Tuesday, October 16, 2018

ትግላችን ስለአንዲት ቤተክርስቲያናችን ነው!



==========================






ከወደ ምሥራቅ ጎጃም ስለቤተክርስቲያናችን እየተሰማ ያለው ዜና መልካም ነው፡፡ አቡነ ማርቆስ ሀገረ ስብከቱን ለቀው ከሄዱ ቆይተዋል፡፡ ኾኖም ግን አዲስ ሊቀ ጳጳስ መንበረ ጵጵስናውን እስካልተረከበ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለቀዋል ማለት አንችልም፡፡
ብጹእነታቸው አቡነ ማርቆስ ከዚህ ቀደም በተደረጉ የተቃውሞ ጎዞዎች እኔ ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ ነበር፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንስ ቢኾን ካጠፉ ሊከስዎት አይችልምን ተብለው ሲጠየቁ ደግሞ ማንም የማያውቃቸው የማርቆስ ዱርየዎች ናቸው ሲሉም ነበር፡፡ ቤተክርስቲያንን ለመታደግ ጎን ለጎን ኾኖ የጎሪጥ ተያይቶ የሚኾን አይደለም፡፡ ምእመናን በአንድ ወገን ካህናት እንባረራለን በሚል ፍርሐት በሌላ ጎን ኾነን ስንታገል ይኸው ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡የዘንድሮው ትግል ግን የፍጻሜ ትግል ይመስላል፡፡ ይህን የምለውም፡-
1ኛ. ኹሉም ካሕናት ከምእመናን ጋር ኾነው መነጋገር መወያየት ጀምረዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት በተደረጉ ብዙ ስብሰባዎች ላይ ካህናት ዲያቆናት ከምእመናን ጋር ኾነው አቡነ ማርቆስን መሞገት ጀምረዋል፡፡ ይህን በማድረጋቸውም የሚደርስባቸውን መከራ ግፍ ከሥራ መባረር ኹሉ በአኮቴት እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡
2ኛ. ለሃይማኖቱ ዘብ የቆመው ወጣት በራሱ ጊዜ ያለማንም ቀስቃሽ አባ ማርቆስ ጎጃምን ዳግም ቢረግጡ ችግር ይፈጠራል ብለው መንግሥትንም ጫና ፈጥረውበታል፡፡
3ኛ. በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት የዞኑ አስተዳዳሪ እና የከተማዋ ከንቲባ ለከቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ በመጻፍና በአካል ችግሩን በማሳወቅ አባ ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ቢመጡ ብጥብጥ ይፈጠራልና በእናንተ በኩል ስለእምነቱ ተከታዮች ስትሉ መፍትሔ ፈልጉ ማለታቸው፡፡
በእነዚህና በመሣሠሉት ጉዳዮች መነሻነት የአቡነ ማርቆስ መጨረሻቸው እንደኾነ ተረድተናል፡፡ ምእመናን 11 ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ በመሄድ በትዕግሥትና በልጅነት መንፈስ አቡነ ማርቆስ እንዲነሡ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 3 ጊዜ ለክልሉ ጸጥታ ዘርፍ 3 ጊዜ ለፌዴራል አርብቶ አደሮችና … ጉዳዮች ሚኒስትር በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ኾኖም ግን እስካሁን ድረስ መፍትሔ አልተገኘም ነበር፡፡ ዘንድሮ ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስን እንጠይቃለን፡፡
ከዚህ በፊት ምእመናን በሄዱ ማግስት በቤተክርስቲያኒቱ ገንዘብ አበል እየተከፈላቸው ለሆዳቸው ያደሩ ካህናት እየሄዱ አባ ማርቆስ አይነሡብን ሲሉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ካህናትም ከምእመናን ጋር ኾነው አባ ማርቆስን አንፈልጋቸውም ሊሉ ተዘጋጅተዋል፡፡ ጎንቻን ተነሥ በለው ማርቆስ ላይ ማንም አልተቀበለኝም ያሉት ብጹእነታቸው ጎንቻን በዓይነኩሉ እና በዕዝራ አማካኝነት እንዲደግፋቸውና ቅዱስ ሲኖዶስን እንዳይነሡ እንዲጠይቁ አደራጅተዋል፡፡ ያም ኾነ ይህ ግን ከእነርሱ ጋር ያሉት ጥቂት የውሸት እና የጥፋት ኃይሎች ከእኛ ጋር ካሉት ብዙ የቤቱ ቅናት ካቃጠላቸው ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ በብዛትም በጥራትም፡፡
ትናንት በጀመረው 37ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ምሥራቅ ጎጃም ኹለት ሥራ አስኪያጅ ኹለት ጸሐፊ ለስብሰባው የቀረቡበት ብቸኛው ሐገረ ስብከትም ኾኖ ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚያውቀው ሥራ አስኪጅ ሊቀ ብርሐናት ከሐሊ በቃሉ እና ፀሐፊው አባ ወልደ ትንሣኤ ከምእመናን ጋር ኾነው አባ ማርቆስ እንዲስተካከሉ በመጠየቃቸው የውሸት ሪፖርት እንደማይቀርብላቸውና ኹልጊዜ የወንጌል እና የልማት አባት እየተባሉ የሚሸለሙትን ሽልማት እንደማያገኙት በማረጋገጣቸው ዋናውን ማኅተም ማግኘት አልችል ሲሉ ያለጠቅላይ ቤተክህነት እውቅና ማኅተም አስቀርጸው የራሳቸው የሚሏቸውን ሰዎች ሥራ አስኪያጅና ፀሐፊ አድርገው ሾመዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ኹለቱም ወደ ስብሰባው ያመሩ ሲኾን አባ ማርቆስ በሐሰተኛ ማኅተም የሾሟቸው አዲሶቹ የሊቀ ጳጳሱ ቀኝ እጆች ተቆርጠው ተጥለዋል፡፡ ምሥረቅ ጎጃም ሐገረ ስብከትንም ወክለው እንደማይቀመጡ ተነግረው አድማጭ ብቻ ሊኾኑ ተቀምጠዋል ተብሏል፡፡
ስለዚህ በዚህ ጉባዔ ላይ ምሥራቅ ጎጃምን ወክለው ሪፖርት የሚያቀርቡት ሊቀ ብርሐናት ከሐሊ በቃሉ ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ሊቀ ብርሃናት ከሐሊ ደግሞ እውነተኛውን ነገር እንደሚናገሩ፣ ሀገረ ስብከት መታሸጉን፣ ምንም ሥራ እየሠሩ እንዳልኾነ፣ አባ ማርቆስ ባደራጇቸው ሰዎች ምክንያት መዝገብ ቤት ሠራተኛዋን እንዳንገራገሩ፣ ማኅተሙን ከመዝገብ ቤት ለመውሰድ ጥረት እንዳደረጉ፣ ምእመናን ከዳር ዳር እንደተነሣባቸው እውነቱ ይፈርጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ያም ኾነ ይህ ግን እኛ የምንፈልገው አቡነ ማርቆስ ሐገረ ስብከታችንን እንዲለቁልን ብቻ ሳይኾን በቀኖና ተለይተው ንስሐ እንዲሰጡ ጭምር ነው፡፡
አቡነ ማርቆስ ለተሐድሶዎች ወለል ያለ በር ከፍተው ምእመናንን ያስነጠቁ ልባቸውንም ያሸፈቱ ናቸው፡፡ ካህናት ያውቃሉ ምእመናን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በመሳቅ እንደ ቀልድ ቆጥረው ነው የሚሄዱት፡፡
ብዙ ነገሮችን በእርሳቸው ደረጃ መባል የሌለባቸውን ነገሮች ብለዋል፡፡ ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም ላይ ቤተልሄም ሲመርቁ ይችን እንደ ኩሽና ቤት ያንን እንደ አዳራሽ ቁጠሩት ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያንን እንደ አዳራሽ ቁጠሩ የሚል ሥገፋ እና ደሙ የሚዘጋጅበትን  እንደ ኩሽና ቤት ቁጠሩት የሚል ሰው የተዋሕዶ ነው ማለት ይከብዳል፡፡
ትናንት ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል በተካሄደው ውይይት ላይ አንድ አባት እየቀፈፋቸው አንድ ነገር ተናግረዋል፡፡ ይህንን ግን እዚህ ላይ መጻፍ እኔንም ይቀፈኛል፡፡ ደግሞም መጻፍ አልፈልግም፡፡ የዚህ ንግግራቸው በቀጥታ የተሐድሶዎች ሃሳብ እንደኾነ ግን በዕለቱ የነበሩ ኹሉ ታዝበዋል፡፡
የዘንድሮውን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አባ ማርቆስ የሚነሡበት እንዲኾን በተለይ አቡነ ዘካርያስ እውነታውን ስለሚያውቁት ብዙ ነገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም የጻፉት ደብዳቤ ያንን በትክክል የሚያስረዳ ነው፡፡ ኾኖም ግን የዚህን ሀገረ ስብከት ተረካቢ ማን ሊኾን ይችላል በሚለው ላይም ውይይት ቢደረግ መልካም ነው፡፡ አቡነ ማርቆስን አስወግዶ አባ ቶማስን ቁጭ ቢያደርጓቸውስ? አባ ቶማስ የአዊ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው ኹሉ ነገራቸው እንደአባ ማርቆስ ነው፡፡ እርሳቸውንም ተቃውመው ይነሡልን የሚሉ ድምጾች በዘንድሮው የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ መሰማታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነርሱ ይነሡ ያሏቸውን አንሥተው ምሥራቅ ጎጃም ላይ ቢመድቧቸውስ? ነገም ተቃውሞ ልናሰማ ነው እስከ መቼ? ለኹሉም ነገር አምላክ እርሱ ይኹነን፡፡
በትናንትናው ስብሰባ ላይ በጣም ደስ የሚል ንግግር ሰምቻለሁ፡፡ ‹‹የእኛ ትግል ጥቅም ፈልገን አይደለም የእናንተን የካህናትን ቀንበር ለማስወገድ ነው፡፡ እኛ የራሳችን ሥራ አለን፡፡ እንበላለን እንጠጣለን በዚያ ዙሪያ ከቤተክርስቲያን 05 ሳንቲም አንፈልግም፡፡ እናንተ ግን ቀንበራችሁ እንዲነሣላችሁ እንታገላለን፡፡ እኔ እየበላሁ አባቶቼ ጦማችሁን አታድሩም አፈር ልብላላችሁና›› ብሎ ሲናገር ልቤን ነክቶታል፡፡ በእውነት ካህናት ዛሬ ያነሡኝ ነገ ያነሡኝ እያሉ መጨነቅ የለባቸውም፡፡ የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን ተማሪዎቻቸውን በአግባቡ እንዲያስተምሩ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ትግላችን ይቀጥላል፡፡
ስለአቡነ ማርቆስ አቡነ ዘካርያስ የጻፉትን ደብዳቤ ከታች ተመልከቱት፡፡
#share ማድረግ ይጠቅማል፡፡
======================
ጥቅምት 06/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment