ጥቅምት ፩/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※ ※※※※※※※※
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው እነሆ ከሰማይ የወረድሁ የእግዚአብሔር ልጅ የሕይወት
ምግብ እኔ ነኝ እያለ ያስተምር ይመክር ይገስጽ ነበረ፡፡ ነገር ግን
ትምህርቱን የሚንቁ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው
በመሸ ጊዜ ሰማዩ ቀልቷልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ ማለዳም ሰማዩ ደምኖ ቀልቷልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ የሰማዩን ፊትማ መለየት
ታውቃላችሁ የዘመኑንስ ምልክት አትችሉምን፡፡ ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም
ብሎ ትቷቸው ሄደ፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን በክርስቶስ ትምህርት አያምኑም ለዚህም ነው ሁልጊዜ ትምህርቱን ለመስማት
ሳይሆን ሊፈትኑት የሚቀርቡ፡፡ እነዚህ ሰማይ ስላቀላ ብራ ይሆናል፤ ስለደመነ ዝናብ ይጥላል እያሉ ለራሳቸው ምልክትን የሚሹ ናቸው፡፡
የሰማዩን ምልክት በዚህ ይተረጉሙታል የዘመኑን ምልክት ግን አላወቁምና ምልክትን ፈለጉ፡፡
እግዚአብሔር ዝናብን ሊሰጠን ሲፈልግ ሰማይ ላይ ምልክት ማሳየት አይጠበቅበትም፡፡ አይተናል እኮ ከጭንጫ
ዓለት ላይ ውኃ ሲያፈልቅ ከሰማይ መና ሲያወርድ፡፡ አይተናል እኮ ሰማይ ሲለጎም ዝናብ መስጠት ሲያቆም፡፡ እርሱ ሁን ያለው ይሆናል
እርሱ አትሁን ያለው አይሆንም ሁሉ ነገር ከእርሱ ነው፡፡ የሰማይ እና የምድር ጌታ ፊት ቆመው እንድናምንህ ከሰማይ የወረድህ የእግዚአብሔር
ልጅ ነህ እንድንልህ ምልክት አሳየን አሉት፡፡ በእውነት እግዚአብሔርን እግዚአብሔር ነው ብለን ለመቀበል ምልክት መፈለግ አለብንን
የለብንም፡፡ ምክንያቱም ድንቅ ምልክቶችን የሚያደርጉ የዲያብሎስ ወገኖችም አሉና፡፡ ለመሆኑ እንዲያዩት የሚሹት ምን ዓይነት ምልክትን
ነው፡፡ እነርሱ ተአምራትን ማየት ይፈልጋሉ ምልክት ሲያደርግ መመልከትን ይሻሉ፡፡ እርሱም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ይሠራ ነበር፡፡
የዐራት ቀን ሬሳ ዓልአዛርን ሲያስነሣ በባዶ ግንባር ላይ ዓይን ሲፈጥር የ፴፰ ዓመት በሽተኛን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲል ማየ
ቃናን ወይን ሲያደርግ ዓይተናል ተመልክተናልም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ተአምራት ሲያደርግ የተደረገላችሁን ድንቅ ተአምር ለማንም
አትናገሩ እያለ ነበር የሚያሰናብታቸው፡፡ ሆኖም አንዳንዶች ለፈሪሳውያን እና ለሰዱቃውያን እየሄዱ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንዲህ ያለ
ድንቅ ተአምር አደረገልኝ እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያንም ጌታችንን ይህን ተአምር የሚያደርገው እኮ
በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል ነው ብለው ተራ ወሬ ማራገብ ጀመሩ፡፡ እዚህ ላይ ምልክት አድርግልን ይላሉ እዚያ ላይ ደግሞ በአጋንንት
አለቃ ምልክትን ያደርጋል ይሉታል፡፡ ከክፉ የልብ መዝገብ ክፉ ወሬ ከፉ አሳብ ብቻ ነው የሚመነጨው ለዚህም ነው ክፉ እና አመንዝራ
ትውልድ ምልክትን ይሻል ያለው፡፡
እኔ እግዚአብሔርን አምላኬ ነው ብየ ለማመን ምልክትን የምሻ ተአምራትን እንዲያደርግልኝ የምማጸን ከሆነ
እኔ ክፉ ወይም አመንዝራ ትውልድ ነኝ ማለት ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ ትውልዱ ምልክትን የሚሻ ተአምራትን የሚናፍቅ ክፉ እና አመንዝራ ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜ
ድንቅ ተአምር ይሠራልናል እኮ አላስተውል ብለን እንጅ፡፡ ሰማይን ያለምሰሶ የዘረጋ ምድርን ያለመሠረት በውኃ ላይ ያጸና አምላክ
በእውነት ሌላ ምልክትን እንዲሰጠን እንዴት እንለምነዋለን፡፡ ፀሐይን በቀን ከዋክብት ጨረቃን በሌሊት ያሰለጠናቸውን አምላክ ሌላ
ምልክት እንዴት ስጠን እንለዋለን፡፡ ፀሐይን በምሥራቅ አውጥቶ በምዕራብ የሚያስገባ አምላክን እንዴት ካንተ ሌላ ምልክትን እንሻለን
እንለዋለን፡፡ ጨለማውን አስወግዶ ብርሃንን የሚያመጣልንን አምላክ እንዴት ሌላ ምልክት አሳየን እንለዋለን፡፡ ተኝተን በዚያው እንዳንቀር
ቀስቅሶ የሚያስነሣንን አባት እንዴት ሌላ የተለየ ምልክትን እንሻበታለን፡፡ ይህ የምንሻው ምልክት ተአምር ነው፡፡ በእርግጥ ተአምራትንም
የምንሻ ሲደረጉ እንድናይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ ተአምራትን አንፈልጋቸው ይኾናል፡፡ ተአምረ ማርያም፣ ተአምረ ኢየሱስ
፣ተአምረ መላእክት፣ ተአምረ ቅዱሳን፣ ተአምረ ጻድቃን፣ ተአምረ ሰማእታት ሲነበቡልን እንቅልፋችን ይመጣል ነገር ግን ምልክትን እንሻለን፡፡
የምንሻው ምልክት፡- ወይ እኛ ላይ እንዲደረግ ወይ እኛ እንድናደርገው አልያም ዓይናችን እያየ ሌላ ሰው ላይ እንዲደረግ ነው፡፡
በእርግጥ ፊልም እና የእግር ኳስ ሲመለከት የሚውል ዓይን ከዚህ የተለየ ማየት አይፈልግም፡፡ በቃ ሁሉ ነገር በቀጥታ ስርጭት ሲሆን
ብቻ ነው ደስ የሚለው፡፡ እውነትም ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡
በሀገራችን እንደተለመደው የመብራት መጥፋት ለውኃ መሄድ ምልክት ነው፤ የዝናብ መዝነም ለመብራት መሄድ ምልክት
ነው፡፡ ስለዚህ ዝናም ሊዘንብ ከሆነ ዛሬ መብራት ይጠፋል እንላለን፡፡ መብራት ከጠፋ ደግሞ ዛሬ ውኃ ትሄዳለች እንላለን፡፡ ይህ
በቃ የተለመደ ምልክታችን ሆኗል፡፡ የሚገርመው ነገር በበጋ መብራት ሲጠፋ ምን እንላለን መሰላችሁ “ዛሬ ደግሞ ምን ሆነው ነው ያጠፉት
ዝናም የለ ደመና የለ” እንላለን በቃ ምልክት አድርገን ይዘነዋላ፡፡ እንደዚህ ሁሉ አምላካችንንም አምላካችን ነው ብለን ለመቀበል
ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን እንሻለን፡፡ አምላካዊነቱን ለመቀበል ግን የምንሻው ምልክት ተአምራዊ ሥራን ነው፡፡
እውነተኛው ተአምር ከሰው ልጅ የአስተሳሰብ አድማስ በላይ ከኅሊናም በላይ ምጡቅ የማይደረስበት ለማንም የማይሰጥ
ልዩ ጸጋ ነው፡፡ ከመደበኛው የሰው ልጅ ተግባራትና ክዋኔዎች የተለየ ድርጊት ነው፡፡
ተአምር የምንለው እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ከጸጉራቸው ጫፉ ከልብሳቸው ዘርፉ ምንም
ሳይነካ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን ፫÷፳፮ እዚህ ላይ ልብ በሉ የእሳት የሁልጊዜ ተግባሩ ማቃጠል ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ቅዱሳን
ማቃጠል ተሳነው፡፡
ተአምር ማለት እንደ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድሰት እየሉጣ በፈላ ውኃ መካከል ገብቶ ሳይቀቀሉ መውጣት ነው፡፡
/ድርሳነ ገብርኤል ዘሐምሌ ፲፱ ተመልከት/ የፈላ ውኃ ከድንጋይ በቀር የተጣለለትን መቀቀል የሁል ጊዜ ተግባሩ ነው ሆኖም ግን ቅድስት
እየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን መቀቀል አልቻለምና እንደቀዘቀዘ ሆኖ ታየ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ዳንኤል ለተራቡ አናብስት ተጥሎ ምንም ሳይነኩ መውጣት ነው፡፡ ትን ዳን ፮÷፳፪ ተመልከት፡፡
አናብስት ያውም ርቧቸው ቀርቶ ጠግበውም ቢሆን እንኳ የተጣለላቸውን ያገኙትን ነገር አይምሩም ይሰባብራሉ እንጅ ይህ የአናብስት የዘወትር
ግብራቸው ነው፡፡ ነገር ግን ዳንኤልን ሰባብረው ለመብላት አልቻሉም እንዲያውም ለመስገድ ተገደዱና ሰገዱለትዳንኤልን በልተውራባቸውን
ከማስታገስ ይልቅ ረሃባቸውን መረጡ፡፡
ተአምር ማለት እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ በገባዖን ሰማይ ፀሐይን ማቆም በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃን ማዘግየት ነው፡፡
መጽ ኢያሱ ፲÷፲፪-፲፬ ተመልከት፡፡ ፀሐይ የዘወትር ግብሯ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ በኩል ወጥታ በማደሪያዋ ምዕራብ መግባት ነበር፡፡
ዛሬ ግን በኢያሱ ግዘት ጠላቱን ድል እስከሚያደርግ ድረስ ቆማ ቆይታለች፡፡
ተአምር ማለት እንደ ጴጥሮስ በውኃ ላይ እንደ የብስ መራመድ ነው፡፡ ማቴ ፲፬÷፳፱ ባህር እንደየብስ ሆና
ሰው ሄዶባት አታውቅም ምክንያቱም የማስጠም ግብር አላትና፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ና ብሎታልና ቅዱስ
ጴጥሮስ ሲራመድባት እንደየብስ ሆነችለት አላሰጠመችውም ነበር፡፡
ተአምር እንደ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባን ተነሥ ብሎ ማንሣት ነው፡፡ የሐዋ ፫÷፯ ከእናቱ ማኅጸን
ጀምሮ ዐንካሳ የነበረ ሰው ተንሥእ (ተነሣ) ሲባል አፈፍ ብሎ መነሣት አይችልም ነበር፡፡ የዚህ ደግሞ የባሰ ነበር መልካም በሚሏት
መቅደስ ደጅ የሚያስቀምጡት ሰዎች ተሸክመው ወስደው ነበር፤ አሁን ግን የማንንም እርዳታ ላይጠይቅ ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስና
ቅዱስ ዮሐንስ ተነሥ ብለው አስነሡት፡፡ እርሱም ተነሥቶ እስኪዘል ድረስ ደስታውን ገልጿል፡፡
ተአምር ማለት እንደበለዓም አህያ እንደቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥቶ መናገር ነው፡፡ ዘኁ ፳፪÷፳፰ አህያ
አፍ አውጥታ ስትናገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው የበለዓምን አህያ ነው፡፡ አህያዪቱ በለዓም ያላየውን የተመዘዘ ሰይፍ የያዘውን መልአክ
ተመልክታ መንገዷን መቀጠል አልችል ባለች ጊዜ በለዓም አብዝቶ ደበደባት፡፡ በዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የአህያዪቱን አፍ ከፍቶ
እንድትናገር አደረገ፡፡ በተመሳሳይ ሉቃ ፲፱÷፵ ላይ ፈሪሳውያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሆሳዕና በአርያም እያሉ
ያመሰግኑት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ገስጻቸው አሉት፡፡ እርሱም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ እንኳ የቢታንያ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል አላቸው፡፡
ተአምር ማለት እንደ ኤልያስና እንደ ኤልሳዕ ሙትን ማንሣት ነው፡፡ ኤልያስ አንድ ሙት ኤልሳዕ ሁለት ሙት
አነሥተዋል፡፡ ፩ኛ ፲፯÷፳፪ ላይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ የብላቴናው ነፍስ ወደርሱ ተመለሰች እርሱም ዳነ” ይላል፡፡
ኤልያስ እንዲህ የሞተውን ዮናስን አንሥቶታል፡፡ የኤልያስ በረከት እጥፍ ሆኖ ያደረበት ኤልሳዕም በሕይወቱ አንድ ከዐረፈ በኋላ ደግሞ
አንድ በድምሩ ሁለት ሙታንን አንሥቷል፡፡ ፪ኛ ነገ ፬÷፴፭ ላይ “ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ ደግሞም
ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕጻኑ ላይ ተጋደመ ሕጻኑም ዐይኖቹን ከፈተ” ይላል፡፡ ከዐረፈ በኋላም ኤልሳዕ ፪ኛ ነገ ፲፫÷፳፩ “ሰዎችም አንድ
ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ” ይላል፡፡
የሞተ ሰው ሲነሣ ያየነው እንግዲህ በኤልሳዕና በኤልያስ ነው፡፡
ተአምር ማለት እንደሙሴ ባሕርን ከፍሎ ህዝብን በሰላም ማሻገር ነው፡፡ ዘጸ ፲፬÷፳፩-ፍጻ ተመልከት፡፡ ባህር
ተከፍሎ ውኃ እንደግድግዳ ቆሞ የብስ ሆኖ ህዘብን ያሻገረ ባህር አይተን አናውቅም ነበር ዛሬ ግን ከእስራኤላውያን ጋር ስንሰለፍ
በሙሴ በትር ባህር ሲከፈል ውኃ ግድግዳ ሆኖ ሲቆም እነሆ ተመለከትን፤ በደረቅ መንገድም እነሆ ሄድን፡፡
ተአምር ማለት እንደ ሐዋርያት፣ እንደ አባ ኤፍሬምና እንደ አባ ባስልዮስ፣ እንደ አባ ሕርያቆስ የማያውቁትን
ያልተማሩትን አውቆ ተምሮ በቅቶ መገኘት ነው፡፡ የሐዋ ሥራ ፪ን ስንመለከት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እነርሱ ከሚያውቁት
ከሚናገሩት ቋንቋ በተጨማሪ ፸፩ ቋንቋ ተገልጾላቸው ህዝቡን ሁሉ በየራሳቸው ቋንቋ ለማስተማር በቅተዋል፡፡ ውዳሴ ማርያም የሰኞ አንድምታን
ስንመለከት ደግሞ በአስተርጓሚ ሲጨዋወቱ የነበሩት ባስልዮስና ኤፍሬም በጸሎታቸው የባስልዮስ ቋንቋ ጽርእ ለኤፍሬም፤ የኤፍሬምም ቋንቋ
ሱርስት ለባስልዮስ ተገልጾላቸው ያለአስተርጓሚ ተነጋግረዋል፡፡ በቅዳሴ ማርያም ምእራፍ ፩ አንድምታ ላይ ስንመለከት ደግሞ የምናገኘው
አባ ሕርያቆስን ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ግበረ ገብ ካህን ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ትእቢት የያዛቸው ካህናት ነገር
ሰሩበት፡፡ ቀድሰህ አቁርበን እንበለው ብለው ተነሡበት፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሰህ አቁርበን አሉት፡፡ ከዚያም ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ
ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን ማንን እናውጣለት እያሉ ነገር ሲሠሩ እነሆ የአምላክ እናት ምሥጢርን ሁሉ ገልጣለት “ጎሥዐ ልብየ
ቃለ ሰናየ፤ ልቤ መልካም ነገርን አወጣ” ብሎ አዲስ ቅዳሴ ለመድረስ በቅቷል፡፡
ይቀጥላል
ይቆየን፡፡
※※※※※※※※※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ድረ ገጽ፡- http://www.melkamubeyene.blogspot.com
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ድረ ገጽ፡- http://www.melkamubeyene.blogspot.com
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB
No comments:
Post a Comment