Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፱



የቀኖና ልዩነቶቻችን
ልዩነት ፪፡- ጾመ ነቢያትን የተመለከተ ልዩነት
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ሌላው በቀኖና ከቅብዐቶች ጋር የምንለያየው በነቢያት ጾም መግቢያ እና መውጫ ላይ ነው። ጾመ ነቢያት መቼ ይጀምራል የሚለውን ሲናገሩ ቅብዐቶች መሰረተ ሐይማኖት በተሰኘው የመጀመሪያው መጽሐፋቸው ፵፰ ላይ እንዲህ ይናገራሉ።                                                     ==============================
ማንም ነቢያት 40 ቀን ውጭ የጾመ የለምና አርባ መዓልተ ወዓርባ ሌሊተ ጾመ ሙሴ ነው ያለውና። እኛ ግን ኅዳር ፲፱ ቀን እንጀምራለን። ታኅሣሥ ፳፱ ዕንገድፋለን።በአረቱም ዘመን ማለት ነው። አብርሃም ሶርያዊ እኮ ያችን ሶስት ቀን ለራሱ ታምር ስሰራችለት ነው እንጅ እንድት ፆም ያለው ስለዚህ እንደ ህግ አይደለም እንደ ፍላጎት ነው እንጅ ሰባቱን አጽዋማት በደንብ የማይጾም ሰው እንዴት ለሶስት ቀን ጾም ለምን ታምር ይፈጥራሉ እንደውም ተረፈ ጾም ናትና ለምን ቢሉ ጾሙቀን ብቻ ነው። አንድም ሸክም ማብዛት ነውና። ምክንያቱም ጌታም ሸክም አታብዙባቸው ብሏልና»x ይላል።
ኅሊና ያለው ሰው በእውነት ጾምን ሸክም ነው ሊል ይችላል? ብሉ ጠጡ ጾም ሸክም ነውና እያለ የሚሰብክ መምህር በእውነት ጤነኛ ነው ትላላችሁ? ለማንኛውም ጾመ ነቢያትን ወደ ማብራራቱ መቼ እንደምንጀምር መቼ እንደምንጨርስ እንመልከት።
ቅብዐቶች ጾመ ነቢያትን የሚጀምሩት ኅዳር ፲፱ ቀን ነው የሚጨርሱት ደግሞ ኹልጊዜ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ነው። እኛ ግን የምንጀምረው ኅዳር ፲፭ ቀን ሲኾን የምንጨርሰው ደግሞ በሦስቱ ዘመናት ታኅሳስ ፳፱ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ታኅሳስ ፳፰ ቀን ነው። ይህ የቀኖና ልዩነት ከየት መጣ? በዝርዝር እንመልከት።
============
ጾመ ነቢያት
===========
ደራሲው የነቢያት ጾም መግቢው ኅዳር ፲፱ ቀን ነው ይላል። ለዚህም እንደ ምክንያት ያስቀመጠው ነቢያት የጾሙት ቀናትን ስለኾነ ኅዳር ፲፱ ጀምረን ታኅሣሥ ፳፱ ስንገድፍ ቀን ይኾናል የሚል ነው። በመዠመሪያ ጾም ማለት ቀን መቁጠር ማለት አይደለም። እስኪ ዐቢይ ጾምን ተመልከቱ። ጌታ የጾመው መዓልት እና ሌሊት ነው እኛ ግን ፲፭ ቀናትን ጨምረን ፶፭ ቀናትን ነው የምንጾም። ለምን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከቻሉ ይሞክሩ ካልቻሉ ግን ጾም ማለት ቀን መቁጠር ማለት ስለልኾነ ነው ብለን በዚህ እንረታቸዋለን። ቀን መቁጠር ከተጀመረ ግን ዓቢይ ጾምም ክርክር ሊያስነሣ ይገባው ነበር ማለት ነው። በዚያውስ ላይ የእኛ ጾም እንደ ነቢያቱ እንደነሙሴ እንደነኤልያስ እንደነዳንኤል ኾኖ ሞቶ ነው እንዴ ከእነርሱ ጋር የምናነጻጽረው?
ደራሲው ጾመ ነቢያትን በተመለከተ ከ፵ ቀናት በላይ በትርፍነት የተጨመሩትን ቀናት አስመልክቶ ሲናገር፡-
አንባቢያ ሆይ አንድ ነገር ልብ የምትሉት ነገር አለ ይኸውም ሐዋርያትና ሰለስቱ ምዕት የደነገጉትን ያቆዩትን ነው የምንከተለው ወይስ? አብርሃም ሶርያዊ የጨመረውን ጭማሪ»x በማለት ቅዱሳንን በመናቅ ሲናገር አስተውለናል። ይህንን አልቀበልም ካለ ዐቢይ ጾም ላይ ጾመ ሕርቃል ለምን ተጨመረ? ብንለው ዝም ከማለት ውጭ መልስ የለውም። ሠለስቱ ምእት እኮ የወሰኑት ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ጾመ ኹሉ እናንተም በጥንቃቄ ጹሙት ብለው ነው። ታዲያ ጾመ ነቢያት ላይ ሲኾን ልብላ ልብላ ማለት ከምን የመጣ ነው?
ጾመ ነቢያት የገና ጾም በመባልም ይታወቃል። ነቢያት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እየጠበቁ አምላክ ይወርዳል ይወለዳል ብለው የጾሙት ነው። ይህ ጾም በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ኅዳር ፲፮ ይጀምርና ታኅሣሥ ፳፱ ይፈሰካል፤ በዘመነ ዮሐንስ ግን ኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ይፈሰካል።  በአራቱም ዓመታት ፵፫ ቀናትን ይጾማል ማለት ነው። ነገር ግን ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኅዳር ፲፭ የሚገባው ጾም ስለሚረሳ ኹልጊዜ ኅዳር ፲፭ ይጀምራል ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ በማያዳግም መልኩ ተወስኗል። በዚህ የተነሣ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናት በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ፵፫ ቀናት ይጾማሉ። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጾሙ ቀናት ቀን ይቀንሳሉ፤ በሦስቱ ዘመናት ፵፬ ቀናትን የምንጾመው ለጾም ማድላት ተገቢ ስለኾነ ነው። ይህንንም ፍትሐ ነገሥት ፲፭÷፭፻፹፬  ላይ፡-
«ዳግመኛም ቢቻላችሁ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ በማለታቸው ይህን ሕግ እነሆ ወሰኑ በጾሙ ምክንያት ጠብ ክርክር ቢኾን መጾም ይገባል። ከመብላት በጣም ይሻላል» ብለው አዘዙን።
በጾም ወቅት እንብላ እና እንጹም የሚል  ክርክር ከተፈጠረ መጾም ይሻላል ምክንያቱም ከመብላት በጣም ይሻላልና ብለው በአንድ ዐረፍተ ነገር አሠሩልን። ከዚህ ወዴት እንሸሻለን? ብሉባቸው ባልተባልንባቸው ቀናት እንብላበት እና እንጹምበት የሚሉ ሰዎች ቢከራከሩ እንጹምበት ያለው እንዲረታ በዚህ እወቁ። ስለዚህም እንብላ ባይ ቅብዐቶች እና እንጹም ባይ ተዋሕዶዎች ስለጾም ቢከራከሩ በዚህ አንቀጽ እና ቊጥር መሠረት እንጹም የሚሉ ተዋሕዶዎች እንደሚረቱ የታወቀ ነው። እንዳንጾምባቸው ከታዘዝንባቸው ቀናት ውጭ ብንጾም በረከት እንጂ መርገም አያገኘንምና።
በዚህ ጾም የሚነሣው መሠረታዊ ጉዳይ ነቢያቱ አርባ ቀናትን ብቻ ነው የጾሙት ይህ በትርፍነት የተጨመረው አራት ወይም ሦስት ቀን ከየት መጣ የሚል ነው። ለዚህ መልሱ፡-
&  ፩ኛ. ፍትሐ ነገሥቱ ፲፭÷፭፻፷፰ ላይ «ከእነርሱም የሚያንስ እንደ ረቡዕና እንደ ዓርብ የሚ አለ። ይኸውም ከልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ነው። መዠመሪያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የገና በዓል ነው» በማለት መዝግቦት እናገኘዋለን። በእኛ አቈጣጠር መሠረት የኅዳር እኩሌታ ደግሞ ለት ተከፍሎ ግማሹ ወደታች ግማሹ ወደ ላይ ነው። በዚህም መሠረት የኅዳር እኩሌታ ማለት ኅዳር ፲፮ ስለ ጾሙ በዚህ ቀን ይጀምራል ማለት ነው። መንፈቅ የምንለው ኅዳር ፲፮ን እንጂ ኅዳር ፲፱ አይደለም ማለት ነው። ኅዳር ፲፱ እንጀምራለን የሚለው የቅብዐቶች አነጋገር እና ተግባር በዚህ መሠረት ውድቅ ናል ማለት ነው። ኖም ግን ስንክሳሩ ይህ ፲፮ የሚለውን ፲፭ ያደርገዋልና የማያዳግመው ውሳኔ በሲኖዶስም የጸደቀው ኅዳር ፲፭ የሚለው ነው። ስንክሳሩም እንደሚከተለው ይነበባል።
&  ፪ኛ. ስንክሳሩ ኅዳር ፲፭ ቀን «ወበዛቲ ዕለት ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘውእቱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት ዘሠርዕዎ ክርስቲያን ያዕቆባውያን ዘግብጽ - በዚችም ቀን የስብከተ ጌና ጾም መዠመሪያ ነው። ይህ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተወለደበት በግብጽ የሚኖሩ ያዕቆባውያን የሠሩት ነው» በማለቱ የኅዳር እኩሌታ የሚለው በግልጽ ኅዳር ፲፭ ነው ብለን በዚህ ቀን ጾማችንን እንጀምራለን። ስንክሳሩ ኅዳር ፲፱ ቀንን «ወበዛቲ ዕለት ኮነ ጾመ ስብከተ ጌና ዘሮም ወአፍርንጊ ወሶርያ ወአርማንያ ዘእንበለ ግብጽ ወኢትዮጵያ ወኖባ - በዚችም ዕለት የሮም፣ የአፍርንጊ፣ የሶርያ፣ የአርማንያ ክርስቲያን ከግብጽ ከኢትዮጵያና ከኖባ በቀር የስብከተ ጌና ጾምን የሚጀምሩበት ነው» ይለዋል ከዚህ እንደምንረዳው የቅብዐት እምነት የትመጣው ሲታይ ሮም እንደ ነው። ሮም ደግሞ ካቶሊካውያን ናቸው። ስለዚህም የቅብዐት እምነት ከካቶሊክ የመጣ ነው ቢባል ሐሰት አይደለም ማለት ነው።
&  ፫ኛ. ሐዋርያው ፊልጶስ ኅዳር ፲፮ ቀን በሰማዕትነት ካሳረፉት በኋላ ሥጋውን ሊያቃጥሉ ሲነሡ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋውን ሰወረባቸው። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ከዕለቱ ጀምረው ቀናትን እንደጾሙ በኅዳር ፲፰ ሥጋውን ሰጣቸውና ቀበሩት። ስለዚህም ሦስቱ ቀናት ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ተጨመረ። መምህር ወልደ አብርሃም፣ ምስጢረ ተዋዶ፣ ገጽ ፺፬።
&  ፬ኛ. በዓለ ልደት ረቡዕና ዓርብ ቢውል ይበላበታልና ለዚያ ማካካሻ ወይም ምትክ የምት ጾም የገሐድ ጾም አንድ ቀን ከጾመ ፊልጶስ በፊት ተጨመረችና ኅዳር ፲፭ ቀን እንዲጾም አዘዙን። ጌታ የጾመው ጾም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሳለ ፶፭ ቀናትን እንደምንጾመው ያለ ነው። የመዠመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል የመጨረሻውን ሳምንት ደግሞ የሕማማት ሳምንት በማለት እንደምንጾመው ይህንንም እንዲሁ አደረግን። ይህም የአባቶቻችን ትእዛዝ የአባቶቻችን ሥርዓት ነውና እኛም ተቀበልነው። አስቀድመን እንደተናገርነው በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ መጾም ከመብላት እጅግ ይሻላል እንዳሉን እንጾመው ዘንድ ይገባናል።
&  ፭ኛ. አብርሃም ሶርያዊ ከኅዳር ጾም አስቀድሞ እንዲጾም አዝዟልና ነው። በስምዖን ጫማ ሰፊው አማካኝነት ተራራውን ያፈለሱበትን ድንቅ ተአምር ማሰቢያ አድርገው ይጾሙታልና ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ተብሎ እንደ ተጨመረም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስተምራሉ። ደራሲው ግን የአብርሃም ሶርያዊ ጾም እያላችሁ አትጹሙ በማለት ምእመናንን ወደ ፕሮቴስታንታዊ አስተሳሰብ እንዲሸጋገሩ ደክሟል። ኾኖም ግን ዐቢይ ጾም ላይ ሳይቀር ጾመ ሕርቃል ብለን በአንድ ሰው ስም ተሰይሞ እንጾማለንና አብርሃም ሶርያዊም በስሙ ጾም ቢሠየምለት ስሕተት አይደለም።
&  ፮ኛ. ጾሙ መግቢያው ኅዳር ፲፭ ንና ቀናት ተጨምረው ታኅሣሥ ፳፭ ያልቃል ከዚህ ጀምሮ እስከ ገና በዓል ድረስ ያሉ ቀናትን መርአዊ ብለን እንጾመዋለን የሚሉም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አሉ።
&  ፯ኛ. የቤተክርስቲያናችን ትልቁ ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖደስ ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ኅዳር ፲፭ ይጀመራል ብሎ ወስኗልና መግቢያው ኅዳር ፲፭ ነው እንላለን።
ደራሲው ግን ምንም ማስረጃ ሳያስቀምጥ፣ ሳይሰጥ እና ሳይጠቁም ቅዱሳንን በመናቅ እና በመንቀፍ ጾመ ነቢያት ኅዳር ፲፱ ቀን ይገባል ብሎ የጻፈው ጽሑፍ በእነዚህ ሰባት መሠረታዊ ማስረጃዎች መሠረት ወደ ጥልቁ መቃብር ቀብረነዋል። ደራሲው በዚህም አለ በዚያ አባቶቻችን ሠለስቱ ምእት የጾሙ መግቢያን «መንፈቁ ለኅዳር» ብለው ወስነውታልና ፲፱ ቀን ይገባል ማለቱ ክሕደት ነው የአበውን ሥርዓት እና ሃይማኖትም መንቀፍ ነውና ተመለስ ይዘኸው የጠፋኸውን ነፍስም ወደ እውነተኛው መንገድ መልስ እንላለን።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት / ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment