወር ከ፭ ቀን መኾኑ ይቀርና ፱ ወር ከ፮ ቀን ይኾናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይኾን ጉዳይ ነው። ስለዚህ ይህ የቀን አቈጣጠራችን ያመጣው ጉዳይ ነው ማለት ነው። በዚህም ደራሲው የጻፈው የፈጠራ እና የልብ ወለድ ድርሰት ከንቱ ኾነ ማለት ነው።
W ፫ኛ. የልደት በዓል ዕለት ምርያ በዋለችበት ዕለት በታኅሳስ መጨረሻ እንዲከበር አባቶቻችን አዝዘውናል። ዕለተ ምርያ የምትባለዋም ጳጉሜን ፭ ቀን ናት። ዕለተ ምርያ ማለትም ዕለተ መድኃኒት ማለት ነው። ይህችን ዕለት ይዛችሁ ታኅሳስ ፳፰ ወይም ታኅሳስ ፳፱ ላይ ልደትን ታገኙታላችሁ። ለምሳሌ በዘመነ ማቴዎስ ዕለት ምርያ (ጳጉሜን ፭) ማክሰኞ ዋለች እንበል። መስከረም ፩ ረቡዕ ይውላል ማለት ነው። ታኅሳስ ወር ትሄዱና ማክሰኞ የሚውሉ የወሩ የመጨረሻ ቀናትን ታወጣላችሁ ማለት ነው። መስከረም ፳፰ ማክሰኞ ይውላል። ጥቅምት ፳፮ አሁንም ማክሰኞ ይውላል። ኅዳር ፳፬ ማክሰኞ ይውላል። ታኅሳስ ፳፪ ማክሰኞ ይውላሉ። ከማክሰኞ እስከ ማክሰኞ ድረስ አስልተን የታኅሳስን የመጨረሻ ማክሰኞ የሚውለውን ቀን እናገኛለን ይህ ቀንም ታኅሳስ ፳፱ ይኾናል ማለት ነው። ስለዚህ ገና በዘመነ ማርቆስ ታኅሳስ ፳፱ ይውላል ማለት ነው። ዕለተ ምርያን አልለቀቀም። የሦስቱንም ዘመናት (ዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ) በዚህ መልኩ አስሉት ታኅሳስ ፳፱ ይውላል። ወደ ዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እንምጣ እስኪ። በዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ፭ ዕለተ ምርያ ረቡዕ ዋለች እንበል። ሐሙስ ጳጉሜን ፮ ዓርብ መስከረም ፩ ይውላሉ ማለት ነው። መስከረም ፩ በዋለበት መስከረም ፳፱ ይውላል። በዚሁ መሠረት ጥቅምት ፳፯፣ ኅዳር ፳፭፣ ታኅሳስ ፳፫ ዓርብ ይውላሉ ማለት ነው። የታኅሳስ ዕለተ ምርያ በዋለችበት ረቡዕ የሚውለውን የወሩ መጨረሻ ቀን ፈልጉ እስኪ። ታኅሳስ ፳፫ ዓርብ ውሏል የዚህ ሳምንት ታኅሳስ ፴ ይኾናል። ከዚያ ረቡዕ የሚውለውን ቀን ተመልሳችሁ አስሉት። ሐሙስ ታኅሳስ ፳፱ ይኾናል ዕለተ ምርያ የዋለችበት ረቡዕ ታኅሳስ ፳፰ ይኾናል ማለት ነው። ስለዚህ በዘመነ ዮሐንስ ልደቱ በ፳፰ ይውላል ይከበራል ማለት ነው።
W ፬ኛ. በዓሉ በቀኖና የሚከበር እንደመኾኑ መጠን አክብሩት በተባልንበት ዕለት ልናከብረው ግዴታ ነው። ከጥንት ጀምራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብሔራዊ ሃይማኖት ኾና የቆየች ስለኾነች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንኳን በዘመነ ዮሐንስ የሚዘጉት ታኅሳስ ፳፰ ነው። ይህ እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ ባይገባውም ማለት ነው።
ሌላው በቅብዐቶች ዘንድ የሚነሣው ጥያቄ ልደት አንድ ቀን ቀድሞ ከተከበረ ጥምቀት፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን እና ሌሎች በዓላትም ለምን አንድ ቀን ቀድመው አይከበሩም የሚል ነው። ይህንን ለሚሉ ሰዎች እንዲህ እንመልሳለን።
እግዚአብሔር የአዳምን ንስሐ ተቀብሎ ተስፋ የሰጠው «በኃሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ» ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ የሚል ነው። እዚህ ላይ ለአዳም መዳን የጌታችን መሰቀል ግድ ነው ለመሰቀል ደግሞ መወለድ ያስፈልገዋል። ስለዚህ ነው «ከልጅ ልጅህ ተወልጀ» ያለው። ስለዚህ የጌታ በዓል በኵረ በዓላት ነው ማለት ነው። አዳም ተስፋ ያደርግ የነበረውም የጌታን መወለድ ነበር። ጌታችን በመወለዱም ለእኛ አርአያ ሊኾኑ የሚችሉ ሥራዎችን አድርጓል። ለምሳሌ በስምንተኛው ቀን ተገዝሯል በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቋል። እነዚህ ሥራዎቹ ለእኛ አርአያ ሊኾኑ የሚችሉ ናቸው እንጂ አዳም ለድኅነቱ ግን ተስፋ ያደረጋቸው አይደሉም። ስለዚህ ተስፋ የተደረገበትን በዓል ሱባዔ የተቈጠረለትን በኵረ በዓላት የኾነውን ልደት ብቻ ነው አንድ ቀን አስቀድመን ልናከብረው አባቶቻችን የወሰኑልን። ምስጢር የጠነቀቁ መጻሕፍትን ያወቁ እኮ ናቸው ይህንን የወሰኑልን። ከልጅ ልጅህ ተወልጀ በመስቀል ተሰቅየ ሞቼ ተነስቼ አድንኃለሁ አለው እንጂ ተገዝሬ ተጠምቄ አድንኃለሁ አላለውም። ግዝረቱም ጥምቀቱም ለአርአያ ነው ልደቱ ሞቱ ትንሣኤው ግን ለድኅነታችን ነው። ስለዚህ ለድኅነታችን የተፈጸመውን ልደት እንጂ ጥምቀት እና ግዝረቱን ወደፊት አምጥተን አናከብረውም። በዚያውስ ላይ ጌታ ተገዘረ ተጠመቀ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ መባሉ ስለተወለደ ነው እንጂ ባይወለድ ኖሮ እንዲህ ሊባል ይችል ነበርን?
መምህር ወልደ አብርሃም በምስጢረ ተዋሕዶ መጽሐፋቸው ገጽ ፺፩ ላይም «ልደት በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከ፳፱ ወደ ፳፰ ከመጣ ግዝረትም እና በዓለ ስምዖንም ለምን ወደኋላ አይመጣም ብለው ለሚያነሡት ጥያቄ መልሱም እንደሚከተለው ይኾናል። ልደት በአሀዝ እና በትንቢት የታጠረ ስለኾነ ዕለተ ምርያን የሚከተል ሲኾን ዕለተ ፅንስ እንዳይፋለስ በአቡሻኸር አቈጣጠር ቀምረው ልደትን በአራት ዓመት አንዴ ዕለተ ምርያ በምትውልበት ጳጉሜን ፭ በታህሳስ ፳፰ እንድናከብረው አዝዘውናል። ብዙ በዓላት በተሸጋሸጉበት ማክበራችን የአባቶች ሥርዓት ስለኾነ ነው። ለምሳሌ ትንሣኤ የሚውለው መቼ ነው? መጋቢት ፳፱ ለምን አልኾነም፤ ስቅለት የሚውለው መቼ ነው? ለምን መጋቢት ፳፯ አልኾነም እነዚህንና የመሣሰሉትን በዓላት ለምን ተሸጋሸጉ አንልም። ምክንያቱም እነዚህ በዓላትም ኾኑ የልደት በዓል የበዓል አከባበር ሥርዓት ወይም ቀኖና እንጂ አባቶቻችን ስለሠሩልን ያንን መቀበል ግድ ይላል። ዋናው ነጥብ ግን የጌታ ልደት አከባበር ቀኖና እንጂ ዶግማ ስላልኾነ መሠረታዊ የሃይማኖት መከራከሪያ ኾኖ መቅረብ የለበትም» በማለት ያስረዳሉ።
ጠቅለል ስናደርገው የበዓላት አከባበር ላይ ለመነጋገር በመዠመሪያ የተወለደውን ክርስቶስን በተዋሕዶ ከበረ ብለን ልንቀበለው ይገባል።
ቅብዐቶች «ልደት በ፳፱ ቀን እንዲከበር ዲድስቅልያውም ፍትሐ ነገሥቱም አዝዟል። ታዲያ እናንተ ከዲድስቅልያውና ከፍትሐ ነገሥቱ ውጭ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ለምን ታከብራላችሁ?» ብለውም ይጠይቃሉ። ዲድስቅልያውም ፍትሐ ነገሥቱም እንደዚህ ይላሉ ልክ ነው።
ዲድስቅልያ ፳፱÷፪ ላይ፡-
«መጀመሪያው በዓል ይኸውም ክርስቶስ የተወለደበት ቀን በዕብራውያን አቈጣጠር በዘጠኝኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን ነው። በግብጻውያን አቈጣጠር በአራተኛው ወር በታኅሳስ ሃያ ዘጠኝ ነው» በማለት ይናገራል።
ፍትሐ ነገሥቱም ፲፱÷፯፻፳፮ ላይ ይህንን የዲድስቅልያውን ትእዛዝ ራሱን ይጽፈዋል። ከዚህ የምንመለከተው ጌታችን የተወለደው ታኅሳስ ፳፱ ቀን እንደኾነ ነው። የልደት በዓሉንም ታኅሳስ ፳፱ እንድናከብር ነው ነገር ግን ታኅሳስ ፳፱ ብቻ የሚል የብቻ አጥር አላስቀመጠም። መጻሕፍትን ጠቃቅሰው ሰውን ለማሳት ከተነሡ እስኪ እነዚህን ጉዳዮች እንመልከታቸው።
@ ፩ኛ. መሠረተ እምነቱን ደብቀን በቀኖና በበዓላት አከባበር ላይ በሥርዓተ ቤተክርቲያን ላይ መከራከር አለብን ወይ? አንድ ሰው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መከራከር ያለበት እኮ የእምነቱን መሠረታዊ አስተምህሮ በሚገባ ከተረዳ እና ከተስማማ በኋላ ነው። የአንድ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ስለ ሌላ ቡድን ተጫዋቾች አሰላለፍ ማውራት መከራከር እንዲህ ነው መሰለፍ የነበረባቸው ወዘተ ብለው በማይመለከታቸው ገብተው ሊዘባርቁ ሊነታረኩ አይችሉም ምክንያቱም አይመለከታቸውምና። ከኾነለት የራሱን አሰላለፍ ነው ማሳመር ያለበት። ምን ለማለት ፈልጌ ነው ልደት ታኅሳስ ፳፰ ወይም ታኅሳስ ፳፱ ይከበር አይከበር ብሎ ለመናገር በመዠመሪያ ስለጌታ ልደት ማወቅ አለብን። የጌታን ልደት ከማክበራችን አስቀድሞ ጌታ የተወለደው እንዴት ነው? ቃል ሥጋ የኾነበት ምስጢር ምንድን ነው? እንዴት የሰውን ሥጋ ለበሠ? አካላዊ ቃል እንዴት በሥጋ ማርያም ተገለጠ? ምስጢሩ እንዴት ነው? ወዘተ በሚለው ነገር ላይ መዠመሪያ መተማመን ያስፈልጋል። እንዴት በሥጋ ማርያም እንደተገለጠ ሳንስማማ እኛ በተዋሕዶ ከበረ ስንል አይደለም በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው የከበረ እያሉ እየተከራከሩ ልደት ታኅሳስ ፳፰ ወይም ታኅሳስ ፳፱ ነው እያልን ልንጨቃጨቅ አንችልም። ምክንያቱም ይህ መሠረታዊ ጉዳይ አይደለምና። የልደት በዓል ሳይከበርም ሊቀር ይችል ነበር እኮ ሥርዓት ቀኖና ባይሠራለት ኖሮ። አሁን ግን አባቶቻችን እንዳዘዙን እናከብራለን። ልደት ታኅሳስ ፳፰ ወይም ታኅሳስ ፳፱ ተከበረ ማለት እኮ ጌታችን በየዓመቱ ይወለዳል ማለታችን አይደለም። ታዲያ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስለምትከበረው አንዲት ቀን ምን አከራከረን?
@ ፪ኛ. ዲድስቅልያው ላይ ተጽፎ የምናገኘው ኹሉ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። የዲድስቅልያውን ሐሳብ ፍትሐ ነገሥቱም ስለሚተባበርበት አንዳንድ ነጥቦችን ማንሣት እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ስለኤጲስቆጶሳት በሚናገርበት አንቀጹ ላይ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት ፩ኛ ጢሞ ፫÷፩-፯ ያለውን ቀጥታ መዝግቦት እናገኛለን።
«ማንም ሰው ኤጲስ ቆጶስነትን ሊሾም ቢወድ እነሆ መልካም ሥራን ወደደ። ነውር የሌለበት ሰው ኤጲስ ቆጶስ ይኾን ዘንድ ይገባል። አንዲት ሴት ያገባ፣ በሐሳቡ ንቁ የኾነ… ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ»
ይላል ፍትሐ ነገሥት ፭÷፹፫ ላይ። ይህ ራሱ ሳይቀየር ዲድስቅልያው ላይም አለ ስለኤጲስቆጶሳት በሚናገርበት አንቀጽ ፬÷፲፪ ላይ ተጽፎ ይገኛል። እንዲህ ይላል፡
«እንደዚህ ያለ ኤጲስ ቆጶስ አንዲት ሴት ያገባ ቤተሰቦቹን በመልካም ማስተዳደር የሚችል የሚያስተምርና የሚመክር ልጆቹን በንጽሕና ያሳደገ ይሾም» ይላል።
በነገራችን ላይ ሙሉውን አንቀጸ ኤጲስቆጶሳት እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ።
እዚህ ላይ ለማሳየት የፈለግሁት የጌታ ልደትን ዲድስቅልያ በ፳፱ አክብሩ እያለ «በተዋሕዶ ከበረ» የሚሉ የተዋሕዶ አማኞች ልደትን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሳስ ፳፰ ያከብራሉ ብለው እንደ ነውር ስላመጡ ዲድስቅልያውን በሙሉ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ካላችሁ ስለኤጲስ ቆጶሳትም ሲናገር «አንዲት ሴት ያገባ፣ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርና ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ» ይላልና ያገባ ኤጲስ ቆጶስነት መሾም የለበትም ስንል ዲድስቅልያውን አልተቀበላችሁትም ልትሉን ነው ለማለት ነው። ታዲያ ዲድስቅልያውን ስታከብር «ኤጲስ ቆጶስም ያገባ እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድር እንዲሁም ልጆቹን በሚገባ የሚያሳድግ» መኾን አለበት በማለት ያገቡትን ኤጲስ ቆጶሳት እንድታደርግ ቤተክርስቲያንንም እየተገዳደርህ ነው ማለት እኮ ነው። ልደትን ታኅሳስ ፳፰ እንዲከበር ያደረጉ መናፍቃን ናቸው እንዳለው ኹሉ ኤጲስ ቆጶስ ሚስት ልትኖረው አይገባም ያሉም መናፍቃን ናቸው ማለቱ ነው። ስለዚህ ልደት መቼ ጀምሮ ነው ታኅሳስ ፳፰ መከበር የጀመረው? እና ምስጢሩስ ምንድን ነው? ብሎ መመርመር ይበጃል እላለሁ።
W ፫ኛ. ልደት ከታኅሳስ ፳፱ መውጣት የለበትም በሚለው ከጸኑ እነዚህን በዓላት ለምን እንደዚህ እንዲቀያየሩ ተደረገ የሚለውን መመለስ አለባቸው። ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት የሚውሉበትን ቀን አስቡት። ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ቀን፣ ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት ፳፱ ቀን፣ ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት ፰ ቀን ነው። እኛ ግን እነዚህን በዓላት የምናከብረው ቀኑን እየቀያየርን ዕለቱን ሳንቀያይር ነው። ለምን እንዲህ አደረግን ታዲያ? በዚህም ስሕተት ሠርተን ነው ማለት ነው? ወይስ ደግሞ መናፍቃን አምጥተውብን ይኾን? ቀኖና ስለኾነ ብቻ ነው። ለድሜጥሮስ በተገለጠለት ባሕረ ሐሳብ መሠረት የሚሠራ ነውና ኹላችን እንስማማበታለን።
ከዚህ በተጨማሪም በዐቢይ ጾም የሚውሉ በዓላትን በተመለከተ በመቀያየር እናከብራለን። ለዚህም መጋቢት ፳፱ ይከበር የነበረውን የብሥራት በዓል ታኅሳስ ፳፪፣ መጋቢት ፳፯ ይከበር የነበረውን የስቅለት በዓል ጥቅምት ፳፯፣ መጋቢት ፭ ይከበር የነበረውን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓለ እረፍት ጥቅምት ፭ ወዘተ እንድናከብራቸው ታዝዘናል። ለምን ቀኑ ተቀያየረ የሚለውን መመለስ ከቻልን ልደት ታኅሳስ ፳፰ ቀን ለምን ተከበረ ብለን አንጠይቅም።
ጠቅለል ስናደርገው በመጀመሪያ መሠረተ እምነቱ ላይ መተማመን ይገባናል እንጂ የበዓላት አከባበር ላይ ዘው ብለን ገብተን ልናወናብድ አይገባም። ይህ አካሄድ በር ተከፍቶ መግባቱን ሳያምን ወለል ላይ ቆሞ እንደ መከራከር ያለ ነው። ይህንን መጠየቅ ያለበት የሚመለከተው ሰው ብቻ ነው የማይመለከተው ሰው ግን አይመለከተውም። ቤተክርቲያናችን አስቀድመን ከላይ በገለጽነው ምክንያት ልደቱን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታኅሳስ ፳፰ ቀን ስታከብር ኖራለች አሁን እያከበረች ትገኛለች ወደፊትም እንዲሁ በቀኖና ቤተክርስቲያን እስካልተሻሻለ ድረስ ስታከብር ትኖራለች።
ይቀጥላል---
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፳፩/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment