Tuesday, October 9, 2018

የርክበ ካህናት ሲኖዶስ እና ተስፈኛው ተጓዥ

በሕገ ቤተክርስቲያናችን መሠረት የቤተክርስቲያናችን ወሳኝ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ኹለት ጊዜ ለቤተክርስቲያናችን ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ለመወሰን ጉባዔ ያደርጋል። በዚኽ መሠረት ነው በርክበ ካህናት የሚጀመረው የዘንድሮው ዓመት ኹለተኛው ሲኖዶስ ስብሰባ ነገ የሚጀመረው። ነገ ረቡዕ ሚያዝያ ፳፬/፳፻፲ ዓ.ም በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የቤተክርስቲያናችን ዐበይት ጉዳዮች እንደሚዳሰሱበት እናምናለን። የቅዱስ ሲኖዶስን ስብሰባ ተከትሎ የአባትነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማሳሰብ በርካታ ተስፈኛ ተጓዦች በጸሎቱ መርኃ ግብር እየተገኙ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
በተለይ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ከተስፈኛ ተጓዦች መካከል ወደር ያልተገኘላቸው መኾናቸው የታወቀ ነው። አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን ከተቆጣጠሩበት ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰበሰብባቸው ጉባዔያት ኹሉ አቤቱታውን ሳያሰማ ቀረበት ቀን ያለ አይመስለኝም። የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ጆሮ የሚሰጥ አካል አለመገኘቱ ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ሲሰበሰብ ለማሳሰብ ብቻ ሳይኾን ከስብሰባ በፊትም የምእመናን ተወካዮች ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት እየሄዱ ስለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን አቤት ማለታቸው የአደባባይ ሐቅ ነው። ስለቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት ሲሉ ስለምእመናንም ድኅነት ሲሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አንድ እልባት መስጠት ቢችሉ ምንኛ በተደሰትን ነበር። ግን አልኾነም።
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ላይም በመደገፍ እና በመቃወም ላይ በኹለት ሐሳብ ተከፍለው የሚታዩ ናቸው። ፓትርያርኩ፣ አቡነ ማርቆስ፣ አቡነ ቶማስ፣ አቡነ አረጋዊ በአንድ መስመር ለጥፋት ሌሎችም እንደ እነ አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ አቡነ ቀውስጦስ፣ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ኤልሳዕ ወዘተ የመሳሰሉት ደግሞ በሌላ መስመር ለምእመናን ድኅነት ተሰልፈዋል። በእርግጥ ወደየትኛው ማዘንበል እንዳለባቸው ግራ ተጋብተው መሐል ላይ ያሉም አይታጡም። ያም ኾነ ይህ ግን መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ለጥፋት የሚሮጡትን አፋቸውን እየከፈተ ፊታቸውንም እየጸፋ ለምእመናን ድኅነት ወደሚተጋው እውነተኛ መንገድ መምጣታቸው አይቀርም የጊዜ ጉዳይ እንጂ።
አቡነ ማርቆስ ከምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ጋር ሳይግባቡ ይኼው ፮ ዓመታት ተቆጠሩ። ይህን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ ይፈታው ዘንድ ምእመናን በራሳቸው ወጭ ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል። የዛሬው ጉዞ ፲፩ኛ መኾኑ ነው እንግዲህ። መናፍቃን በቤተክርስቲያናችን ካደረሱት ፈተና ይልቅ አቡነ ማርቆስ ያደረሱባት በደል የከፋ ነው። ይህን የተረዳው ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው የጥቅምት ሲኖዶስ ስብሰባ ይህ ኹሉ ችግር እንዲፈታ አጣሪ ኮሚቴ ወደቦታው እንዲሄድ መወሰኑ አይዘነጋም። ሆኖም ግን ለብር እንጅ ለቤተክርስቲያናችን ክብር የማይጨነቅ አባል የኮሚቴው አባል ኾኖ መምጣቱ ጉዳዩን የከፋ ማድረጉ አይዘነጋም። ምእመናንን ሳያወያይ ከቤተክርስቲያን ሳይኾን ከአቡነ ማርቆስ ደጋፊዎች ጋር ብቻ ተወያይቶ ያንን ወስዶ ለጠቅላይ ቤተክህነት በዘገባ መልኩ ማቅረቡ ይታወሳል። የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ብጹእ አቡነ ዲዮስቆሮስ ግን አጣሪ ኮሚቴው ባሳየው ኢክርስቲያናዊ ተግባር ማዘናቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም። ወደቦታው ሌላ አጣሪ ኮሚቴ እንደሚላክም አሳስበው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሚቀያየሩበት የመጨረሻው ቀን ላይ አቡነ ማርቆስ የእኔ ጉዳይ ከዚህ በኋላ እንዳይታይ አጀንዳየ እንዲዘጋልኝ እጠይቃለሁ በማለት እርሳቸው አባል በነበሩበት የመጀመሪያው ቋሚ ሲኖዶስ አቤቱታ ያቀረቡት። ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ በምልዓተ ጉባዔው እንጅ በቋሚ ሲኖዶሱ መታየት አይገባውም በሚለው የአቡነ ሳዊሮስ (የሲኖዶስ ጸሐፊ) ሰፊ ክርክር ተደርጎበት ስብሰባው ያለስምምነት ተበትኖ እንደቀረ የታወቀ ነው። እንዲያውም ቃለጉባዔውን ይጽፍ የነበረው ሰው የእርሳቸው ጉዳይ እንደተዘጋ አድርጎ ቃለጉባዔውን ጽፎ ሳያነቡ እንዲፈርሙ አድርገው ነበር። ነገር ግን ስለቤተክርስቲያናችን ተግተው እየሠሩ የሚገኙት ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ ቃለ ጉባዔውን አስነብበው በውይይታቸው ያልተካተተ ሐሳብ ተካቶ ስላገኙት ቃለጉባዔውን ሳይፈርሙ እንደወጡ የታወቀ ነው።
ተስፈኛው ተጓዥ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ዛሬም እልህ አስጨራሹን ረዥም መንገድ እየተጓዙት ነው። ፲፩ኛውን ጉዞ ዛሬ በምእመናን ተወካዮች ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ እያደረገ ነው። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ይህን ስለአንዲት ቤተክርስቲያን ለ፲፩ኛ ጊዜ እየደከመ ያለውን ምእመን መልካም አቀባበል ያደርጉለታል ተብሎ ይጠበቃል። አባቶቻችን ሆይ በደሙ ስለገዛን ስለክርስቶስ ኢየሱስ ብላችሁ የቤተክርስቲያናችንን ጉዳይ በትኩረት ተመልከቱት። ምሥራቅ ጎጃም የቀደመ ክብሩን የቀደመ ማንነቱን ሃይማኖታዊ ተግባሩን በሚገባ እንዲፈጽም እንቅፋት የኾኑትን ኹሉ እንድታስወግዱልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን። እንቅፋቶቹ ብዙዎች ናቸው በጣም ብዙዎች እንደእኛ ግን አቡነ ማርቆስ ትልቁ እንቅፋታችን ኾነዋል። ይህንን ለ፲፩ኛ ጊዜ የሄደውን የምእመናንን ተወካዮች ጉዞ ተከትሎ የአቡነ ማርቆስ ደጋፊዎች (በግድ እንድትመጡልኝ የተባሉት) ነገ መሄዳቸው አይቀርም። እነርሱ በቤተክርስቲያን በጀት ቤተክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ይተጋሉ የምእመናን ተወካዮች ደግሞ ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ ቤተክርስቲያንን ይታደጋል። እግዚአብሔር ያሸንፋል አንጠራጠርም። የተስፈኛው ተጓዥ አሁንም እየተጓዘ ነው። አበው ሊቃነ ጳጳሳትም መልካም አቀባበል ያደርጉለታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እግዚአብሔር አምላክ ስለቤተክርስቲያናችን ሲል መልካሙን ኹሉ እንዲያሳስባቸው እንለምናለን።


✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሚያዝያ ፳፫/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment