Tuesday, October 9, 2018

የቅብዐት እና የተዋሕዶ ልዩነት….. ክፍል ፩



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የቅብዐትን እና የተዋሕዶን ልዩነት ከመሠረቱ ለመመልከት በመጀመሪያ ቅብዐት ወደ ሀገራችን እንዴት እንደገባ ታሪካዊ አመጣጡን በሚገባ መመልከት ያስፈልጋልና ወደዚያው እናቀናለን። ይህን የታሪክ መረጃ ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ መድሎተ አሚን ከተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ዋዜማ ከተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲሁም የታሪክ ጸሐፊው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ መጻሕፍት እና በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ በጻፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ ያለ ነውና ኹሉም የሚስማማበት ታሪክ ነው።
ማንኛውም ማስረጃ ጠቅሶ በታሪኩ ላይ መከራከር በሳል ሐሳብ መስጠት መመካከር ይችላል ከዚህ ውጭ ግን እንዳልተማረ ሰው ለስድብ አፉን የሚከፍት ሰው ካለ በእርሱ ከምናዝን በቀር በእኛ ላይ ምንም ሊመጣ የሚችል ነገር አይኖረውም። ይህን መጻፍ ስጀምርም ሳያውቁ የጠፉትን ወገኖቻችንን ለማስረዳትና ወደ እውነተኛዪቱ መንገድ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። መማር የሚፈልጉ ብዙ ነፍሳት ስላሉ ስለእነርሱ ስንል እውነቱን እውነት ሐሰቱን ከማለት በቀር ሌላ አማራጭ የለውም። ስለዚህ በማስረጃ እውነቱን እውነት ሐሰቱንም ሐሰት ነው በማለት እንድንነጋገር አሳስባለሁ።
የቅብዓት ምንፍቅና ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባ?
ለዚህ እምነት ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያቱ ግራኝ አህመድ የተባለው አረመኔ እስላም ነው፡፡ በ፲፬፻፶፫ . የቱርክ እስላሞች ቊስጥንጥንያን እና ሞንጎልያን ከያዙ በኋላ ከዐረብ እስላሞች ጋር ኃይላቸውን አስተባብረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኃይላቸው እየጨመረ ስለሄደ የክርስትና ሀገራትን በመውረር እስልምናን በግድ በሌሎች ላይ መጫናቸውን ተያያዙት፡፡ ወደ አፍሪካም በመግባት ሰሜን አፍሪካን የራሳቸው ግዛት በማድረግ ዓላማቸውን አስፈጸሙ፡፡ ሆኖም ግን ወደ ኢትዮጵያ መግባትና እምነታቸውን ማስፋፋት አልቻሉም ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሀገራችን ተወልዶ የሀገራችንን ውኃ ጠጥቶ የሀገራችንን እህል ተመግቦ ያደገው ግራኝ አህመድ ክርስቲያኖችን በመደምሰስ አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል ክርስትናን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ከቱርክ እስላም ባለሥልጣናት ጋር ወዳጅነቱን ጀመረ፡፡ የዚህ የግራኝ መሐመድ ድብቅ ሴራ ከቤተመንግሥት እንደደረሰ ባለሥልጣናቱ ከክርስቲያን ሀገሮች እርዳታ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ነገር እነዚህ ለእርዳታ ጥያቄ የቀረበላቸው ሀገራት ካቶሊካውያን ስለሆኑ እርዳታውን አዘግይተውታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበሯ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ለይታ የራሷ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሳካላት ስላልቻለ አሁን የቀረበውን የእርዳታ ጥሪ ለመስማት ዘግይታለች፡፡ ግራኝ መሐመድም በኅቡእ ያደራጀውን የጥፋት ወታደር አሰልፎ በድብቅ ከቱርክ እየተላላከ ያስመጣውን መሣሪያ አስታጥቆ በሀገራችን ላይ በጠላትነት ተነሣ፡፡ በዚህ የሃይማኖት ወረራ ላይ የቤተክርስቲያናችን ውድ ቅርሶች፣ መጻሕፍት፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ ምእመናን አንገታቸው ለስለት ደረታቸው ለጥይት ኾነ፡፡ ብዙዎች በሰማእትነት አለፉ የክርስቲያኖች እልቂት ኾነ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ የእስልምናን እምነት በግድ ተቀበሉ እየተባሉ ሳይወዱ ከሞት ለማምለጥ ብቻም እምነታቸውን ለውጠው እስላም የሆኑም አልጠፉም፡፡ በዚህ የጥፋት እና የእልቂት ዘመን ኹሉ ክርስትና አልጠፋችም፡፡ ይህን የግራኝ ወረራ ለማስቆም ሀገራችን የፖርቹጋሎችን ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ይህን ውለታ ነው እንግዲህ ለሃይማኖታቸው ማስፋፊያነት እንደ ምክንያት የተጠቀሙበት፡፡ የፖርቹጋሎችን ድጋፍ የጠየቁት ዐፄ ልብነ ድንግል ሲሆኑ ድጋፋቸው የደረሰው እና ግራኝን ድል ለማድረግ የተቻለው ግን በልጃቸው በዐፄ ገላውዴዎስ ዘመን የካቲት ፳፩ ቀን ፲፭፻፵፪ . ነበር፡፡ ከዚህ የግራኝ መሸነፍ (መገደል) በኋላ የፖርቹጋሎችን ትብብር ምክንያት በማድረግ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ባለሥልጣኖች በተላላኪያቸው ቤርሙዴዝ አማካኝነት አንድ ጥያቄ ለገላውዴዎስ አቀረቡ፡፡ ቤርሙዴዝ ገላውዴዎስን እንዲህ አለው ‹‹ገላውዴዎስ ሆይ አባትዎ እርዳታ እንድናደርግላቸው ሲጠይቁን ከሀገራችሁ መሬት ቆርሰው ሊሰጡን እና የሀገራችሁ ብሔራዊ ሃይማኖት የሮማ ክቶሊክ እንዲኾን ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከግብጽ የሚመጡት ጳጳሳት ቀርተው ጳጳሳቱ ከሮማ እንዲመጡ ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን አባትዎ የገቡልንን ቃል ኪዳን ይፈጽሙልን እኔም የመጀመሪያው ጳጳስ ልሁን›› አላቸው፡፡ ገላውዴዎስ ግን ‹‹ሀገራችንን ቆርሰን አንሰጥም፣ ሃይማኖታችንንም አንለውጥም፣ ጳጳሳትንም ከግብጽ ማስመጣታችንን አቁመን ከሮማ አናስመጣም ላደረጋችኹልን ትብብር ግን ገንዘብ እንከፍላችኋለን›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ቤርሙዴዝ በጣም ተናደደ ከንጉሡ ከገላውዴዎስ ጋርም ተጣላ፡፡ በዚህ ጠብና ክርክርም የተነሣ የተናደደው ቤርሙዴዝ ፲፭፻፶፱ . ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለፖርቹጋል ቤተ መንግሥትና ለቫቲካን ቤተ ክህነት የኾነውን ኹሉ ነገራቸው፡፡
በወቅቱ የነበሩት የሮማው ጳጳስና የፖርቹጋሉ ንጉሥ በዚህ የቤርሙዴዝ መግለጫ ላይ በጥልቀት ከተወያዩበት በኋላ ሌሎች ሚሲዮኖችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የካቶሊክ እምነት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ ወዘተ አሰልጥነው ዐሥር የሚሆኑ ሚሲዮኖችን ወደ ሀገራችን ላኩ፡፡ በዚህ ጊዜ የሀገራችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደ አባ ዝክሪ እና እንደ አባ ጳውሊ ያሉት ከጳጳሳቸው ከአቡነ ዮሴፍ ጋር ኾነው ሚሲዮናውያኑን ተከራከሯቸው፡፡
 ✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ግንቦት ፲፪/ ፳፻፲ .
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment