፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
«ቀብዐ» የሚል ቃል በመያዛቸው ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ
ምእመናንን ግራ ለማጋባት የሚሞክሩ የቅብዐት አስተማሪዎች በዝተዋል። ስለዚህ «ቀብዐ» የሚለው ቃል አነገሠ፣ አከበረ፣ ሾመ፣ አዘጋጀ፣
አዋሐደ ወዘተ ተብሎ እንደሚተረጎም ማስተዋል አለባችሁ። «ቀብዐ» «ቀብዐት» ወዘተ የሚሉ ቃላትን መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ ብታገኙ
ልትደናገሩ አይገባም። ቃሉ እንደ ቃልነቱ ምንም ችግር የለበትምና። ነገር ግን ትርጉሙ ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። «ቀብዐ»
ማለት በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ ማለት እንዳልኾነ ማስተዋል ይኖረብናል። ስለዚህ ጥንቃቄ እንድታደርጉ በማሰብ ቃሉን በማግኘታችሁም
እንዳትደናገጡ በማሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት በተረጎሟቸው የአንድምታ ትርጓሜያት ያገኘነውን ሙሉ
ትርጓሜ እነሆ ብለናል።
እዚህ ላይ ግን ኹላችሁም በቅብዐቶች ዘንድ የሚሰጠው ትርጉም
እና በቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት የተተረጎመው ምን ያህል እንደሚራራቅ በማስተዋል ልታነቡ እንደሚገባ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።
ተጨማሪ በቅብዐቶች የሚነሡ ሌሎች ጥቅሶችም አሉ እነዚያን ደግሞ
ወደፊት አምላክ ቢፈቅድ እና ታትማ ብትደርሳችሁ ያንጊዜ #ደብረ_አሚን ላይ ታገኙታላችሁ።
==================================
ላእለ እግዚአብሔር ወላእለ
መሢሁ በእግዚአብሔር አብ በእኔ በእግዚአብሔር ወልድ። በእግዚአብሔር ወልድስ ይኹን ሰቅለው ገድለውታል በእግዚአብሔር አብ ምን ብለው
ተነሡ ቢሉ ወልድ ቢነክ አብ ይነክ እንዲሉ ወልድን መስቀል መግደል አብን መስቀል መግደል ኾኖባቸዋልና ባያገኙት ቀርቶባቸዋል እንጂ። አንድም አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ የመሰከረለት
ወልድን እሩቅ ብእሲ ማለት አብን ዕሩቅ ብእሲ ማለት ነውና።
==================================
እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ አሁን አንተን አይሻም (ቃል
ይቤ በል) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ፣ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ። ወአነ ዮም ወለድኩከ አሁንም
«አነ» ን አይሻም ዛሬም በተዋሕዶ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ። ተውህቦ ለእግዚአብሔር ቃል ስም በሥጋ ዘበህላዌሁ ይሰመይ እንዲል
ስለ ሥጋ እንግድነት አንድም «ይቤ ሥጋ» አንተ ሥጋ ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ
ልጄ ነህ አለኝ። አንተ ልጄ ነህ ዛሬም በተዋሕዶ ወለድኩህ ማለት በቃል ርስት። አንድም አሁንም አንተን እና አነን
አይሻም (ሥግው ቃል ይቤ) ቅድመ ዓለም አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ ። ዛሬም
አውጻእኩከ አንሣእኩከ ሲል ነው። በትንሣኤ የወለድኩህ ልጄ ነህ አለኝ። አሁን ኹለተኛ የሚወልደው ኾኖ አይደለም በምሳሌ ተናገረው
እንጂ። ሰው ዘምቶ ያረጃል፤ በልቶ ያፈጃል። ሕዝብን ሰብስቦ ልጁን አስጠርቶ ልጄ «ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ይሉሃል እኔ ነኝ፤
በርስቴ ውጣበት ውረድበት» ብሎ ይሰጠዋል። እርሱም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ይዘምታል።
በርስቱ ርስት በጉልቱ ጉልት ጨምሮበት ይመጣል። አባቴ በሰጠኸኝ ርስት
ጉልት ጨምሬበት መጣሁ ይለዋል። እርሱም ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቅስ የዛሬው ይብለጥ ይለዋል። ጌታም ከአቤል ጀምሮ እስከ ዕለተ
ዓርብ ያሉትን ነፍሳት «እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሰቱ ወርእዩ ብርሃነ ዐቢየ» በገነት አድርጐ ባረገ ጊዜ ልጄ
ነህ አለው እንጂ።
==================================
ይህ ቃል በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ዕብ ፩÷፰-፱ ላይም ተጽፎ
እናገኘዋለን። የቅብዐት እምነት ተከታዮች ይህንንም እንደማታለያ ስለሚጠቀሙበት ትርጓሜው አንድ መኾኑን መናገር እንፈልጋለን።
አፍቀርከ ጽድቀ ወዓመፃ ጸላዕከ
በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር አምላክከ እውነትን ወደድህ ሐሰትን ጠላህ ማለት ትንቢተ ነቢያትን መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ
አንድም ሰው መኾንን ወደድህ አለመኾንን ጠላህ። ሰው እኾናለሁ ብሎ በነቢያት አናግሮ መቅረት መጥላት የነቢያትን ነገር ሐሰት ማድረግ ነውና፤ አንድም
ቀጠሮ መፈጸምን ወደድህ አለመፈጸምን ጠላህ። አንድም ጻድቅ አምላክ ወልደ አምላክ የሚልህን ወደድህ፤ ወዓማፄ ዕሩቅ ብእሲ ወልደ
ዮሴፍ የሚልህን ጠላህ።
በእንተዝ ቀብዐከ እግዚአብሔር
አምላክከ ሰው መኾንን ስለወደድህ አለመኾንን ስለጠላህ የባሕርይ አባትህ
እግዚአብሔር አብ አዋሐደህ። አንድም እግዚአብሔርነትህ አምላክነትህ አዋሐደህ። ቅብዓ ትፍሥሕት እምእለ ከማከ እምእለ ከማከ እንዳንተ
ያሉ ነቢያት ካህናት ከተቀቡት ልዩ የሚኾን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት
ተዋሕዶን ተዋሐድህ። አንድም ነቢያት ካህናት ከተቀበሉት ልዩ የሚኾን ቅብዓ ትፍሥሕትን ማለት
ልዩ ተዋሕዶን ተዋሐድህ። ቅዱስ ጳውሎስ ዘይኄይስ ያለውን ዮሐንስ አፈወርቅ በዘይተ ፍሥሐ ብሎ ወስዶታል። ዘይኄይስ ማለቱ የእርሱ
የማይነሣ ሕጸጽ የሌለበት የባሕርይ የእነርሱ የሚነሳ ሕጸጽ ያለበት የጸጋ የሱ ከራሱ የእነርሱ ግን ከእርሱ ነውና።
==================================
ናሁ ቊልዔየ ዘአኀዝክዎ እነሆ
በስልጣኔ የያዝኩት ዘሩባቤል። ወእስራኤልኒ ኅሩይየ የመረጥኩት ዘሩባቤል። ዘተወክፈቶ ነፍስየ ልቡናየ የወደደችው ዘሩባቤል። ወወሀብኩ
መንፈስየ ዲቤሁ መንፈሰ ረድኤትን ያሳደርሁበት ዘሩባቤል። ወናሁ ያመጽእ ፍትሐ ለአሕዛብ እነሆ ለአሕዛብ ኦሪትን ያስተምራል። ኢይኬልሕ
ወኢይጠርእ አይጮኽም፤ አይገነታም (በጥርአ ቃል እንዲል፤ ጥበብ ፲፯÷፲፰)። ወኢይሰምዕዎ ቃሎ በአፍኣ በአፍኣ ያሉ ሰዎች ቃሉን
አይሰሙትም። የቃሉን መለዘብ መናገር ነው።
አንድም ናሁ ቊልዔየ ዘአኀዝክዎ
በሥልጣን አንድ የምንኾን ልጄ ክርስቶስ። ወእስራኤልኒ ኅሩይየ የመረጥኩት ልጄ ክርስቶስ፣ ልብነቴ የወደደችው ልጄ ክርስቶስ፣ መንፈስ
ቅዱስን በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ያስቀመጥሁበት ልጄ ክርስቶስ፣ ለአሕዛብ ወንጌልን ያስተምራል። አይጮኽም አይገነታም በአፍኣ ያሉ
ሰዎች ቃሉን አይሰሙትም ማለት የቃሉን መለዘብ መናገር ነው። ከዚህ እንዲህ አለ፤ ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ በምኲራብ ይላል ዮሐ ፯÷፳፰
አይጣላም ቢሉ አይጣላም። ከዚህ እንዲህ ማለቱ በሥጋዊ ነገር አይከራከርም ሲል ነው። ከዚያ ወአልዐለ ቃሎ ማለቱ መንፈሳዊውን አሰምቶ
ያስተምራል ሲል ነው።
=================================
ይህ ቃል ሉቃ ፬÷፲፰-፲፱ ላይም ተጽፎ እናገኘዋለን። የቅብዐት
እምነት ተከታዮች ይህንንም እንደማታለያ ስለሚጠቀሙበት ትርጓሜው አንድ መኾኑን መናገር እንፈልጋለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍን
ገልጦ አነበበ ይላል ያነበበው ቃልም ይህ በኢሳይያስ ትንቢት ተጽፎ ያለውን ቃል ነውና ትርጓሜው ተመሳሳይ ነው። ሊቃውንቱም ብዙ
ቦታ እየደጋገሙ ጽፈውታል ተርጒመውታልም።
መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ
ዘቀብዐኒ ዘበእንቲአሁ ወአስተፍሥሖሙ ለነዳያን ፈነወኒ ስለሱ ነዳያን ትሩፋንን ደስ አሰኛቸው ዘንድ በኔ ያደረ መንፈሰ ረድኤት ላከኝ
ይላል ኢሳይያስ ወእፈውሶሙ ለቊሱላነ ልብ በቊስለ መከራ የተያዙትን አድናቸው ዘንድ ወእስብክ ሎሙ ግዕዛነ ለፂውዋን ለተማረኩት ነፃነትን
አስተምራቸው ዘንድ ማለት ሚጠትን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ። ወይርአዩ ዕውራን ዕውራነ ልቡና እስራኤል ያዩ ዘንድ ላከኝ። ወእስምዮ
ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሩየ ዕለተ ሚጠትን የተመረጠ እለው ዘንድ ወለዕለተ ፍዳ ኅሪተ ዕለተ ፍዳም ያላት ዕለተ ሚጠት ናት የባቢሎን
ሰዎች ፍዳን ስለተቀበሉባት ዕለተ ፍዳ አላት። ወአስተፍሥሖሙ ለልህዋን ሰባ ዘመን ያዘኑትን ደስ አሰኛቸው ዘንድ። ወእሁቦሙ ክብረ
ለእለ ይላህውዋ ለጽዮን ኢየሩሳሌምን አጥተው ላዘኑ ሰዎች ክብረ ሥጋን እሰጣቸው ዘንድ።
ወህየንተ ሐመድ ዕፍረተ ትፍሥሕት
ለእለ ይላህዉ ትቢያ ይበንባቸው ስለነበረ ፈንታ ላዘኑ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ ሽቱን እሰጣቸው ዘንድ ወልብሰ ክብር ህየንተ መንፈስ
ትኩዝ ሰባ ዘመን ስለአዘነ ልብ ፈንታ ደስ አሰኘው ዘንድ ፈነወኒ ላከኝ፣ አንድም መንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌየ ዘቀብዐኒ ዘበእንቲአሁ
አስተፍሥሖሙ ለነዳያን ፈነወኒ ያዋሐደኝ በህልውናዬ ያለ የእግዚአብሔር የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድም ሳይናበብ መንፈሰ
እግዚአብሔር ላዕሌየ በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ያዋሐደኝ እግዚአብሔር አብ ምእመናንን አስተምር ዘንድ ላከኝ አንድም መንፈስ
ዘዚአየ በህላዌ ለሊሁ ኀደረ ላዕሌየ ብሎ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ተረጒሞታልና ብሎ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ
ላዕሌየ በእኔ ህልው ነው ወዘበእንቲአሁ ቀብዐኒ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ምእመናንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ። ወእፈውሶሙ
ቊሱላነ ሥጋን በተአምራት ቊሱላነ ነፍስን በትምህርት አድናቸው ዘንድ።
ሌሎች ተጨማሪ አንድምታ ትርጓሜዎችን
ከደብረ አሚን ያነባሉ።
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
መልካሙ በየነ
ሰኔ ፬/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment